ቭላድሚር ፑቲን እና የቱርኩ አቻቸው ኤርዶዋን ተገናኝተው መወያየታቸው ተነገረ

የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን (ቀኝ) እና የቱርኩ አቻቸው ረሲፕ ታይፕ ኤርዶሃን (ግራ)።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን (ቀኝ) እና የቱርኩ አቻቸው ረሲፕ ታይፕ ኤርዶሃን (ግራ)።

በካዛኪስታን እየተካሄደ ካለው ስብሰባ ጎን ለጎን የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የቱርኩ አቻቸው ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን ተገናኝተው መወያየታቸው ተነገረ።

ሁለቱ መሪዎች በውይይታቸው ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል የሩሲያ ያጋዝ አቅርቦት ወደ አውሮፓ የሚደርስበት ሁኔታ እና የእህል ምርት ለዓለም ገበያ ማቅረብ ስለሚቻልበት መንገድ ተጠቃሽ ናቸው።

ቀደም ሲል ሁለቱ መሪዎች ሲገናኙ በጦርነት ውስጥ የሚገኙትን ሩሲያ እና ዩክሬን ለማደራደር ቱርክ ጥያቄ ልታቀርብ እንደምትችል የሞስኮ ባለሥልጣናት ጠቁመው ነበር።

ከዚህ በፊት ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመች በኋላ ሁለቱን አገራት ለማደራደር ቱርክ ያደረገችው ጥረት ፍሬያማ ሳይሆን መቅረቱ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ ከኪዬቭም ሆነ ከሞስኮ ጋር መልካም የሚባል ግንኙነት ያላት አንካራ፤ በጦርነቱ ምክንያት መንቀሳቀስ ሳይችሉ በዩክሬን ወደቦች ላይ ቆመው የነበሩ መርከቦች እንዲንቀሳቀሱ ሁለቱን አገራት አግባብታ ነበር።

ሐምሌ 2014 ዓ.ም. ላይ ቱርክ ሁለቱን አገራት ካደራደረች በኋላ እህል የጫኑ መርከቦች በጥቁር ባሕር በኩል አድርገው ከዩክሬን ወደቦች መንቀሳቀስ ችለው ነበር።

የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) አባል የሆነችው ቱርክ፤ ጦርነቱን ተከትሎ ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ የጣሉትን ማዕቀብ በመቃወም በሁለቱም ተዋጊዎች መካከል ተቀባይነት ሊኖራት የምትችል አደራዳሪ ተደርጋ ትወሰዳለች።

ቱርክን የጋዝ ማዕከል ማድረግ

ፕሬዝዳንት ቱፒን ከኤርዶዋን ጋር በካዛኪስታን ሲገናኙ፤ አገራቸው ለአውሮፓ አገራት ለምትለከው ጋዝ ቱርክን የምርቷ ዋነኛ መተላለፊ ማዕከል የማድረግ ሃሳብ እንዳላት ገልጸዋል።

ፑቲን የሩሲያን የጋዝ ምርት አውሮፓ ለማድረስ ሁነኛ መተላለፊ አገር ቱርክ ነች ብለው ስለመናገራቸው ተዘግቧል።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመች በኋላ ኖርድ ስትሪም ተብሎ የሚታወቀው እና ጀርመን ድረስ የተዘረጋው የጋዝ ማስተላለፊያ፣ በባልቲክ ባሕር ስር ሆነ ተብሎ ተፈጽሟል በተባለ ፍንዳታ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት እየሰጠ አይደለም።

ስምምነትን ማራዘም

ሠራተኞች

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ሁለቱ አገራት እህል የጫኑ መርከቦች እንዲያልፉ ከስምምነት መድረሳቸው ለበርካቶችም የሥራ እድልን ፈጥሯል።

የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን በበኩላቸው በአገራቸው አደራዳሪነት ሩሲያ እና ዩክሬን የደረሱት እህል የማስተላለፍ ስምምነት መራዘም አለበት ብለዋል።

ሁለቱ አገራት ጥሬ እህል የጫኑ መርከቦች ከዩክሬን ወደቦች ወደ ዓለም ገበያ እንዲንቀሳቀሱ የደረሱት ስምምነት ከአራት ሳምንታት በኋላ የሚያበቃ ነው። ይሁን እንጂ ሁለቱ አገራት የሚፈቅዱ ከሆነ የስምምነቱ ተፈጻሚነት ሊራዘም ይችላል።

ኤርዶዋን አገራቸው እና ሩሲያ፤ የሞስኮ ምርት የሆኑ የእርሻ ግብዓቶች እና ጥሬ እህሎች ወደየትኞቹ ታዳጊ አገራት ይላኩ በሚለው ላይ መወሰን ይችላሉ ብለዋል።

ፑቲን በበኩላቸው የዩክሬን እህልን የተቀበሉት አገራት ስምምነት እንዲደረስ ላስቻሉት የቱርክ ፕሬዝዳንት ምስጋና ማቅረብ አለባቸው ሲሉ ተደምጠዋል።