ተመድ ሩሲያ የዩክሬንን ግዛቶች መጠቅለሏን ባወገዘበት ጉባኤ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ድምጸ ተዓቅቦ አደረጉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተባበሩት መንግሥታት ሩሲያ የዩክሬን ግዛቶችን በኃይል መያዟን በከፍተኛ ድምጽ ባወገዘበት ጠቅላላ ጉባኤ የአፍሪካ አገራት የተከፋፈለ ድምፅ አሰምተዋል።
ሃያ ስድስት የአፍሪካ አገራት ሩሲያ በዩክሬን አራት ግዛቶች ላይ ያደረገችውን አወዛጋቢ ሕዝበ ውሳኔ እና ግዛቶቹን መጠቅለሏን በማውገዝ ድምፃቸውን አሰምተዋል።
ከዚህ ቀደም ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ የሚያወግዘውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውሳኔ ውድቅ ያደረገችውን ኤርትራን ጨምሮ 19 አገራት ደግሞ ድምጸ ተአቅቦ አድርገዋል።
ከእነዚህም መካከል የሩሲያ አጋሮች የሚባሉት ኢትዮጵያ፣ ማሊ፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሱዳን፣ ኡጋንዳ እና ዚምባብዌን ጨምሮ ሌሎች አገራት ይገኙበታል።
ድምጸ ተአቅቦ ካደረጉት መካከል ሦስቱ የሩስያ ከፍተኛ ዲፕሎማት ሰርጌ ላቭሮቭ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር አገራቸው ከአፍሪካ አገራት ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር በሚል የጎበኟቸው ናቸው።
ላቭሮቭ ኢትዮጵያን ጨምሮ በግብፅ፣ በዲሞክራቲክ ኮንጎ እና በኡጋንዳ ጉብኝት አድርገው ነበር።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አዲስ አበባ በነበራቸው ጉብኝት ለዓለም አቀፍ የምግብ ዋጋ መናር እና ለነዳጅ ቀውስ ተጠያቂዎቹ ምዕራባውያን አገራት ናቸው ሲሉ ወቅሰዋል።
ላቭሮቭ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እንዲሁም ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር ውይይት አድርገዋል።
በያዝነው ወር የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሜትሮ ኩሌባ አህጉሪቷ በሩሲያ ላይ ያላትን ድጋፍ ለመሸርሸር እና መሪዎቹ ዩክሬንን እንዲደግፉ ለማሳመን በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ጉብኝት አድርገዋል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምታደርገው የቦምብ ጥቃቶች መጠናከሩን ተከትሎ ጉብኝታቸውን ለማሳጠር ተገደዋል።
ቡርኪናፋሶ፣ ካሜሩን እና ኢኳቶሪያል ጊኒ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጠቅላላ ጉባኤ ላይ አልተገኙም።
ውሳኔው በ143 አገራት ድጋፍ ሲያገኝ ቻይና እና ሕንድ ግን ድምጸ ተአቅቦ አድርገዋል።
ሩሲያን ጨምሮ አራት አገራት ደግሞ ውሳኔውን ባለመቀበል የተቃውሞ ድምጽ ሰጥተዋል። ከሩሲያ ጋር አብረው የቆሙት ቤላሩስ፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ሶሪያ እና ኒካራጉዋ ናቸው።
ሩሲያ የዩክሬንን ከወረረች ወዲህ በዚህን ያህል ድምጽ ተቃውሞ ሲገጥማት የመጀመሪያው ነው።
ባለፈው ሳምንት እጅግ በደመቀ ሥነ ሥርዓት ፕሬዝዳንት ቪላድሚር ፑቲን ሉሃንስክ፣ ዶኔስክ፣ ዛፖሪዥያ እና ኬርሶን የሩሲያ አንድ አካል እንዲሆኑ ፊርማቸውን ማኖራቸው ይታወሳል።
ሉሃንስክ፣ ዶኔስክ፣ ዛፖሪዥያንና ኬርሶን የምሥራቅ ዩክሬን ግዛቶች ነበሩ።
ፑቲን ይህን ፊርማቸውን ያኖሩት ሩሲያ ሾማቸው ከነበሩ የግዛቶቹ አስተዳዳሪዎች ጋር ከተጨባበጡ በኋላ ነው።












