አዲስ አበባን የጎበኙት ላቭሮቭ ለዓለም የምግብ ገበያ ቀውስ ምዕራባውያንን ተጠያቂ አደረጉ

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Foreign Affairs - Ethiopia
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ፣ ለዓለም አቀፍ የምግብ ዋጋ መናር እና ለነዳጅ ቀውስ ተጠያቂዎቹ ምዕራባውያን አገራት ናቸው አሉ።
የስድስት ቀናት የአፍሪካ ጉዟቸው ማጠናቀቂያ ላይ ላቭሮቭ ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት “ይህ ቀውስ ከሩሲያ እና ከዩክሬን ጦርነት ቀደም ብሎም የነበረ ነው” ብለዋል።
“እውነት ነው፣ የምግብ ገበያው ዩክሬን ውስጥ ባለው ሁኔታ ተጽዕኖ አድሮበታል። ነገር ግን ይሄ የሆነው በሩሲያ ዘመቻ ምክንያት ሳይሆን ባልተገባው የምዕራባውያን እርምጃ ነው” ብለዋል።
አክለውም “ምዕራባውያን ያልተገባ እርምጃ ወስደው ማዕቀቦች በመጣላቸው ምክንያት የምግብ ገበያው ተመሳቅሏል” ሲሉ የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አዲስ አበባ ላይ ተናግረዋል።
ላቭሮቭ ከኢትዮጵያው አቻቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋርም የሁለትዮሽ ምክክር አድርገዋል።
አዲስ አበባ ውስጥ ባደረጉት ንግግር፣ የዓለም የምግብ ገበያ መናወጥ የጀመረው ኮሮናቫይረስ በተነሳበት ወቅት እንደሆነ ገልጸዋል።
ይህ ወቅት ምዕራባውያን በትሪሊዮን የሚቆጠር ዶላር አውጥተው ያለ አሳማኝ ምክንያት ምግብ የገዙበት እንደሆነም አክለዋል።
የማዳበሪያ ዋጋ የጨመረው በምዕራባውያን ዘንድ አረንጓዴ ሽግግር በተባለው ሂደት ምክንያት እንደሆነ ላቭሮቭ በንግግራቸው ጠቅሰዋል።
ይህንን የሽግግር ፖሊሲ “ግድ የለሽ” ያሉት ላቭሮቭ፣ ይህ ፖሊሲ ዋነኛ ኃይል አመንጪዎችን ገሸሽ ያደረገ እንደሆነም ገልጸዋል።
ማክሰኞ አመሻሽ ላይ ለይፋዊ ጉብኝት አዲስ አበባ የገቡት ሰርጌይ ላቭሮቭ፣ ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እንዲሁም ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር ውይይት አድርገዋል።
ባለሥልጣናቱ የሁለቱን አገራት ወዳጅነትን በማጠናከር፣ በምጣኔ ሀብት፣ በንግድ፣ በሳይንስ እና በቴክኖሎጂ የሚያደርጉትን በማጎልበት ላይ ተወያይተው ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገልጸዋል።
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በአዲስ አበባ ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቀው ሽኝት እንደተደረገላቸው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳውቋል።
ላቭሮቭ ሩሲያ ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር በሚል ካለፈው ሳምንት ማብቂያ ጀምረው በግብፅ፣ በዲሞክራቲክ ኮንጎ በኡጋንዳ እና በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገዋል።
አፍሪካ 40 በመቶ ስንዴ የምታገኘው ከዩክሬን ሲሆን፤ በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የስንዴ ምርት እጥረት እንደተከሰተ አይዘነጋም።
የዩክሬንን የጥራጥሬ የውጭ ንግድ ለማስቀጠል ባለፈው ሳምንት የተደረሰው ስምምነት ግን ገበያውን እንደሚስተካከል ተስፋ ፈንጥቋል።












