የአብራሪዎችን አእምሮ ያነባሉ የተባሉት የመጪው ዘመን ተዋጊ ጄቶች

ቴምፐስት ምስል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የብታኒያ ጦር ጥቅም ላያ አውሎት የነበረው ‘ስፒትፋየር’ የጦር ጄት አጀብ አስብሎ ነበር።

አብራሪዎች ስፒትፋየር ጄትን የምንቆጣጠረው ልክ እንደ አንድ የሰውነት ክፍላችን ነው በማለት ጄቱን ማብረር ምን ያክል ቀላል እና ምቹ እንደሆነ ገልጸው ነበር።

የ2030 አብራሪዎች ግን ከዚህም የመለጠ ቀላል ትስስር ከሚያበሯቸው የጦር ጄቶቻቸው ጋር ይኖራቸዋል።

የወደፊቶቹ የጦር ጄቶች ለአብራሪዎቻቸው ከመታዘዝም ባለፈ የአብራሪዎቻቸውን አእምሮ ማንበብ ይጀምራሉ ተብሏል።

‘ቴምፐስት’ የሚል ስያሜ የተሰጠው የጦር ጄት በዩናይትድ ኪንግደም ቢኤኢ ሲስተምስ፣ ሮልስ-ሮይስ፣ ኤምዲቢኤ ከተሰኘው ሚሳኤል አምራች ኩባንያ እና ከጣሊያኑ ሊዮናርዶ ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል።

ይህ ዘመናዊ ጄት ይዞት ከሚመጣው አማራጮች (ፊቸርስ) መካከል አንዱ አብራሪዎች ሥራ ሲበዛባቸው ወይም አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ሲገቡ እርዳታ መለገስ የሚያስችል አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ [ሰው ሰራሽ ልህቀት] አለው።

አብራሪዎች የሚያደርጉት የራስ ቅል መከላከያ (ሄልሜት) የአብራሪውን የአእምሮ መልዕክቶችን እና ሌሎች ለውጦችን ይከታተላል።

ለምሳሌ አብራሪው እራሱን ቢስት ይህ ሰው የላቀ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጀቱን የመቆጣጠር ኃላፊነትን ይረከባል።

አምራቹ ቢኤኢ ሲስተምስ ይህ የጦር ጄት እአአ 2027 ላይ የሙከራ በረራ ማድረግ እንደሚጀምር ገልጿል።

ይህ በግንባታ ላይ ያለው ቴምፐስት ጄት በጊዜ ሂደት መጠኑ እና ክብደቱ እያነሰ መጥቷል። የሙከራ በረራ ማድረግ ሲጀምርም በሰው አልባ አውሮፕላኖች ታጅቦ እንዲበር በማድረግ ክትትል ይደረግበታል።

የቴምፐስት ንግድ ልማት ዳይሬክተር ጆን ስቶከር፤ የወደፊቶቹን ጄቶች ማምረት ዘወትር እየተቀያየረ ከሚሄደው ቴክኖሎጂ ዘርፍ ጋር ተጣጥሞ መሄድን ይጠይቃል ይላሉ።

ወደፊትም የእነዚህን የጦር ጄቶች ሥርዓት ላይ ማሻሻያ ማድረግ (አፕግሬድ) ቢያስፈልግ አንድን መተግበሪያ ከኢንተርኔት ላይ አውርዶ ስልክ ላይ እንደመጫን ቀላል ይሆናል ይላሉ።

አብዛኛው የጄቶቹ ምርት የሚከናወነው በሮቦቶች ነው። ሮቦቶች መረጃዎችን ለአቅራቢያዎች እያደረሱ ግብዓቶች እንዲቀርቡ ያደርጋሉ።

ከዚህ የጦር ጄት ጋር ተመሳሳይ የሆነ ጄት እያበለጸገች ያለችው ጃፓን፤ በቴምፐስት ግንባታ ላይ ከብሪታኒያ እና ጣሊያን ኩባንያ ጋር ትብብር ታደርጋለች ተብሏል።

ሚስቲቡሺ የተሰኘው የጃፓን ኩባንያ ለአገሪቱ አየር ኃይል ሚስቲቡሺ ኤፍ-ኤክስ የተሰኘ የጦር ጄት እየገነባ ይገኛል።

ቴምፐስት እአአ 2018 ላይ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ቴምፐስት እአአ 2018 ላይ

የብሪታኒያ፣ የጣሊያን እና የጃፓን ኩባንያዎች በጦር አውሮፕላኖቹ ግንባታ ላይ መረጃ መለዋወጣቸው እና አብረው መስራታቸው ነገሮችን ቀላል ከማድረጉ በተጨማሪ ግንባታቸው ፈጣን እንዲሆን አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጆን ስቶከር ይናገራሉ።

እንደ ቦይንግ ላሉ ግዙፍ ኩባንያዎች የአውሮፕላን ሞተር የሚያቀርበው ሮልስ-ሮይስ ለቴምፐስት ጄት ሞተር የመስራት ኃላፊነት አለበት።

ሮልስ-ሮይስ ጄቱ ለመብረር የሚያስፈልገውን ኃይል ከመስጠት ባሻገር፤ ለአጠቃላይ የጦር አውሮፕላኑን ሥርዓት ጉልበት መስጠት ይኖርበታል።

የሮልስ-ሮይስ ከፍተኛ ኃላፊ የሆኑት ጆን ዋርደን፤ “ለዚህን አውሮፕላን ሥርዓት በሙሉ ኃይል መስጠት እንፈልጋለን” ይላሉ።

ኤምቢዲኤ የተሰኘው ጦር መሳሪያ አምራች በበኩሉ ጄቱ ላይ የሚገጠሙ ሚሳኤሎችን ያቀርባል።

የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት እስካሁን ድረስ ለቴምፐስት ፕሮጀክት 2 ቢሊዮን ፓውንድ ሰጥቷል። የጦር ጄቱ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት የመንግሥት ወጪ ገና በብዙ እጥፍ ሊጨምር እንደሚችል ይገመታል።

 'ታይፉን' ተዋጊ ጀት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በበርካታ የአውሮፓ አገራት ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘው 'ታይፉን' ተዋጊ ጀት

ቴምፐስት ማበልጸግ ለምን አስፈለገ?

በአሁኑ ወቅት ጠንካራ የሚባል ጦር ያላቸው አውሮፓውያን አገራት የሚጠቀሙባቸው ‘ታይፉን’ ጄቶች “የአየር ላይ ኃያልን” የሚል ስያሜ በበርካቶች ተሰጥቷቸዋል።

ታይፉን ተዋጊ ጄት በኤየርባስ፣ ቢኤኢ ሲስተምስ እና በጣሊያኑ ሊዮናርዶ ጥምረት የተገነባ ሲሆን፤ የብሪታኒያ፣ የጀርመን፣ የጣሊያ እና የስፔን አየር መከላከያዎች በዋናነት ይጠቀሙበታል።

ታይፉን ጄቶች እንዲገነቡ የብሪታኒያ መንግሥት 12 ቢሊዮን ፓወንድ ወጪ አድርጎ ነበር። ዛሬ ላይ የአገሪቱ መንግሥት ከእነዚህ ተዋጊ ጄቶች 21 ቢሊዮን ፓወንድ ማግኘቱን ይገልጻል። 20 ሺህ የሥራ ዕልም የጦር ጄቶቹ አስገኝተዋል።

ታዲያ ታይፉን ጄቶች ውጤታማነታቸው ከተመሰከረላቸው ቴምፐስት በከፍተኛ ወጪ መገንባት ለምን አስፈለገ የሚል ጥያቄ መነሳቱ አልቀረም።

ብዙዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ ላሉት ታይፉን ጀቶች ማሻሻያ አድርጎ በብዛት እንዲመረቱ ይጠይቃሉ።

ቢኤኢ ሲስተምስ ግን እአአ 2040 ላይ ዩናይትድ ኪንግደም እና አጋሮቿ፤ ውስብስብ በሆነ የቴክኖሎጂ ውጤት የታገዘ የደኅንነት ስጋት ስለሚገጥማቸው ስጋቱን ለመቀልበስ እንደ ቴምፐስት ያሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ያስፈልጋሉ ይላል።