ሰሜን ኮሪያ በሁለት ሳምንት ውስጥ ስድስተኛውን ሚሳኤል አስወነጨፈች

ዜና የሚመለከቱ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, EPA

ሰሜን ኮሪያ ሐሙስ ዕለት ሌላ ሁለት የባለስቲክ ሚሳኤሎችን የተኮሰች ሲሆን ይህም ከሁለት ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለስድስተኛ ጊዜ ያስወነጨፈችው መሆኑ ተገለጸ።

ፒዮንግያንግ በቅርቡ ያስወነጨፈችው ሚሳኤል፣ አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ለሚያደርጉት ወታደራዊ ልምምድ “ አፀፋዊ ምላሽ” መሆኑን ረቡዕ እለት አስታውቃለች።

ማክሰኞ ዕለት ፒዮንግያንግ በጃፓን ላይ ያለፈ ሚሳኤል ያስወነጨፈች ሲሆን ይህም አሜሪካ አስቸኳይ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባን እንድትጠራ አስገድዷታል።

በስብሰባው ላይ አሜሪካ፣ ሩሲያ እና ቻይናን ሰሜን ኮሪያን ከጠንካራ ማዕቀብ ተከላክለዋል ስትል ከሳለች።

በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር፣ "ሞስኮ እና ቤይጂንግ ተጨማሪ ማዕቀብ እንዳይጣልባት በመቃወም ለፒዮንግያንግ ሽፋን ሰጥተዋል" ብለዋል።

የቻይና እና የሩሲያ ተወካዮች በበኩላቸው ከቅጣት ይልቅ ያላሰለሰ ውይይት የተሻለ እንደሆነ ተናግረዋል።

ባለፉት ሁለት ወራት አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ሰሜን ኮሪያን እንዴት ማሸነፍ እንደሚቻል የሚያሳዩ እንዲሁም ጥቃቷን ለመከላከል ተከታታይ የጋራ ወታደራዊ ልምምዶችን ሲያካሂዱ ነበር።

ይህ ወታደራዊ ልምምድም ጠላቶቻቸው ለጦርነት እየተዘጋጁ እንደሆነ እንደ ማረጋጋጫ ያዩትን የሰሜን ኮሪያን መሪ ኪም ጆንግ ኡን አስቆጥቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ረቡዕ ዕለት አሜሪካ ፣ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ተጨማሪ ወታደራዊ ልምምዶችን ያካሄዱ ሲሆን ይህም ማክሰኞ ዕለት ለተወነጨፈው ሚሳኤል ምላሽ እንደሆነ ገልጸዋል።

አሜሪካ “የተከለከለ ሚሳኤል ማስወንጨፍ እና ወታደራዊ ልምምድ ማካሄድ የሚወዳደሩ ጉዳዮች አይደሉም” ብላለች።

በተጨማሪም አሜሪካ በኮሪያ ሰርጥ የኒዩክሌር አቅም ያለው ‘ዩኤስኤስ ሮናልድ ሬጋን’ የተባለ የጦር መርከብ የያዘ አውሮፕላን በድጋሜ አሰማርታለች።

ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን እንዳሉት ማክሰኞ ዕለት የተተኮሰው ሚሳኤል ከፍተኛ በሆነ 100 ኪሎ ሜትር ከፍታ 350 ኪሎሜትር እንደተወነጨፈ ተናግረዋል። ሁለተኛው ደግሞ በ50 ኪሎ ሜትር ከፍታ 800 ኪሎሜትር ተጉዟል።

ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ ያስወነጨፈችውና በጃፓን ድንበር ላይ ያለፈ ሚሳኤል ለመጨረሻ ጊዜ የተኮሰችው እንደ አውሮፖውያኑ 2017 ነበር።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ሙከራዎችን እያካሄደች ሲሆን ከአሜሪካ ጋርም የተደረገ ውይይት የለም። ፒዮንግያንግ በጃፓን ድንበር ላይ ያለፉ ሁለት ሚሳይሎችንም ተኩሳለች።

ሰሜን ኮሪያ እንደ አውሮፓውያኑ 2018 በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ወቅት በተካሄደ የአጭር ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ንግግር ወድሟል ያለችውን የኒዩውክሌር መሞከሪያ ሥፍራን እንደገና ማደራጀቷንም የሳተላይት ምስሎች አሳይተዋል።

ባለፈው ወር ሰሜን ኮሪያ የኒዩውክሌር ሕጎቿን ያሻሻለች ሲሆን መሪዋ ኪም ጆንግ ኡን አገራቸው “የማይቀለበስ” የኒዩውክሌር ኃይል እንዳላት አውጀዋል።

በዚህ ሁሉ ኪም አሁንም ሰባተኛውን የኒዩውክሌር ሙከራ ለማድረግ ፖለቲካዊ አጋጣሚ የሚጠብቁ ይመስላል።

የፖለቲካ ተንታኞች ሙከራው በዚህ ወር መጨረሻ ቻይና በምታካሂደው የኮሚዩኒስት ፓርቲ ምክር ቤት ስብሰባ እና ኅዳር ወር ላይ በሚደረገው የአሜሪካ ማሟያ ምርጫ መካከል ባሉት ሦስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ሊደረግ ይችላል ብለዋል።