ደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካ ሚሳኤሎችን በማስወንጨፍ ለሰሜን ኮሪያ ምላሽ ሰጡ

የፎቶው ባለመብት, SOUTH KOREAN MINISTRY OF DEFENCE VIA REUTERS
ደቡብ ኮሪያ እና እና ዩናይትድ ስቴትስ ሚሳኤሎችን ወደ ባህር በማስወንጨፍ በጃፓን የአየር ክልል ላይ ሚሳኤል ላስወነጨፈችው ሰሜን ኮሪያ ምላሽ መስጠታቸውን ሴዑል አስታወቀች።
ሚሳኤሎቹ የምስራቅ ባህር ወይንም የጃፓን ባህር ወደ ሚባለው ስፍራ መወንጨፋቸው ታውቋል። ስፍራው በኮሪያ ሰርጥ እና በጃፓን መካከል የሚገኝ ነው።
ሰሜን ኮሪያ በጃፓን ላይ ያለፈ ሚሳኤል ለመጨረሻ ጊዜ የተኮሰችው እአአ በ2017 ነበር።
በምላሹም ዩናይትድ ስቴትስ፣ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ልምምድ እያደረጉ ነው።
ረቡዕ ዕለት ደቡብ ኮሪያ እና ዩናይትድ ስቴትስ በጋራ አሜሪካ ሠራሽ ሚሳኤሎችን ተኩሰዋል።
አሜሪካ እና አጋሮቿ “ከሰሜን ኮሪያ ለሚቃጣባቸው ትንኮሳ ምላሽ መስጠት የሚያስችላቸውን ዝግጁነት እንዳላቸው” ለማሳየት መተኮሳቸውን የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የጸጥታ ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ለሲኤንኤን ገልጸዋል።
የሰሜን ኮሪያ ሚሳኤል ከተወነጨፈ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የወደቀ ሲሆን ጉዳት አላደረሰም ተብሏል።
ድርጊቱ የቶክዮን እና የዋሽንግተንን ትኩረት ለመሳብ ሆን ተብሎ የተደረገ ሊሆን ይችላል ተብሏል።
የጃፓን ጠቅላይ ሚንስትር ፉሚዮ ኪሺዳ ድርጊቱን “ጠብ አጫሪ” ሲሉ ገልጸውታል። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሃገራቸው ጃፓንን ለመከላከል ያላትን “ጠንካራ ቁርጠኝነት” ያለመቀየሩን በስልክ ለኪሺዳ ገልጸውላቸዋል።
ማክሰኞ ዕለት የኋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ጉዳዩን “አለመረጋጋት የሚፈጥር” ብለውታል።
ሚሳኤሎቹ የጃፓንን ድንበር ሲያቋርጡ ሆካይዶ ደሴትን ጨምሮ በሰሜን ሃገሪቱ ክፍል የሚገኙ ነዋሪዎች የማስጠንቀቂያ ድምጽ እና መልዕክት ተላልፎላቸዋል። “ሰሜን ኮሪያ ሚሳኤል አስወንጭፋለች። ራሳችሁን ወደ ህንጻዎች ወይንም ከምድር በታች ወደ ሚገኙ ስፍራዎች ሸሸጉ” የሚል አጭር የጽሁፍ መልዕክት ደርሷቸዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰሜን ኮሪያ ባሊስቲክ እና ኒውክለር መሳሪያዎችን እንዳትሞክር አግዷታል። ሚሳኤሎችን በሌሎች ሃገራት ድንበር ላይ ሳያስጠነቅቁ ወይንም ሳያማክሩ ማስወንጨፍም ዓለም አቀፍ ሕግን ይጻረራል።
ይህ ድርጊት በሰሜን ኮሪያ እና በጃፓን መካከል ያለውን ውጥረት አሳድጓል። ጃፓን እአአ ከ1910 እስከ 1945 ኮሪያ ቅኝ በመግዛቷ እና ሰሜን ኮሪያ የጃፓን ዜጎችን በማገቷ በሁለቱ ሃገራት መካከል ውጥረት እንዲኖር ካደረጉ ጉዳዮን መካከል ተጠቃሾቹ ናቸው።
ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ባለቤት መሆኗን የሚገልጽ ሕግ አውጥታለች። ይህም መሪው ኪም ጆንግ-ኡን ሃገሪቱ የኒውክለር ባለቤት እንዳትሆነ ከሚያደርግ ንግግር ያሚያርቅ ነው።












