በኢትዮጵያ በዓይነቱ የተለየ ነው የተባለው የሳይንስ ሙዚየም ተመረቀ

ዛሬ መስከረም 24/2015 ዓ.ም. በኢትዮጵያ በዓይነቱ የተለየ ነው የተባለ የሳይንስና ሥነ ጥበብ ሙዚየም በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ተመርቆ ተከፍቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መርቀው የከፈቱት ይህ ሙዚየም፣ የቀለበት ቅርጽ ያለውና መሃሉ ላይ የጉልላት ቅርጽ ያለው ህንጻን የያዘ ሲሆን በሰባት ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ነው።

ህንጻው በቀለበት ቅርጽ እና በጉልላት መልክ የተሰራ መሆኑ “ምሉዕነትን፣ የማያቋርጥ የከፍታ ጥረትንና ምኞትን ማሳያ፣ ረቂቅ ሆነውን የኢትዮጵያዊ ጥበብ እንዲሁም ኢትዮጵያ የወደፊቱን ቴክኖሎጂ ለመጨበጥ ያላትን ፍላጎት” የሚያሳይ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት በፌስቡክ ገጹ ላይ ገልጿል።

የሙዚየሙ ውስጣዊ ክፍል ወደ 1400 ሜትር ስኩየር ስፋት ያለው ድምጽ የማያስተላልፍ ቋሚ እና ጊዜያዊ የአውደ ርዕይ ቦታዎችን የያዘ ነው።
ሙዚየሙ ካረፈበት ቦታ 80 በመቶ የሚሆነው መሬትም ከአራት ሺህ በላይ አገር በቀል እጽዋትና ውብ አበቦች የተሸፈነ ነው ተብሏል። በቂ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራም አለው።
ከዚህም ባሻገር ሙዚየሙ ከተፈጥሮ ጋር በማይቃረን መልኩ የታነጸ ሲሆን የኤሌክትሪክ ኃይል ከፀሐይ ብርሃን እንደሚያገኝም ተዘግቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ ኢትዮጵያ አርተፊሻል ኢንተለጀንስን [ሰው ሰራሽ ልህቀት] በግንባር ቀደምትነት አስቀምጣለች ብለዋል።
ጨምረውም ሙዚየሙ ወጣቱ ትውልድም ሆነ ሌላው የሚጠይቁበት፣ አዳዲስ ነገሮችን የሚፈትሹበት፣ የሚመራመሩበት ለተለያዩ ፈጠራዎች መፈልፈያ መንደርደሪያ እንደሚሆን ተናግረዋል።
“ይህ ሥፍራ ለልጆቻችን ነው። ልጆቻችን በቪዲዮ፣ በፊልም እና በቨርቹዋል የሚያዩዋቸውን በአካል፣ በእጃቸው ነክተው ለማየት የሚስችል አውድ ፈጥሯል። የተሻለች ኢትዮጵያን ለመስራት የሚያነሳሳ ነው” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ።

በዛሬው ዕለት በዚሁ ሙዚየም በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲቱት አማካይነት አውደ ርዕይ የተከፈ ሲሆን ለሁለት ቀናት የሚቆይ አህጉራዊ ጉባኤም ተጀምሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጉባኤውን በንግግር የከፈቱ ሲሆን፣ በንግግራቸው አፍሪካውያን አርተፊሻል ኢንተለጀንስን ለአህጉሪቱ እድገት ለመጠቀም እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አብዮት ውስጥ መሆኗንም አክለዋል።













