የአል ጃዚራ ቢሮ ኃላፊ ልጅ ከእስራኤል በተተኮሰ ድሮን ተገደለ

የአል ጀዚራ የጋዛ ቢሮ ኃላፊ ወንድ ልጅ በገዛ ከእስራኤል በተሰነዘረ ጥቃት ተገደለ።
ሐምዛ አልዳህዱህ የአል ጃዚራ ኔትዎርክ ጋዜጠኛና የካሜራ ባለሙያ ሲሆን ከሌሎች ጋዜጠኞች ጋር የተገደለው በድሮን ጥቃት ነው።
ጋዜጠኞቹ ከኻን ዩኑስ ወደ ራፋህ በመጓዝ ላይ ነበሩ።
ጋዜጠኛው ሙስጠፋ ቱራያም ከተገደሉት ጋዜጠኞች መካከል ይገኝበታል።
በጋዛ የአል ጃዚራ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ዋእል አል-ዳህዱህ ቤተሰቦች ከዚህ ቀደም በጥቅምት ወር አራት ቤተሰቦቹ መገደላቸው ይታወሳል።
ባለቤቱ አሚና፣ የልጅ ልጁ አዳም፣ የ15 ዓመት ልጁ ማሕሙድ እና የ7 ዓመት ሴት ልጁ ሻም ሁሉም በእስራኤል ጥቃት የተገደሉ ናቸው።
የአል ጃዚራ ዘጋቢ ሐምዛ የነበረበት የጋዜጠኛ ቡድን ወደ ሰሜን ራፋ በአቋራጭ በጉዞ ላይ ነበሩ። ይህ አካባቢ ደግሞ በእስራኤል ከወታደራዊ ቀጠና ውጭ በሚል የተለየ ሰላማዊ አካባቢ ነበር።
አል ጃዚራ ባሰራጨው ቪዲዮ ጥቃት በተፈጸመ ቅጽበት የነበረውን ሁኔታና መኪናቸውን ያሳያል።
የጋዜጠኛው አባት ዋእል አል ደህዱህ ከሟች ልጁ አጠገብ እንባ እያነባ ይታያል።
ጋዜጠኛው በደቡባዊ ራፋህ ከተማ ተቀብሯል።
በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ አባቱ ባደረገው ንግግር ‘ልጄ ሐምዛ አካሌ ነበር። እኔነቴ ነበር። ነፍሴ ነበር። ይህ የሐዘን እንባ ነው። ልጅን የማጣት እንባ ነው የማነባው። ’ ሲል ስሜታዊ ስንብት አደርጓል።
“የዓለም ሕዝብ በጋዛ እየተፈጸመ ያለውን ግፍ ይመልከት’ ሲል ጥሪ አቅርቧል።
የአልጀዚራ የጋዛ ቢሮ ኃላፊ ዋእል አልዱህዱህ ራሱ በሌላ ቦታ የመቁሰል አደጋ ደርሶበት ነበር። የሱ ካሜራ ባለሙያ የነበረው ሳመር አቡ ዳቃ ባለፈው ወር ተገድሏል።
ዋእል አልዱህዱህ ልጁን ከቀበረ በኋላ ወደ ዘገባ ሥራው ተመልሷል።
ሟቹ ሐምዛ አልዱህዱህ በኢኒስታግራም ላይ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ነበሩት።
ለመጨረሻ ጊዜ ከመገደሉ በፊት ያጋራው መልእክት ስለ አባቱ ነበር። “ አባቴ ሆይ! አንተ የማትንበረከክ እና ታጋሽ ነህ። በፈጣሪ ደግነት አትጠራጠር። ፈጣሪ ይክስሃል” የሚል ነበር።
አልጀዚራ የእስራኤልን ጥቃት ያወገዘ ሲሆን ጥቃቱ ሆን ተብሎ የተፈጸመ ነው ይላል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን የጋዜጠኛውን ሞት ‘አሳዛኝ’ ብለውታል።
ቢቢሲ የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴርን ሐሳብ ለማካተት ሞክሯል።
የናታኒያሁ አማካሪ የሆኑት ማርክ ሬጌቭ እስራኤል ጋዜጠኞችን ሆን ብላ አትገድልም ብለዋል።
“በመካከለኛው ምሥራቅ ነጻ ፕሬስ የምንፈቅድ ብቸኛ አገር ነን። ጋዜጠኞች መንግሥትን እንዲተቹ የምንፈቅድ በዚህ ቀጠኛ እኛ ብቸኛዎቹ ነን” ብለዋል።
የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ 75 ጋዜጠኞች ተገድለዋል።
በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስትር በጋዛ 22ሺህ ፍልስጤማዊያን እንደተገደሉ አስታውቋል።












