የጠፋው የህንድ ወታደር አስከሬን ከ38 ዓመታት በኋላ ተገኘ

ቻንድራሼክሃር ሃርቦላ

የፎቶው ባለመብት, Hindustian Times

በሂማሊያስ ጠፍቶ የነበረው ህንዳዊው ወታደር አስከሬን ከ38 አመት በኋላ ተገኘ።

ቻንድራሼክሃር ሃርቦላ እና 19 ባልደረቦቹ በህንድ-ፓኪስታን ድንበር ላይ በሚገኘው ሲያቼን በተሰኘው ስፍራ በቁጥጥር ስራ ላይ እያሉም ነው በበረዶ ግግር መውጫ ያጡት።

በወቅቱ አስራ አምስት አስከሬኖች የተገኙ ሲሆን አምስቱ ግን ጠፍተዋል።

ሲያቼን የአለማችን ከፍተኛ የጦር አውድማ ሲሆን የሁለቱም ሃገራት ወታደሮች በማዕበል፣ በበረዶ ውሽንፍር ህይወታቸው ያልፋል።

የሃርቦላን አስከሬን ያገኘው የጦር ሰራዊት ሌላም አስከሬን ያገኘ ሲሆን የግለሰቡ ማንነት እንዳልታወቀ ፒቲአይ የዜና ወኪል ዘግቧል።

በሂማሊያ ኡታራክሃንድ ግዛት በሃልድዋኒ ወረዳ የሚኖሩት የሃርቦላ ቤተሰቦች አስከሬኑ መገኘቱ እርማቸውን እንዲያወጡ እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል። በመንደራቸው ሙሉ ወታደራዊ የቀብር ስነስርአት ተዘጋጅቷል። 

የአንድ ወታደር አስከሬን ከአሥርት ዓመታት በኋላ ሲገኝ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። በአውሮፓውያኑ 2014 ቱካራም ቪ ፓቲል የተገኘ ግለሰብ በበረዶ ግግር ውስጥ ከጠፋ ከ21 ዓመታት በኋላ በተቆጣጣሪዎች ተገኝተዋል።

ሲያቼን ህንድና ፓኪስታን ግዛቴ ነው በሚል የሚወዛገቡበት ስፍራ ነው። አካባቢውን ከጦርነት ቀጠና ነጻ ለማድረግ ውይይት ቢደረግም ሊሳካ አልቻለም።

ኒውክሌር የታጠቁት እነዚህ ጎረቤት ሃገራት የሲያቼን ስፍራ ለመቆጣጠር አጠር ያለ ጦርነት በአውሮፓውያኑ 1984 አድርገዋል።

ከአራት አስርት አመታት በኋላ የሁለቱም ሀገራት ወታደሮች አስከፊ በሆነው ስፍራ ሰፍረው ይገኛሉ።

በአውሮፓውያኑ 2012 ቢያንስ 129 የፓኪስታን ወታደሮች በሲያቼን የበረዶ ግግር በተነሳው ውሽንፍር ህይወታቸው አልፏል። ክስተቱ ሕንድ እና ፓኪስታን ወታደሮቻቸውን ከዚህ አወዛጋቢ አካባቢ እንዲያወጡ ጥሪ ቢያስነሳም ጎረቤቶቹ አገራት ውሳኔ ላይ ሊደርሱ አልቻሉም ።

በአውሮፓውያኑ 2016 ቢያንስ 10 የህንድ ወታደሮች በበረዶ ውሽንፍር ሲሞቱ ሌሎች አራት ደግሞ በ2019 በተመሳሳይ ሁኔታ ህይወታቸው አልፏል።