ለዓለም ዋንጫ ዝግጅት በርካታ የውጭ አገር ሠራተኞች የሞቱባት ኳታር የሠራተኞች አያያዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በጉጉት የሚጠበቀው የዓለም ዋንጫ ውድድሮች እሁድ ኅዳር 11/2015 ዓ.ም. ይጀመራል።
ከተለያየ የዓለማችን ክፍሎች የሚተሙ የእግር ኳስ ደጋፊዎችም በአስር ሺዎች በሚቆጠሩ ስደተኛ ሠራተኞች አማካኝነት በተገነቡ ስታዲየሞች ጨዋታዎችን ይመለከታሉ።
በሠራተኞች ላይ ሞትን ጨምሮ በርካታ የመብት ጥሰቶች ደርሰዋል በሚልም ኳታር ተደራራቢ ውግዘቶችን እያስተናገደች ትገኛለች።
በዓለም ዋንጫ ፕሮጀክቶች ላይ ስንት የውጭ አገር ሠራተኞች ተሳትፈዋል?
ኳታር ለዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ውድድር ሰባት ስታዲየሞችን እንዲሁም አዲስ አውሮፕላን ማረፊያ ፣ በርካታ መንገዶችን የሚያገናኝ መስመር እና 100 ያህል አዳዲስ ሆቴሎችን ገንብታለች።
የፍጻሜዎቹን ጨዋታ በሚያስተናግደው ስታዲየም ዙሪያ አንድ ሙሉ ከተማ ተገንብቷ።
የኳታር መንግሥት ስታዲየሞቹን ለመገንባት ብቻ 30 ሺህ የውጭ አገር ሠራተኞች መቀጠራቸውን አስታውቋል።
አብዛኛዎቹ ከባንግላዴሽ፣ ከሕንድ፣ ከኔፓል እና ከፊሊፒንስ የመጡ ናቸው።
በኳታር ስንት የውጭ አገር ሠራተኞች ሞተዋል?
ኳታር የዓለም ዋንጫ አዘጋጅነት ካሸነፈች በኋላ ከሕንድ፣ ከፓኪስታን፣ ከኔፓል፣ ከባንግላዲሽ እና ከስሪላንካ የመጡ 6 ሺህ 500 ስደተኛ ሠራተኞች መሞታቸውን ዘጋርዲያን በዘገባው አስነብቧል።
ይህ አሃዝ በኳታር የሚገኙ የየአገራቱ ኤምባሲዎች ያወጡትን መረጃ የተመሠረት ያደረገ ነው።
ይሁን እንጂ የኳታር መንግሥት የሞቱት ግለሰቦች በሙሉ ከዓለም ዋንጫ ጋር በተያያዙ ፕሮጄክቶች ላይ የሚሰሩ ስላልሆኑ መረጃው የተሳሳተ ነው ብሏል።
ከሟቾቹ መካከል ብዙዎቹ በኳታር ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ሲሰሩ እንደቆዩ እና በእርጅና ወይም በሌሎች የተፈጥሮ ምክንያቶች ሊሞቱ እንደሚችሉ ተናግሯል።
ከ2014 እስከ 2020 ባለው ወቅት ውስጥ በዓለም ዋንጫ ስታዲየሞች ግንባታ ላይ የነበሩ 37 የጉልበት ሠራተኞች መሞታቸውን የገለጸው የኳታር መንግሥት፣ ከእነዚህ ውስጥ ሦስቱ ሞቶች ብቻ “ከሥራ ጋር የተገናኙ” መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ ብሏል።
ይሁን እንጂ ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት በዚህ አይስማማም፣ በማለት በመንግሥት የቀረበው አሃዝ በጣም ዝቅተኛ ግምት ነው ይላል።
ኳታር በሥራ ላይ እያሉ በልብ ድካም እና በተንፈስ ችግር የሚሞቱትን ከሥራ ጋር በተገናኘ አድርጎ አድርጋ አትቆጥርም። ሆኖም እነዚህ የህመም ምልክቶች ከፍተኛ በሆነ ሙቀት እና በከባድ የጉልበት ሥራ ምክንያት በሙቀት ወላፈን ሲመቱ የሚመጣ ነው።
ተቋሙ ከዓለም ዋንጫ ጋር የተያያዙ አደጋዎችን በተመለከተ በኳታር ውስጥ በመንግሥት ከሚተዳደሩ ሆስፒታሎች እና የአምቡላንስ አገልግሎቶች የተሰበሰቡ መረጃዎች ላይ በመመስረት የራሱን አሃዝ አዘጋጅቷል።
በአውሮፓውያኑ 2021 ብቻ 50 የውጭ አገር ሠራተኞች መሞታቸውን እና ከ500 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት፣ 37 ሺህ 600 ደግሞ ቀላል እና መካከለኛ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሏል።
ቢቢሲ አረብኛም የኳታር መንግሥት የውጭ አገር ሠራተኞችን ሞት አሃዝ መቀነሱን የሚጠቁሙ መረጃዎችን ሰብስቧል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአገሪቷ የውጭ አገር ሠራተኞች አያያዝ እንዴት ይታያል?
በአውሮፓውያኑ 2010 ኳታር ዓለም ዋንጫን ለማዘጋጀት ውድድሩን ካሸነፈች በኋላ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በውጭ አገር ሠራተኞች አያያዟ ላይ ከፍተኛ ወቀሳ አሰምተዋል።
በአውሮፓውያኑ 2016 ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የኳታር ኩባንያዎችን የግዳጅ የጉልበት ሥራን ይጠቀማሉ ሲል ከሷል።
በርካታ ሠራተኞች በማያፈናፍንና በተጨናነቀ መጠለያ ውስጥ እንደሚኖሩ፣ ከፍተኛ የቅጥር ክፍያ እንዲከፍሉ መደረጋቸውን፣ ደመወዝ እንደተከለከሉ እና ፓስፖርታቸውም እንደተቀማ አስታውቋል።
ከአውሮፓውያኑ 2017 ጀምሮ መንግሥት የውጭ አገር ሠራተኞችን በጣም በሞቃታማ የአየር ሁኔታ ውስጥ እንዳይሰሩ ለመከላከል፣ የሥራ ሰዓታቸውን ለመቀነስ እና በሠራተኞች ካምፖች ውስጥ ያለውን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል አንዳንድ እርምጃዎችን እንደሚወስድ አሳውቆ ነበር።
ሆኖም ባለፈው ዓመት ሌላኛው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን ሂውማን ራይትስ ዎች የውጭ አገር ሠራተኞች አሁንም “በቅጣት እና ሕገወጥ በሆነ የደመወዝ ቅነሳ” እየተሰቃዩ መሆናቸውን ገልጿል። ለረጅም ሰዓታት አድካሚና የሚያንገላታ ሥራ ሰርተው ለወራት ደመወዝ እንዳልተከፈላቸውም አስታውቋል።
የኳታር ኩባንያዎች ከባርነት አይተናነስም በሚባልለት ካፋላ በተሰኘው የዓረብ አገራት ሕግን ተከትለው ይሰሩ ነበር። በዚህም አሰራር መሰረት ሠራተኞች ስፖንሰር ቢደረጉም ሥራቸውን መልቀቅ አይችሉም፤ ፖስፖርታቸውንም ይነጠቃሉ።
እንደ ዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት (አይኤልኦ) ባሉ ተቋማት ጫና ምከንያት የኳታር መንግሥት ካፋላን ቢያስቀርም፤ ነገር ግን አምነስቲ አሁንም ኩባንያዎች የጉልበት ሠራተኞች ቀጣሪዎች እንዳይቀይሩ ጫና ያደርጋሉ ብሏል።
በሠራተኛ ሕጉ ላይ ያለው ማሻሻያ የዓለም ዋንጫ ካለቀ በኋላም መቆም እንደሌለበት አስጠንቅቋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኳታር መንግሥት ስለ የውጭ አገር ሠራተኞች መብት ምን ይላል?
ከዓለም አቀፉ ሠራተኞች ተቋም ጋር በመተባበር የኳታር መንግሥት በርካታ ማሻሻያዎችን አድርጓል።
ከእነዚህም መካከል አሠሪዎች ለሠራተኞቻቸው በወቅቱ ክፍያ እንዲከፍሉ ለማድረግ የተነደፈ የደመወዝ ጥበቃ ዘዴን ያጠቃልላል።
የኳታር መንግሥት ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ማሻሻያው በኳታር የሚገኙ አብዛኞቹን የውጭ አገር ሠራተኞችን የሥራ ሁኔታ የለወጠ ነው።
“ማሻሻያዎቹ ተግባራዊ መሆናቸውንም ለማረጋገጥ እርምጃዎች ተወስደዋል” ብለዋል ቃል አቀባዩ ።
“እነዚህ እርምጃዎች በቀጠሉ ቁጥር ሕግን የሚጥሱ ኩባንያዎች ቁጥር ማሽቆልቆሉን ይቀጥላል” ሲሉም አስረድተዋል።
በዓለም ዋንጫ የሚሳተፉ ቡድኖችስ ምን አሉ?
ይህ ጉዳይ እስከ ፍጻሜዎቹ ጨዋታዎች ድረስ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚችል አመላካች ነው።
ዓለም አቀፉን እግር ኳስ የሚመራው ፊፋ ለዓለም ዋንጫ ተሳታፊ 32 ቡድኖች “ትኩረት ሰጥተው በእግር ኳስ ላይ እንዲያተኩሩ” የሚጠይቅ ደብዳቤ ጽፏል።
ስፖርቱን ወደ ርዕዮተ ዓለም ወይም ፖለቲካዊ “ጦርነት” መወሰድ ወይም “የሞራል ትምህርቶችን ለመስጠት መጠቀሚያ” መሆን የለበትም ብሏል።
ለፊፋ ደብዳቤም በምላሹ አሥር የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበራት “ሰብአዊ መብቶች ሁሉን አቀፍ እና በሁሉም ቦታ የሚተገበሩ ናቸው” ብለዋል።
የአውስትራሊያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ኳታር በስደተኛ ሠራተኞች ላይ በደል እየፈፀመች ነው በሚል ነቅፎ ቪዲዮ አውጥቷል።
የዴንማርክ ተጫዋቾች የኳታርን የሰብአዊ መብት አያያዝ ለመቃወም ሙሉ ለሙሉ ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ።












