የዴንማርክ ብሔራዊ ቡድን አስተናጋጇ ኳታርን በመቃወም የተለየ ማሊያ ሊለብስ ነው

የሀመል ምርት የሆነው ማሊያ

የፎቶው ባለመብት, ummel

ኳታር ያላትን የሰብአዊ መብቶች እና የስደተኛ ሠራተኞች አያያዝ ለመቃወም የዴንማርክ ብሔራዊ ቡድን “ደብዛዛ” ማሊያ ለብሶ በዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ እንደሚሳተፍ ተገለጸ።

የስፖርት አልባሳትን የሚያመርተው ሀመል ተጨማሪ የሐዘን መግለጫ ቀለም የሆነውን ሙሉ ጥቁር ማሊያ ለብሔራዊ ቡድኑ ዲዛይን አድርጓል።

የስፖርት ትጥቅ አምራቹ ሀመል እንዳለው “በሺዎች የሚቆጠር ሕይወት የበተገበረበት ነው” ባለው ውድድር ላይ “ዕይታ ውስጥ መግባት እንደማይፈልግ” ገልጿል።

“የዴንማርክ ብሔራዊ ቡድንን እንደግፋለን፣ ነገር ግን ይህ ኳታር በዓለም ዋንጫ ውድድር አስተናጋጅነቷ ከመደገፍ ጋር የሚመሳሰል አይደለም” ብሏል።

በተጨማሪ በማሊያው ዲዛይን ላይ ያለው የዴንማርክ አርማም “ደብዘዝ” እንዲል ተደርጓል። የቡድኑ የውድድር አልባሳት ቀይ የሚሆን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሙሉ ነጭ ይሆናል። ሦስተኛው ደግሞ ጥቁር ይሆናል።

የዴንማርክ ቡድን የመለማመጃ አልባሳት ስፖንሰር የሆነው ድርጅት ደግሞ፣ በኳታር ላይ ለሚሰነዘረው ተቃውሞ ቦታ ለመስጠት ሲል ሎጎው እንዲነሳ አድርጓል።

የኳታር መንግሥት የዓለም ዋንጫ ውድድር ከሚስተናገዱባቸው ስፍራዎች ግንባታ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው አልፏል በሚል የቀረበውን የስደተኛ ሠራተኞች አሃዝን የተቃወሙት ሲሆን፣ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት የሞቱት ሠራተኞች ቁጥር 37 ነው ሲል ገልጿል።

ሀመል እንዳለው “የአገሪቱን የዓለም ዋንጫ ማስተናገጃ ስታዲየሞችን በመገንባት ሥራ ላይ የተሳተፉ ስደተኛ ሠራተኞች አያያዝና በሰብአዊ መብት ይዞታዋ ላይ መግለጫ ማውጣት እንፈልጋለን። ስፖርት ሰዎችን ወደ አንድነት እንደሚያመጣ እናምናለን” ብሏል።

ነገር ግን የኳታርን የዓለም ዋንጫ ዝግጅትን የሚመራው ኮሚቴ በሀመል የቀረበውን ከሌሎች አገራት የመጡ ሠራተኞች ሞትን በተመለከተ ያለውን ተቃውሞታል።

ባወጣው መግለጫ ላይም “ከዴንማርክ እግር ኳስ ማኅበር ጋር ግልጽ እና ውጤታማ ውይይት አድርገናል” ብሏል።

“ለዓለም ዋንጫ ስታዲየሞች እና በሌሎች የውድድር ስፍራዎች ግንባታ ላይ የተሰማሩ 30,000 የሚደርሱ ሠራተኞችን ጤንነትና ደኅንነትን ለመጠበቅ በሐቅ ያደረግነውን ጥረት ለማጣጣል የቀረቡትን ነገሮች በሙሉ ልብ እንቃወማቸዋለን።

“ውድድሩ ዘላቂ ማኅበራዊ ቅርስ ጥሎ እንዲያልፍ ለማድረግ ከኳታር መንግሥት ጋር በመሆን በትጋት ሠርተናል” ብሏል።

በተጨማሪም ኮሚቴው የዴንማርክ እግር ኳስ ማኅበር ለስፖርት ትጥቅ አምራቹ ሀመል “የተደረጉትን ሰፊ ግንኙነቶች እና ያከናወንናቸውን ተግባራት በተመለከተ ውጤቱን በትክክል እንዲያሳውቅ” ጠይቋል።

በመጪው ኅዳር አጋማሽ ላይ የሚጀመረው የዓለም ዋንጫ ውድድር እየተቃረበ ባለበት ወቅት ቀደም ብሎ ዴንማርክ የሰብአዊ መብቶች አያያዝን በተመለከተ በፊፋ ላይ “ተጨማሪ ግፊት” እንደምታደርግ ገልጻ ነበር።

ቢቢሲ ስፖርት በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የፊፋን አስተያየት ጠይቆ ነበር።

የሌሎች ተቃውሞ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አምበል የሆነው ሃሪ ኬን፣ በውድድሩ ላይ በኔዘርላንድስ ቡድን የተጀመረውን ብዝሃነትን እና አካታችነትን ለማበረታታት እንዲሁም ማግለልን ለመቃወም ‘ዋንላቭ’ የሚል ጽሁፍ በክንዱ ላይ ለማሰር አቅዷል።

ቤልጂየም፣ ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ኖርዌይ፣ ስዊዲን፣ ዌልስ እና ስዊትዘርላንድ ይህንን ሃሳብ ደግፈውታል።

ኳታር በተገቢው መረጃ ላይ የተመሠረተ አይደለም በማለት ብትቃወመውም፣ የውጭ አገር ሠራተኞች አያያዝ ላይ እና ባላት ጥብቅ ፀረ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች ሕጓን ጨምሮ በሰብአዊ መብቶች አያያዟ ክፉኛ ስትተች ቆይታለች።

ኳታር የዓለም ዋንጫን ለማስተናገድ ሰባት አዳዲስ ስታዲየሞች፣ አንድ አየር ማረፊያ፣ አዳዲስ መንገዶች እንዲሁም 100 አዳዲስ ሆቴሎችን ገንብታለች።

የኳታር መንግሥት እንዳለው አብዛኞቹ ከባንግላዴሽ፣ ከሕንድ፣ ከኔፓል እና ከፊሊፒንስ የሆኑ 30,000 የውጭ አገር ሠራተኞች በስታዲየሞቹ ግንባታ ላይ ብቻ ተቀጥረው ተሳትፈዋል።

የሰብአዊ መብቶች ቡድኖች በኳታር ውስጥ ባለው የውጭ አገር ሠራተኞች አያያዝ ላይ እና ሕይወታቸው ባለፉት ሠራተኞች ቁጥር ላይ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል።

በፈረንጆቹ የካቲት ወር 2021 ላይ ዘ ጋርዲያን እንደዘገበው፣ ኳታር የዓለም ዋንጫን እንድታዘጋጅ ከተመረጠችበት ጊዜ አንስቶ ከሕንድ፣ ከፓኪስታን፣ ከኔፓል፣ ከባንግላዴሽ እና ከሲሪላንካ የመጡ 6,500 የውጭ አገር ሠራተኞች ሞተዋል።

ይህ የሟቾች ቁጥር የተገኘው ኳታር ውስጥ ከሚገኙት የየአገራቱ ኤምባሲዎች ነው።

ነገር ግን የኳታር መንግሥት በሰጠው ምላሽ፣ ይህ አጠቃላይ የሟቾች አሃዝ ሁሉም ከዓለም ዋንጫ ዝግጅት ጋር ከሚገናኙ ፕሮጀምክቶች ጋር የተያያዙ ሞቶች ባለመሆናቸው አሳሳች ነው ሲል ተቃውሞታል።

የኳታር መንግሥት እንደሚለው ከ2014 አስከ 2020 ድረስ ባሉት ዓመታት በተመዘገቡት አደጋዎች፣ ከዓለም ዋንጫ ስታዲየሞች ግንባታ ጋር በተያያዘ የሞቱ ሠራተኞች ቁጥር 37 ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ “ከሥራ ጋር የተያያዘው” ሦስት ብቻ ነው ብሏል።

የቢቢሲ አረብኛ አገልግሎት ባሰባሰበው መረጃ መሠረት የኳታር መንግሥት ከውጭ አገር የመጡ ሠራተኞች ሞትን በተመለከተ የሚያወጣቸው አሃዞች ዝቅ የተደረጉ ናቸው ብሏል።

ከዓለም ዋንጫ ዝግጅት ጋር በተያያዘ “የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ለደረሰ ጉዳት ወይም ሞት” ካሳ እንዲሰጥ የቀረበውን ጥሪ የእንግሊዝ እግር ኳስ ማኅበር እንደሚደግፈው ገልጿል።