ሩሲያ ከያዘችው የኼርሶን ከተማ ሰላማዊ ሰዎች እንዲወጡ ፑቲን በይፋ ወሰኑ

ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ፑቲን ትናንት አርብ በሩሲያ በሚከበረው የአንድነት ቀን ላይ ንግግር አድርገዋል

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አገራቸው በደቡብ ዩክሬን በቁጥጥሯ ሥር ካዋለችው የኼርሶን ግዛት ሰላማዊ ሰዎች እንዲወጡ መወሰናቸውን በይፋ አረጋገጡ።

የዩክሬን ጦር ቁልፍ ወደ ሆነችው የወደብ ከተማ የሚያደርገው ግስጋሴ ቀጥሏል።

ፑቲን በአደገኛ ቦታዎች የሚኖሩ ሲቪል ሰዎች መፈተን ስለሌለባቸው ሊለቁ ይገባል ብለዋል።

እስካሁን ቢያንስ 70 ሺህ ሰዎች ከኼርሶን የወጡ ሲሆን፣ ይህም ሩሲያ ወረራውን ከጀመረች በኋላ የተቆጣጠረቻት ብቸኛ ከተማ ናት።

ፑቲን ትላንት አርብ በአገሪቱ በሚከበረው የአንድነት ቀን ላይ ባደረጉት ንግግር ንጹሃን የተጋረጠባቸው ሽፍን የመደረግ እና የመጠቃት አደጋ “ሊወገድ” ይገባዋል ብለዋል።

ምንም እንኳን ሩሲያ ብትቀበለውም ዩክሬን ሞስኮ ሰዎችን ከአካባቢው በግዳጅ እያስወጣች ነው ስትል ትከሳለች። ይህም የጦር ወንጀል እንደሆነ ይታመናል።

ሩሲያ በሕዝብ መገልገያ መሠረተ ልማቶች ላይ በተከታታይ በሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮን) እና ሚሳኤል የምትሰነዝረው ጥቃት በሰዎች እና ንብረት ላይ ከባድ ጉዳት እያስከተለ ሲሆን ዩክሬን በተደጋጋሚ ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲቋረጥ ሰበብ ሆኗል።

ፑቲን በኼርሶን ጉዳይ አስተያየት ከመስጠታቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ የሩሲያ ወታደሮች ከኼርሶን እንደሚወጡ የሚያሳዩ ሪፖርቶች ወጥተው ነበር። ይህም ትልቅ የሚባል ማፈግፈግ እንደሆነ ተሰምቷል።

በኼርሶን በሩሲያ የተቋቋመው አስተዳደር ውስጥ ባለሥልጣን የሆኑት ኪርል ስትሪሞሱቭ ለሩሲያ መገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት የሞስኮ ጦር አካባቢውን ለቆ ሊወጣ ይችላል።

የዩክሬን ባለሥልጣናት እርምጃው የዩክሬንን ወታደሮች ወደ አደገኛ ቦታ የሚከት ወጥመድ ሊሆን እንደሚችል በመጠጠር ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ እየሰጡ ነው።

የኼርሶን ከተማ በሩሲያ ቁጥጥር ሥር የዋለችው ሞስኮ ዩክሬንን በወረረች ጥቂት ጊዜ ውስጥ ነው። ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዩክሬን ጦር የከተማዋን ዙሪያ መልሶ በቁጥጥሩ ሥር እያዋለ ነው።

በባለፈው ወር አጋማሽ የሩሲያ ጦር በከተማዋ ወደ መከላከል ስልት መግባቱን ተከትሎ ሲቪል ሰዎች ከተማዋን እንዲለቁ ማሳሰቢያ ደርሷቸው ነበር።

ቀጥሎም በርካታ የጦር አዛዦች የሚጠበቀውን ውጊያ ከማድረጋቸው አስቀድሞ የከተማዋን ነዋሪዎች ለማስወጣት የጀመሩት ዘመቻ መጠናቀቁን ሲናገሩ ተደምጠዋል።

ሩሲያ ኼርሶን እና ሌሎች ሦስት የዩክሬን ግዛቶች የእኔ ናቸው ስትል ትከራከራለች። ሆኖም አንዱም ግዛት ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሯ ሥር አይገኝም።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ውግዘት ቢገጠመውም ሩሲያ ባዘጋጀችው የተቻኮለ “ሕዝበ ውሳኔ” ግዛቶቹ ወደ ሩሲያ መቀላቀላቸው ተገልጿል።

ሩሲያ እንደ አውሮፓውያኑ በ2014 የክሪሚያ ባሕረ ገብ መሬትን ጠቅልላለች።

በቀዩ አደባባይ ትላንት ፑቲን ባደረጉት ንግግር በተጨማሪም 318 ሺህ ምልምል ወታደር የተመዘገበበት ጥሪ ከታቀደው 300 ሺህ ሰው በላይ በማሳካት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

ቁጥሩን ቢቢሲ በገለልተኛ ወገን ባያጣራውም ከተመዘገቡት ምልምል ወታደሮች 49 ሺህ የሚሆነው ወደ ግዳጅ መሰማራቱን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል የሩሲያው የግል ወታደራዊ ኩባንያ ‘ዋንገር ግሩፕ’ የመጀመሪያውን ይፋዊ ዋና መሥሪያ ቤት በሴንት ፒተርስበርግ ከተማ ከፍቷል።

የሩሲያ የግል ወታደራዊ ኩባንያ የሆነው ዋግነር በሴንት ፒተርስበርግ ከተማ ያለው አዲሱ ዋና መሥሪያ ቤት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የሩሲያ የግል ወታደራዊ ኩባንያ የሆነው ዋግነር በሴንት ፒተርስበርግ ከተማ ያለው አዲሱ ዋና መሥሪያ ቤት

የኩባንያው ተዋጊዎች ሩሲያ በዩክሬን በምታደርገው ዘመቻ ንቁ ተሳታፊዎች ሲሆኑ እስረኞች በተፈረደባቸው እስር ፈንታ በውጊያው እንዲሳተፉ እየመለመለ ይገኛል።

የዋግነር ወታደሮች በሶሪያ፣ በሊቢያ እና ሌሎች ግጭቶች ውስጥ ተሳታፊ በመሆን የሰብአዊ መበት ጥሰት ፈጽመዋል የሚል ክስ ይቀርብበታል።

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የወጣውን ሕግ በመቀየር በከባድ ወንጀል ተሳትፈው ከእስር ቤት የወጡ ሰዎችም እንዲካተቱ ፈቅደዋል።

ይህም ማለት በግድያ እና በአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር ተፈርዶባቸው በቅርብ ጊዜ ከእስር ቤት የወጡ ሰዎች በዩክሬን ጦርነት ላይ ይሳተፋሉ ማለት ነው።

ሆኖም በህጻናት ላይ ወሲባዊ ወንጀሎችን ፈጽመው ወይም በሽብር የተፈረዳባቸው ከእስር የተለቀቁ ሰዎች በጦርነት እንዲሰለፉ አይፈቀድላቸውም።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ለመጨረሻ ጌዜ ጦርነቱን በተመለከተ ባደረጉት ንግግር “ዛሬ ሩሲያን የሚያስተዳድሯት ሰዎች ግትር ናቸው” ብለዋል።

ጨምረውም ጠላቶቻችን የሰላም ንግግር አይፈልጉም ይልቅስ ከፍተኛ እልቂት ወዳለበት ቦታ ሰዎችን እየላኩ ነው ብለዋል።

በምሥራቃዊ ከተሞች አገራቸው እያደረገች ያለችውን ውጊያ “ከባድ” ብለውታል።