ቭላድሚር ፑቲን የቀድሞ እስረኞች በሠራዊቱ እንዲመለመሉ ፈቀዱ

በሩሲያ እስር ቤት ውስጥ የሚገኙ አስረኞች (ከፋይል የተገኘ ምስል)

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, በሩሲያ እስር ቤት ውስጥ የሚገኙ አስረኞች (ከፋይል የተገኘ ምስል)

ሩሲያ ቀድሞ የነበራትን ሕግ በመቀየር በግድያ እና በአደንዛዥ ዕጽ ማዘዋወር ተፈርዶባቸው በቅርብ ጊዜ ከእስር ቤት የወጡ ሰዎች በአገሪቱ ሠራዊት ውስጥ እንዲመለመሉ ተፈቀደ።

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የተጠባባቂ ጦር የክተት አዋጅን በተመለከተ የወጣውን ሕግ በመቀየር በከባድ ወንጀል ተሳትፈው ከእስር ቤት የወጡ ሰዎችም እንዲካተቱ ፈቅደዋል።

ሆኖም በህጻናት ላይ ወሲባዊ ወንጀሎችን ፈጽመው ወይም በሽብር የተፈረዳባቸው ከእስር የተለቀቁ ሰዎች በጦርነት እንዲሰለፉ አይፈቀድላቸውም።

በዩክሬን ወረራ የሩሲያ ወታደሮች ወንጀሎችን በመፈጸም ይከሰሳሉ።

የመንግሥታቱ ድርጅት በዩክሬን ምርመራ እንዲያደርግ ያቋቋመው ገለልተኛ ኮሚሽን ባለፈው መስከረም ባወጣው ሪፖርት፣ የሩሲያ ወታደሮች የጦር ወንጀል መፈጸማቸውን ገልጿል።

ይህም ‘የይድረስ ይድረስ’ ፍርድ በመስጠት ሰዎችን መግደልንና “የተወሰኑ” ወታደሮች ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት መፈጸማቸውን አመላክቷል።

ዩክሬን በበኩሏ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የጦር ወንጀል ሊሆኑ የሚችሉ ድርጊቶችን ሩሲያ መፈጸሟን ገልጻለች።

ሩሲያ ግን ሆን ብላ ንጹሃንን እንደማታጠቃ የገለጸች ሲሆን፣ ምንም እንኳን ዩክሬን ባትቀበለውም ወታደሮቿ በተገንጣይ ግዛቶች ላይ በመድፍ ንጹሃን ላይ ጥቃት ፈጽማለች ስትል ሩሲያ ከሳለች።

የተመድ ኮሚሽን የዩክሬን ወታደሮች የሩሲያን ወታደሮች ተገቢ ባለሆነ መነገድ መያዛቸውን የሚመለከት ሁለት ጥሰቶችን ማግኘቱን ገልጾ፣ የሩሲያ ድርጊትን “ትልቅ ቁጥር እንደሆነ ግልጽ ነው” ብሏል።

ባለፈው መስከረም የወጣ አንድ ሪፖርት በሩሲያ እስረኞች በዩክሬን ጦርነት እንዲሳሳተፉ እየተመለመሉ እንደሆነ እና በምላሹም ምህረት እንደሚደረግላቸው አመላክቷል።

የሩሲያ ሕግ የተፈረደበት ግለሰብ በሚሰጠው ማንኛውም አገልግሎት ምህረት እንደማያገኝ ቢገልጽም፣ አንድ ኃላፊ ግን ለእስረኞች ባደረገው አንድ ንግግር እስረኞች የሚስማሙ ከሆነ ተመልሰው ወደ እስር ቤት እንደማይገቡ ሲገልጽላቸው በቪዲዮ ተቀርጾ ይታያል።

በሩሲያ የክተት አዋጅ ጥሪ ከተደረገላቸው 300 ሺህ የተጠባባቂ ጦር አባላቱ እስከ መስከረም 49 ሺህዎቹ በዩክሬን ጦርነት ላይ መሰማራታቸውን ፕሬዝዳንት ፑቲን ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ በጽህፈት ቤታቸው ቁጥጥር ለሚደረግበት ሌላ የወታደር ምልመላ ንቅናቄ 50 ሺህ ሰዎች መመዝገባቸውንም ተናግረዋል።

ፑቲን ለተጠባባቂ ጦሩ የክተት ጥሪ ለማድረግ መወሰናቸው የሩሲያ ወታደሮች በጦርነት አውድማዎች ስኬት እንደራቃቸው የሚያመላክት ነው ሲሉ የወታደራዊ ጉዳይ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

በሺዎች የሚቆጠሩ ሩሲያውያን የክተት ጥሪውን በመቃወም ጥሪው ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮ ከአገር እየሸሹ ይገኛሉ።

ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረችበት ጊዜ ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን እና ታጣቂዎች ተገድለዋል ወይም ተጎድተዋል። ከተሞች ወድመው 7.8 ሚሊዮን ሰዎች በአውሮፓ አገራት ውስጥ በስደተኝነት የተመዘገቡ ሲሆን 2.8 ሚሊዮን የሚሆኑት በሩሲያ ይገኛሉ።