በዓለም ከፍተኛው የተባለውና 1.6 ቢሊየን ዶላር የሚያስገኘው ሎተሪ ዛሬ በአሜሪካ ይወጣል

ፓወርቦል ሎተሪ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ባለፉት ሦስት ወራት አሸናፊ ሳያገኝ የቆየው በአሜሪካ ቀዳሚ የሆነው ሎተሪ፣ ዛሬ ቅዳሜ በሚወጣው ዕጣ በዓለም እስካሁን ከታዩት የሎተሪ ዕጣ ሽልማቶች ከፍተኛውን ሊሰጥ ነው።

ይህ ፓወርቦል የተባለው የጃክፖት ሎተሪ ዕጣ ዛሬ ሲወጣ አሸናፊ የሚሆነው ግለሰብ ለመንግሥት ከሚቆረጥበት ግብር በፊት 1.6 ቢሊየን ዶላር ገንዘብ አሸናፊ ይሆናል።

ይህም የሎተሪ ዕጣ ሽልማት እስካሁን በዓለም ከተመዘገበው ከፍተኛው እንደሚሆን የተነገረ ሲሆን፣ በዚሁ ተመሳሳይ ሎተሪ ከስምንት ዓመት በፊት በወጣ ዕጣ ሦስት ባለዕድሎች ከፍተኛ የተባለውን ክብረ ወሰን 1.59 ቢሊዮን ዶላር አሸንፈው ተካፍለው ነበር።

ይህ የፓወርቦል የሎተሪ ጨዋታ የጀመረው በአውሮፓውያኑ 1992 ሲሆን፣ ዋና ከተማዋን ዋሽንግተንን፣ የባሕር ማዶ የአሜሪካ ግዛት የሆኑትን ፖርቶ ሪኮን እና ቨርጂን ደሴቶችን ጨምሮ በአሜሪካ 45 ግዛቶች ውስጥ ሎተሪው ይሸጣል።

ከፍተኛውን የሎተሪ ሽልማት ለማግኘት ሎተሪውን የቆረጡ ሰዎች የገዙት የሎተሪ ትኬት ስድስት ቁጥሮች ከአሸናፊው ቁጥር ጋር አንድ አይነት መሆን አለበት።

ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ ለተከታታይ 39 ጊዜ ዕጣ የወጣ ሲሆን ገንዘቡን የሚያስገኘውን አሸናፊውን ቁጥር የያዘ ሰው ሳይገኝ ቆይቷል።

ይህንን የሎተሪ ዕጣ የሚያሸነፍ ሰው ገንዘቡ በሰላሳ ዓመታት ውስጥ እየተቀናነሰ፣ ነገር ግን ሙሉውን የሎተሪውን የአሸናፊነት ገንዘብ መጠን እንዲከፈለው የማድረግ አማራጭ አለው።

ነገር ግን ከዚህ በፊት የሎተሪውን ዕጣ ያሸነፉ ሰዎች ሁሉም ለማለት በሚያስችል ሁኔታ፣ መጠኑ የሚቀንሰውን የአሸናፊነት ገንዘባቸውን በአንድ ጊዜ ለመውሰድ ነው የመረጡት።

ዛሬ በአሜሪካ የሚወጣውንና በሚሰጠው የሽልማት ገንዘብ መጠን ከፍተኛ ነው የተባለለትን የሎተሪ ዕጣ አሸንፈው በአንድ ጊዜ ገንዘቡን ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች የሚደርሳቸው ገንዘብ 782.4 ሚሊዮን ዶላር ነው።

ይህ ክፍያም ከአራት ወራት በፊት ላሸነፈው ግለሰብ ከተከፈለው ገንዘብ በብዙ እጥፍ የሚበልጥ ነው።

ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ፔንሲልቬኒያ ግዛት ውስጥ የሎተሪ ትኬቱን ገዝቶ ዕጣውን ላሸነፈው ግለሰብ የተሰጠው ገንዘብ 206.9 ሚሊዮን ዶላር ነበር።

እስከ ዛሬ ከፍተኛው የሎተሪ ዕጣ ተብሎ በታሪክ የተመዘገበው፣ እዚያው አሜሪካ ውስጥ በሦስት የተለያዩ ግዛቶች ነዋሪ የሆኑ ግለሰቦች በ2016 (እአአ) ያሸነፉት የፓወርቦል ሎተሪ ነው።

የሎተሪውን ሽልማት የተጋሩት ሦስት አሸናፊዎች ነዋሪነታቸው በቴኒሲ፣ በፍሎሪዳ እና በካሊፎርኒያ ግዛቶች ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦች ሲሆኑ፣ ሽልማቱን በአንድ ጊዜ ለመውሰድ በመፈለጋቸው በአጠቃላይ 327.8 ሚሊዮን ዶላር ተቀብለዋል።

የሎተሪውን ዕጣ ከቆረጡት ሰዎች መካከል በርካቶቹ አሸናፊ የሚሆኑ ከሆነ በዓመታት ውስጥ ሙሉውን የአሸናፊነት ገንዘብ ከመውሰድ ይልቅ የሚቀንሰውን መጠን በአንድ ጊዜ በእጃቸው ማስገባትን ይመርጣሉ።