ቀላል የሒሳብ ስሌት ተጠቅመው የ26 ሚሊዮን ዶላር የሎተሪ እጣዎችን ያሸነፉት ጥንዶች

የፎቶው ባለመብት, Jerry Selbee
የሎተሪ እጣ ማሸነፍ ለብዙዎች የማይፈታ፤ የማይሳካ ሕልም ነው።
አሜሪካውያኑ ጡረተኛ ጥንዶች ግን የሎተሪ ደንብ እና ግዴታዎችን በማጤን ‘ብልህ’ የሆነ የሒሳብ ስሌትን በመጠቀም የብዙዎችን ሕልም ማሳካት ችለዋል።
ጄሪ እና ማርጅ ሴልብ ባለፉት 10 ዓመታት አንዴ ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ አሸናፊ የሎተሪ ቁጥሮችን አግኝተዋል።
እአአ ከ2003 እስከ 2012 ባሉት ዓመታት ብልህ የሒሳብ ስሌታቸው 26 ሚሊዮን ዶላር አሳፍሷቸዋል።
ሚስጢራቸው ምንድን ነው?
የትኛውንም ሕግ ያልጣሰ “በሦስት ደቂቃዎች ውስጥ” መገመት የሚቻል የስታስቲክስ ስሌት ነው ይላል ጄሪ ሴልብ።
የእነዚህ ጥንዶች ታሪክ ብዙዎች አጀብ አሰኝቷል። 'ጄሪ ኤንድ ማርጅ ጎ ላርጅ' የተሰኘ የ 'ብሬኪንግ ባድ' መሪ ተዋናይ ብራይን ክራንስተን የተወነበት ፊለም በጥንዶቹ ሕይወት ዙሪያ ተሰርቶ ለዕይታ ቀርቧል።

የፎቶው ባለመብት, Paramount+
'መሠረታዊ የሒሳብ ስሌት ነው'
ጥንዶቹ ሙሉ ዘመናቸውን ሚሺጋን ግዛት በምትገኘ ኤቭረት በተሰኘች አነስተኛ ከተማ ነው የኖሩት።
ጄሪ እና ማርጅ 6 ልጆቻቸውን ያሳደጉት በከተማዋ ዋነኛ መንገድ ዳር ከሚያስተዳድሩት የሸቀጥ መደብር ነው።
ጥንዶቹ የጡረታ ዕድሜያቸው ላይ ከደረሱ በኋላ የሸቀጥ መደብራቸውን ሽጠው የቀረ ሕይወታቸውን እንዴት እንደሚመሩ ግልጽ ባልሆነላቸው ወቅት፣ ጄሪ አንድ የሎተሪ ማስታወቂያን ይመለከታል።
ጄሪ ማስታወቂያው ላይ የታተመውን የሎተሪው ደንብ እና ግዴታዎች ከተመለከተ በኋላ ትልቅ ዕድል እንዳለ ይረዳል።
ሎተሪውን ለማሸነፍ ዕድለኛው 6 የእጣ ቁጥሮችን መምረጥ አለበት። ማንም ሰው ስድስቱንም ካለገኘ፤ አምስት፣ አራት እና ሦስት ቁጥሮችን የገመቱ ሽልማቱን ይካፈላሉ።
ሁሉንም አሸናፊ ቁጥሮች በትክክል መገመት ከሚጠይቀው ‘ጃክ ፖት’ በተሻለ መጠን ይህ የተሻለ ዕድልን ይሰጣል።
ጄሪ፣ ባደረኩት ስሌት በርካታ ሎተሪዎችን ብገዛ የማሸነፍ ዕድሌ ከፍተኛ እንደሚሆን ተረዳሁ ይላል።
የ1ሺ 100 ዶላር ቲኬቶች ቢገዛ ቢያንስ አንድ ባለ አራት ቁጥር አሸናፊ የሆነ ቲኬት እንደሚኖረው ተገነዘበ።

የፎቶው ባለመብት, Paramount+
ባለ አራት ቁጥር እና 18 ባለ ሦስት ቁጥር አሸናፊ ቲኬቶችን 1050 ዶላር ወጪ አድርጎ ከገዛ በኋላ፤ 1ሺ 900 ዶላር ማግኘቱን ይናገራል።
ጄሪ ለሎተሪ ቲኬቶች ብዙ እያወጣ በምላሹ ከሎተሪ እጣ የሚያገኘውን ገንዘብ እያሳደገ መጣ።
3ሺ 600 ዶላር ወጪ አድርጎ 6ሺ 300 ዶላር አገኘ። ከዛም በ8ሺህዶላር ቲኬቶች ገዝቶ፤ 16ሺህዶላር አሸናፊ ሆነ።
ጥንዶቹ በዚህ አልተገደቡም።
በሎተሪ ቲኬቶች ላይ ብዙ ወጪ የሚያደርግ ኩባንያ ለማቋቋም መወሰኑ።
ጂኤስ ኢንቨስትመንት ስትራቴጂስ የተሰኘ ኩባንያ እውን አድርገው በአነስተኛዋ ከተማ ለሚገኙ ከገበሬዎች እስከ ጠበቆች የአክሲዮን ድርሻ መሸጥ ጀመሩ።
ይህ የተመሠረተው ኩባንያ ብዙ ቲኬቶችን እየገዛ የሽልማት መጠኑም እያደገ መጣ። በአንድ ግዜ 853ሺ ዶላር ማሸነፍ ችለው ነበር።
ይሁን እንጂ ጥንዶቹን አትራፊ ያደረገቸው የሚሺጋኑ ዊንድፎል ሎተሪ ሽያጩን አቆመ።
ከዚያም ጥንዶቹ በብዙ ርቀት ላይ በምትገኘው ማሳቹሴትስ ግዛት ተመሳሳይ ደንብ እና ግዴታዎች ያሉት ሎተሪ እንዳለ መረጃ ይደርሳቸዋል።
ጥንዶቹ ስድስት የአሜሪካ ግዛቶችን አቆራርጠው በዓመት 7 ጊዜ በአማካይ 600ሺ ዶላር ወጪ እያደረጉ ሎተሪ መግዛታቸውን ቀጠሉ።
ጄሪ እና ማርጅ ሎተሪ ለመግዛት በሄዱበት ማሳቹሴት ሆቴል አርፈው፣ በፈረቃ ተከፋፍለው በቀን ለ10 ሰዓታት ያህል የሎተሪ ቲኬቶቹን ማሰናዳት ይጠበቅባቸው ነበር።
“ለእኛ ብቻ ሳይሆን ጓደኞቻችንን እና የቤተሰብ አባላትን ውጤታማ የሚያደርግ በመሆኑ አስደሳች ነበር” ይላል ጄሪ።

የፎቶው ባለመብት, Paramount+
የጥንዶቹ እና የሎተሪ ቁርኝነት ማብቂያ
የጥንዶቹ እና የሎተሪ ቁርኝነት እአአ 2012 ላይ አብቅቷል።
ቦስተን ግሎብ የተሰኘው ጋዜጣ በማሳቹሴትስ የሚገኝ መደብር አሸናፊ ያደረጉ በርካታ አጠራጣሪ የሆኑ የሎተሪ ቲኬቶችን ሽጧል የሚል ምርመራ መጀመሩን ተከትሎ የጥንዶቹ ጉዞ ቆሟል።
የጋዜጣው ምርመራ ከጥንዶቹ በተጨማሪ የዝነኛው ማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ (ኤምአይቲ) ተማሪዎችም የካሽ ዊንድፎል ሎተሪ ቲኬቶችን በብዛት ይገዙ እንደነበረ አመላክቷል።
በቀጣይ የግዛቱ አስተዳዳሪዎች ሕጎች ተጥሰው እንደሆነ ምርመራ ቢያደርጉም፤ ምንም አይነት ማጭበርበርም ሆነ ሙስና አለመፈጸሙን አረጋግጠዋል።
“እነዚህ ሒሳብ አዋቂዎች ሕጋዊ መንገዶችን ተጠቅመው በሎተሪ እጣዎች ሚሊዮኖችን ማጋበሳቸው አስደንቆኛል” ሲሉ የግዛት መርማሪ ግሬግ ሱሊቫን ለሲቢኤስ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ጥንዶቹ ተጠቃሚ የሚሆኑበት አይነት ሎተሪ በአሜሪካ ቆሟል። አሜሪካውያኑ ጡረተኛ ጥንዶች ግን ቀድመው ሚሊዮን ዶላሮችን ሰብስበዋል።
ጄሪ እንደሚለው ከግብር በኋላ የተጣራ 8 ሚሊዮን ዶላር ወደ ባንካቸው ገቢ አድርገዋል።
በገንዘባቸው የቤተሰብ መኖሪያ ቤት አሳድሰዋል።
የስድስት ልጆቻቸውን፣ የ14 የልጅ ልጆቻቸውን እና የ10 የልጅ ልጅ ልጆቻቸውን ትምህርት ወጪ ሸፍነውበታል ወይም ለመሸፈን መድበውበታል።
ከሁሉም በላይ ጥንዶቹ የሎተሪ ውጣ ውረዳቸውን “አስደሳች” ነበር ሲሉ ያስታውሱታል።












