የፈረንሳይ የፓርላማ አባል “በዘረኛ” ንግግራቸው ከሥራ ታገዱ

የፓርላማ አባሉ ግሪጓር ዲ ፎርናስ

የፎቶው ባለመብት, National Assembly

የፈረንሳይ ቀኝ አክራሪ ፓርቲ የፓርላማ አባል ጥቁር ባልደረባቸው ስለስደተኞች እየተናገሩ ባለበት ሰዓት “ወደ አፍሪካ ሊመለሱ ይገባል!” በማለት ምክር ቤቱ ውስጥ በመጮሃቸው ከሥራቸው ለ15 ቀናት ታገዱ።

የፓርላማ አባሉ ግሪጎሪ ዲ ፎርናስ፣ ንግግራቸው ባልደረባቸውን ካርሎስ ማርቲንስ ቢሎንጎን ኢላማ ያደረገ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

“ንግግሬ በባሕር አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመግባት የሚሞክሩ ስደተኞችን የተመለከተ ነው” ብለዋል ፎርናስ።

ፈረንሳይ ውስጥ የተወለዱት ጥቁሩ የፓርላማ አባል ቢሎንጎ ግን የባልደረባቸውን ንግግር “አሳፋሪ” ሲሉ ገልጸውታል።

ይህንን ተከትሎ አርብ ዕለት የፓርላማ አባላት እርሳቸውን ከምክር ቤቱ ለማገድ እና ገቢያቸውን ለመቀነስ ድምጽ ሰጥተዋል።

በዚህም የፓርላማ አባሉ ለ15 ቀናት ከምክር ቤቱ የታገዱ ሲሆን፣ ውሳኔው በምክር ቤቱ የተሰጠ “እጅግ ከባዱ እቀባ” እንደሆነ ተገልጿል።

ቢሎንጎ፣ በቅርብ ቀናት የባሕር ሲሳይ ከመሆን ለተረፉት 234 ስደተኞች ማረፊያ ለመፈለግ ኤስኦኤስ ሜዲትራኒያን የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ያቀረበውን የእርዳታ ጥያቄ በተመለከተ ለፈረንሳይ መንግሥት ጥያቄ እያቀረቡ ባለበት ወቅት ነበር ፎርናስ አስተያየቱን የሰጡት።

የናሽናል ራሊ ፓርቲ አባሉ ስደተኞችን በተመለከተ አስተያየት የሚሰጡ ከሆነ ብዙ ቁጥርን የሚያመለክቱ ቃላትን መጠቀም ነበረባቸው በሚልም የሃሳባቸው ትክክለኛ ትርጉም አካራካሪ ሆኖ ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ፎርናስ፣ ከማይክራፎን ውጪ የተቀዳውና በፈረንሳይኛ ቋንቋ የሰጡት አስተያየት “ወደ አፍሪካ ሊመለስ ይገባል” የሚል ቢሆንም፣ ነጠላ እና ብዙ ቁጥር የሚያመለክቱት ቃላት ተመሳሳይ ድምጸት ስለነበራቸው ንግግራቸው አወዛግቧል።

ይህም ንግግራቸው የምክር ቤት አባሉን የሚመለከት ነው የሚል አሻሚ ትርጉምን በመያዙ ነው፣ ንግግራቸው ቅሬታን የፈጠረው።

የግራ ዘመሙ ፍራንስ አንባውድ ፓርቲ የፓርላማ አባሉ ቢሎንጎ በበኩሉ “ዛሬ በቆዳዬ ቀለም መጥቷል። የተወለድኩት ፈረንሳይ ነው። ፈረሳያዊ የፓርላማ አባልም ነኝ” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኤልዛቤጥ ቦርን “ለዘረኝነት ምንም ዓይነት ቦታ የለንም” ያሉ ሲሆን፣ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ጀራልድ ዳርማኒን በበኩላቸው የፓርላማ አባሉ ከሥራ መልቀቅ አለባቸው ብለዋል።

ፎርናስ፣ አስተያየቱን የሰጡት ስደተኞችን ወደ አውሮፓ የምታጓጉዘውን ጀልባ ቢሎንጎ እየጠቀሱ እያለ ነው ሲሉ የቀረበባቸውን ክስ አልተቀበሉትም።

የፓርቲያቸው መሪ ማሪን ሊ ፔን በበኩላቸው ተቃዋሚዎቻቸውን “ያልተገባ ጩኸት ፈጥረዋል” ሲሉ ከስሰዋል።

ይሁን እንጂ በኋላ ላይ ፎርናስ የሰጡት አስተያየት ቢሎንጎን ጎድቶት ከሆነ ለተፈጠረው አለመግባባት ይቅርታ ጠይቀዋል።

የግራ ዘመሙ ኤልኤፍአይ ፓርቲ መሪ ጂን ሉክ መለንቾን በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ የፓርላማ አባሉ የሰጡት አስተያየት “የምንታገሰው አይደለም” ሲሉ ከምክር ቤቱ መባረር አለባቸው ብለዋል።

በዚህ ዓመት በተካሄደውና በፓርቲው ፕሬዝዳንታዊ እና የፓርላማ የምርጫ ዘመቻዎች ስደት ዋነኛ መከራከሪያ ነጥብ የነበረ ሲሆን፣ የቀኝ አክራሪው ፓርቲ መሪዋ ሊ ፔን፣ ፕሬዚደንት ሆነው ከተመረጡ ስደተኞችን ለመቀነስ የሚያስችል ሃሳብ አቅርበው ነበር።

ሰኔ ወር ላይ በተካሄደው የፓርላማ ምርጫ ፓርቲው 89 መቀመጫዎችን በማሸነፍ በብሔራዊ ምክር ቤቱ ውስጥ ያለውን ተሳትፎ በአስር እጥፍ ጨምሯል።