ሲም ካርድ ከመቀየር እስከ ጽንስ ማቋረጥ የደረሰው የአውስትራሊያ እግር ኳስ ዘረኝነት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአውስትራሊያ እግር ኳስ ሊግ በአገሪቱ በጣም ውጤታማ ከሆኑት ክለቦች የአንዱ ከአገሪቱ ቀደምት ነዋሪዎች ከሆነው ማኅበረሰብ የመጡ ተጫዋቾች ላይ ከፍተኛ ጥቃት በአሰልጣኞች ደርሶባቸዋል በሚል ምርመራ ጀመረ።
እንደ አውስትራሊያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኤቢሲ) ዘገባ ከሆነ ተጫዋቾቹ ከቤተሰባቸው እንዲገለሉ እና ከፍቅር አጋሮቻቸው ጋር እንዲለያዩ ተነግሯቸዋል። በሌላ አጋጣሚ ደግሞ እርግዝና እንዲያቋርጡ ታዘዋል ሲል አመልክቷል።
ሃውቶን የተባለው እግር ኳስ ክለብ "አሳዛኝ" ያለውን ጉዳይ ለመመርመር ቃል ገብቷል።
ይህ የታወቀው ቡድኑ በነባር የአገሪቱ ተወላጆች [አቦርጂንስ] ዙሪያ ስላለው አያያዝ በተገመገመበት ወቅት ነው።
የሪፖርቱን ይዘት ጠንቅቆ የሚያውቀው ኤቢሲ ከ2005 እስከ 2021 ባለው ጊዜ ውስጥ መቀመጫውን ሜልበርን ባደረገው ክለብ ላሳለፉ ሦስት ተጫዋቾችን ቃለ መጠይቅ አድርጓል።
ሃውቶን ሃውክስ በመባልም ይታወቃል።
ከስፖርቱና በቤተሰቦቻቸው አንዱን እንዲመርጡ መገደዳቸውን ለመገናኛ ብዙኃኑ ተናግረዋል።
ሌላው ደግሞ አንድ አሰልጣኝ "ያልተወለደ ልጄን እንዳስወርድ እና የትዳር ጓደኛዬን መተው እንዳለብኝ ጠይቆኛል" ብለዋል።
"ሲም ካርዴን ከስልኬ እንዳወጣ እና በእኔ እና በቤተሰቤ መካከል ምንም ተጨማሪ ግንኙነት እንዳይኖር ተደርጌያለሁ። ከዚያ ምሽት ጀምሮ ከአንዱ አሰልጣኝ ጋር እንደምኖርም ተነገረኝ" ብሏል።
የትዳር ጓደኛው ፅንሱን ያላቋረጠች ሲሆን ጥንዶቹ ከወራት በኋላ ታርቀዋል።
የመጀመሪያ ልጃቸውን ከወለዱ በኋላ እንደገና በድጋሚ ያረገዘችው ሚስት ተመሳሳይ መከራ እንዳያጋጥማቸው እርግዝናውን ማቋረጥ እንደሚገባት ተሰምቷት እንደነበር ለኤቢሲ ተናገራለች።
ሌላ ተጫዋችም ለኤቢሲ እንዳስታወቀው ሃውቶን ጓደኛው ማርገዟን ሲያውቅ ተመሳሳይ ምላሽ እንደሰጠው ተናግሯል።
በኋላም ከእርሷ ጋር ለመለያየት እና ግንኙነቱን ለማቋረጥ ተገደደ። እሷም በኋላ ላይ ፅንስ አቋረጠች።
ከሌላ ግዛት የመጣው ሦስተኛው ተጫዋች በበኩሉ ቤተሰቡ ከእሱ ጋር ለመኖር ወደ ሜልበርን እንዳይዛወር ለማድረግ ክለቡ መሞከሩን ተናግሯል።
ሦስቱም ጥንዶች ከክስተቶቹ በኋላ የነበራቸውን የአዕምሯዊ ጤንነት ውጣ ውረድን ተናግረዋል።
ውንጀላውን የሚገልጸው ዘገባ ከሁለት ሳምንት በፊት በሃውቶን እንደደረሰው ኤቢሲ ዘግቧል። ለአውስትራሊያ እግር ኳስ ሊግ (ኤኤፍኤል) ባለሥልጣናትም ተላልፏል።
ዛሬ ረቡዕ ዕለት መገናኛ ብዙኃን ጋር ቆይታ ያደረጉት የኤኤፍኤል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጊለን ማክላክላን የኤቢሲን ዘገባ "ፈታኝ እና የሚረብሽ" ብለውታል።
"ከዚህ በላይ ከባድ ውንጀላዎችን ማግኘት ከባድ ነው" ብለዋል።
በስም ጥር ጠበቃ የሚመራ ገለልተኛ ቡድን ጉዳዩን ለመመርመር እንደሚመደብም ጠቁመዋል።
ምርመራው በሚከናወንበት ወቅት አሰልጣኞች ከኃላፊነታቸው ይነሱ አይነሱ በሚለው ላይ ክለቦች ዛሬ ይወሰናሉ።
የሃውቶን ቃል አቀባይ ግኝቱ "አስጨናቂ ታሪካዊ ውንጀላዎችን" ቢያነሳም በክለቡ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ "ካለው ባህል አኳያ ደኅንነቱ የተጠበቀ" መሆኑንም አመልክቷል።
"ክለቡ በዚህ ሂደት ለተሳተፉት ሁሉ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል። ደኅንነታቸውም ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው" ሲል አክሏል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ የኤኤፍኤል ተጫዋቾች በስታዲየም ከሚገኙ ተመልካቾች የሚደርስባቸውን የዘረኝነት ጥቃት እና የክለብ ባለሥልጣናትን ደካማ ድጋፍ በማንሳት ቅሬታ አቅርበዋል።
ቀደምት የአገሬው ተወላጅ እና የኤኤፍኤል ኮከብ የነበረው አዳም ጉደስ እንደተናገረው በተቀናቃኝ ደጋፊዎች ለዓመታት ሲደርስበት የነበረው ግፍ "ልቡ ተሰበሮ" በ2015 ጫማውን እንዲሰቅል አስገድዶታል።
ሌላው መቀመጫውን ሜልበርን ያደረገው ኮሊንግዉድ የተባለው ክለብ ባለፈው ዓመት በተደረገ ግምገማ "ከዘረኝነት" ጋር በተያያዘ ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል።












