የትግራይ ኃይሎች የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ወታደሮች መጠነ ሰፊ ጥቃት ከፈቱብን አሉ

የትግራይ ኃይሎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የትግራይ ኃይሎች በኤርትራ ወታደሮች መጠነ ሰፊ ጥቃት እንደተከፈተባቸውና ከባድ ውጊያ ከኤርትራ ጋር በሚያዋስኗቸው አካባቢዎች መካሄዳቸውን ተናገሩ።

የትግራይ ክልል ከኤርትራ ጋር የሚዋሰኑባቸውን በርካታ አካባቢዎችን በመጥቀስ ጥቃት እንደተከፈተባቸው የተናገሩት የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ በተጨማሪም የኢትዮጵያ መከላከያ እና የአማራ ኃይሎችም ተሳትፈዋል ሲሉ ከስሰዋል።

ይህንን በተመለከተ ከኢትዮጵያም ሆነ ከኤርትራ መንግሥት የተሰጠ ምላሽ የለም።

የኢትዮጵያ ቆይታቸውን አጠናቅቀው ወደ አገራቸው የተመለሱት በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር፣ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ግን የኤርትራ ሠራዊት ሰሞኑን ድንበር አቋርጦ ወደ ትግራይ ክልል ስለመግባቱ አሜሪካ እንደምታውቅ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

ማይክ ሐመር "የኤርትራ ጦር ከድንበር ማዶ የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች ስንከታተል ቆይተናል" ካሉ በኋላ ይህንኑ የኤርትራ እንቅስቃሴ አገራቸው እንደምታወግዝ ተናግረዋል። 

ሮይተርስ የዜና ወኪል ያነጋገራቸው ሁለት የእርዳታ ድርጅት ሠራተኞች በድንበር አካባቢ ከባድ ውጊያ እንደተካሄደ አመልክተው፣ ነገር ግን የኤርትራ ወታደሮች ወደ ትግራይ ክልል ተሻግረው መግባታቸውን በተመለከተ ሊያረጋግጡ አልቻሉም።

የአሜሪካ መንግሥት እና የአውሮፓ ኅብረት የኤርትራ ሠራዊት ዳግም ወደ ተቀሰቀሰው ጦርነት ተመልሰው መግባታቸውን በመጥቀስ ተቃውሞ ማሰማታቸው ይታወቃል።

ባለፈው ነሐሴ ወር መልሶ የተቀሰቀሰው የሰሜን ኢትዮጵያ የጦርነት ተጨባጭ መረጃ ማግኘት አስቸጋሪ በሆነበት ሁኔታ ውስጥ እንደቀጠለ መሆኑን ከትግራይ እና ከአማራ ክልል የተለያዩ ቦታዎች የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የህወሓት መሪዎች በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ሠራዊቶች ጥቃት እየተፈጸመባቸው መሆኑን ሲገልጹ፣ ከሁለቱ አገራት ባለሥልጣናት በኩል ግን እስካሁን የተባለ ነገር የለም።

ጥቃቱም ከተከዘ አስከ ኢሮብ መከፈቱን የጠቀሱት አቶ ጌታቸው ረዳ በማይ ኩህሊ፣ በዝባን ገደና፣ በአዲአውአላ፣ በራማ፣ በጾሮና እና በዛላምበሳ አካባቢዎች ከባድ ውጊያ መደረጉን አመልክተዋል።

ይህንንም ተከትሎ የትግራይ ኃይሎች ወታደራዊ ዕዝ የተባለው አካል፣ ጦርነቱ የትግራይ ሕዝብን ኢላማ ያደረገ ነው በማለት፣ የክልሉ ሕዝብ የተከፈተበትብ ጥቃት ለመመከት “ለአጠቃላይ ጦርነት እንዲነሳ” ጥሪ የሚያቀርብ መግለጫ አውጥቷል።

ካገረሸ አራት ሳምንታት ያስቆጠረውን ጦርነት ለማስቆም እና ድርድር እንዲጀመር ለማበረታታት አዲስ አበባ ሰንብተው ወደ ዋሽንግተን የተመለሱት የአሜሪካ መንግሥት ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር፣ ኤርትራ ተመልሳ ወደ ግጭቱ መግባቷ አገራቸውን እንደሚያሳስባት ገልጸዋል።

ማይክ ሐመር ከአስር ቀናት በላይ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ጨምሮ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ከአፍሪካ ኅብረት እና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል።

ልዩ መልዕክተኛው ከአዲስ አበባ ወደ አሜሪካ ከተመለሱ በኋላ ማክሰኞ መስከረም 10/2015 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፣ በትግራይ ኃይሎች እና በፌደራሉ መንግሥት መካከል ያለውን ግጭት ለማስቆም ዋነኛ እንቅፋት የሆነው “በሁለቱም ወገኖች በኩል ያለው አለመተማመን ነው” ብለዋል።

ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበውን ጦርነት በድርድር ለማብቃት አሜሪካንን ጨምሮ የአፍሪካ ኅብረት ለወራት የዘለቀ የሽምግልና ጥረት ሲያደርጉ ቢቆዩም፣ ቢያንስ ውጊያው መልሶ እንዳይከሰት የሚያደርግ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ማስገኘት ሳይችሉ ቆይተዋል።

ኦሉሴንጉ ኦባሳንጆ የአፍሪካ ኅብረትን ወክለው በተደጋጋሚ ከአዲስ አበባ መቀለ ሲመላላሱ ቆይተው ድርድር የመጀመር ተስፋ እንዳለ ቢገልጹም ይህ ነው የሚባል ውጤት አልታየም።

በሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ አምባሳደር ማይክ ሐመርን ጨምሮ የአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አኔት ቬበር እንዲሁም ሌሎች ዲፕሎማቶች በመቀለ እና በአዲስ አበባ በነበራቸው ውይይት፣ ድርድር ከሚጀመርበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን የሚያመለክት ተስፋ ተፈጥሮ ነበር።

ነገር ግን ከዚህ በኋላ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለወራት ጦርነቱን ጋብ አድርጎት የነበረው የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ተኩስ አቁም ተጥሶ ጦርነት ተቀስቅሷል።

ሐመር ዋሽንግተን ላይ ትናንት አሁንም የድርድር ተስፋ እንዳለ አመልክተዋል። ሁለቱም ወገኖች የጦርነት አማራጭን ትተው በጠረጴዛ ዙሪያ ለመቀመጥ የሚያስችል “ደፋር ውሳኔ እንደሚወስኑ ተስፋ አለን” ብለዋል።

ጦርነቱ መልሶ ከተቀሰቀሰ በኋላ የኤርትራ ጦር ጥቃቶችን ሰንዝሮብናል ሲሉ በተደጋጋሚ ሲከሱ የነበሩት የትግራይ ኃይሎች፣ በቃል አቀባያቸው በአቶ ጌታቸው በኩል ማክሰኞ ዕለት እንዳሳወቁት አሁንም መጠነ ሰፊ ጥቃት የኤርትራ እና የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ከፍቶብናል ሲሉ ከስሰዋል።

ከሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት የትግራይ ኃይሎች በተለያዩ አካባቢዎች ጦርነት በመቀስቀስ እያስፋፉ መሆናቸውን በመግለጽ መክሰሱ ይታወሳል።

ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ለወራት ቆሞ የነበረ ሲሆን፣ ባለፈው ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም ዳግም መቀስቀሱ ይታወሳል።

ጦርነቱን እንደ አዲስ በመጀመር መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች እርስ በእርስ ይካሰሳሉ።

በተለያዩ ወገኖች ሲካሄድ የነበረው የሰላም ጥረት ውጤት ሳያመጣ የቆየ ቢሆንም፣ ጦርነቱ ዳግም ካገረሸ በኋላ አገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መንግሥት እና ህወሓት ተኩስ አቁመው ድርድር እንዲጀምሩ አጥብቀው እየጠየቁ ነው።