እናት፣ አባት እና ልጅን ጨምሮ አራት ሰዎች በትግራይ ክልል በደረሰ የመብረቅ አደጋ ሞቱ

በትግራይ ክልል በሰሜናዊ ምዕራብ ዞን በሚገኘው ዛና ወረዳ ከጣለ ከባድ ዝናብ ጋር በደረሰ የመብረቅ አደጋ ምክንያት አራት ሰዎች ሕይወታቸው እንዳለፈ ተገለጸ።
የዛና ወረዳ አስተዳዳሪ ሙላቴ ሐደጎ ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ በመብረቅ አደጋው ምክንያት ከሞቱት ሰዎች መካከል ሦስቱ የአንድ ቤተሰብ አባላት ናቸው።
በአደጋው "አባት፣ እናት እና ወንድ ልጃቸው ሞተዋል" ብለዋል። በተጨማሪም አንድ ሌላ ግለሰብ በመብረቅ አደጋው መሞታቸውንም አክለዋል።
ማክሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2018 ዓ. ም. ማምሻውን ከባድ ዝናብ በመጣሉ ምክንያት የመብረቅ አደጋው እንደተከሰተ አቶ ሙላቴ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ከ11 ሰዓት እስከ ምሽት 3 ሰዓት በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት በወረዳው በሚገኙ ሁለት ቀበሌዎች ማለትም በሃድነት ቀበሌ እና በማይለሚን ቀበሌ የመብረቅ አደጋው ደርሷል" ብለዋል።
የሞቱት ሰዎች ሦስት ወንድ እና አንዲት ሴት መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ሦስቱ የአንድ ቤተሰብ አባላት ይኖሩ የነበረው ሃድነት በተባለው ቀበሌ ውስጥ ሲሆን፣ አራተኛው አባወራ ደግሞ በማይለሚን ቀበሌ ይኖሩ ነበር።
እስከ ምሽት ሦስት ሰዓት ድረስ በከፍተኛ ሁኔታ የጣለው ዝናብ ለወረደው መብረቅ ምክንያት ሲሆን፣ በመብረቁ ተመትተው ሕይወታቸው ያለፈው ሰዎች ቤታቸው ሳሉ አደጋው እንደደረሰባቸው የወረዳው አስተዳዳሪ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የአደጋው ሰለባዎች የመብረቅ አደጋው ከደረሰ በኋላ ወዲያውኑ ሕይወታቸው እንዳለፈም አቶ ሙላቴ አክለው አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት በተለይም በሰሜን ምዕራብ የትግራይ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ከባድ ዝናብ ስለሚከሰት አርሶ አደሮች በፍጥነት ሰብላቸውን እንዲሰበስቡ የትግራይ ሜትሮሎጂ ተቋም እና የትግራይ ግብርና ቢሮ ማስጠንቀቂያ ሰጥተው እንደነበር ተገልጿል።
የዛና ወረዳ አስተዳዳሪም ይህንን ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብን በተመለከተ ቅድመ የማስጠንቀቂያ መረጃ ለኅብረተሰቡ ቀድመው ማድረሳቸውን፣ ነገር ግን "የመብረቅ አደጋ እንደሚመጣ ግን መረጃ አልነበረንም" ብለዋል።
የመብረቅ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል በትክክል ግምት መስጠት ባይቻልም፤ በዘመናዊ የሜትሮሎጂ ምርምር በመታገዝ የመብረቅ አደጋ ሊከሰት የሚችልበትን ዕድል እንዲሁም ጠቅለል ባለ ሁኔታ የትኛው አካባቢ ሊከሰት እንደሚችል ትንበያ ማስቀመጥ እንደሚቻል ጥናቶች ይጠቁማሉ።
ከአንድ ወር በፊትም በሃድነት ቀበሌ እና በኩምቶም ቀበሌ በተከሰተ የመብረቅ አደጋ ሳቢያ የ14 ዓመት ታዳጊ ሕይወት ማለፉን ያስታወሱት አቶ ሙላቴ "በሁለት ወር ውስጥ በወረዳው በአጠቃላይ ስድስት ሰዎች በመብረቅ አደጋ ሞተዋል" ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ የዝናብ ሁኔታ እየተስተዋለ መሆኑን ነዋሪዎች እየተናገሩ ነው።
ቀደም ባሉ ዓመታት በተለይ በክረምት ወቅት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ በደረሱ የመብረቅ አደጋዎች ምክንያት የሰዎች ሕይወት ማለፉ መዘገቡ ይታወሳል።















