በትግራይ 600 ሺህ ብር ለአጋቾች ከፍላ የልጇን መገደል በማኅበራዊ ሚዲያ የተረዳችው እናት

የፎቶው ባለመብት, Yordanos Gayim
በትግራይ ክልል በሽረ አቅራቢያ በምትገኘው እንዳባጉና ከተማ ከሰሞኑ የሰባት ዓመት ልጅ ታግቶ ተገድሎ መጣሉ የከተማዋን ነዋሪዎች እና የማህበራዊ ሚዲያዎች ተጠቃሚዎችን በከፍተኛ ሁኔታ አስደንግጧል።
ናዖድ ተክላይ ብርሃነ የተሰኘው የሰባት ዓመቱ ሕጻንን ያገቱት ግለሰቦች ለማስለቀቂያ ከእናቱ 600 ሺህ ብር ከተቀበሉ በኋላ ልጁን ገድለው ድልድይ ላይ የጣሉት ባለፈው ሳምንት ነው።
ሕጻኑ በግፍ ተገድሎ አስከሬኑ ተጥሎ በእረኞች መገኘቱንም የሁለት ልጆች እናት የሆነችው የ32 ዓመቷ ዮርዳኖስ ጋይም ለቢቢሲ ትግርኛ ተናገራለች።
የልጆቿን ሕይወት ለማቃናት በደቡብ ሱዳን ከጥቂት ዓመታት በፊት ነዋሪነቷን ያደረገችው ዮርዳኖስ፣ ሐምሌ 22/2017 ዓ.ም. ምሽት የደረሳት የስልክ ጥሪ አስደንጋጭ ነበር።
"ቤተሰቦቼ ምሽት 1፡30 ላይ ደውለው ልጅሽ ጠፍቷል አሉኝ። እኔ እንደመሰለኝ ቤታችን አካባቢ የጉድጓድ ውሃ ስላለ ክረምትም ስለሆነ ተንሸራቶ ገብቶ ይሆናል? ወይም እናቴ እንደታመመች ስላወቀ ወደ ሽረ ስትሄድ ተከትሏት ሄዶ ይሆናል? እንጂ ልጄ ይታገታል ብዬ ፈጽሞ አላሰብኩም" ብላለች።
ዮርዳኖስ የልጇን መጥፋት ከሰማችበት ከዚያች ምሽት ጀምሮ እስከ ንጋት ድረስ ልጇን መፈለግ ተያያዘች። የራሷ እና የሰባት ዓመት ልጇ ያለበትን ፎቶ በማያያዝ ያየው ሰው ካለ በሚል ለጓደኞቿ እና ቤተሰቦቿ "ይህንን ልጅ ያየ አይናችሁ ይብራ" በሚል መልዕክት በማኅበራዊ ሚዲያዎች አሠራጨች።
የልጅ ነገር የሆነባት እናት በዓይኗ እንቅልፍ አልዞር ሳይል በነገታው ጥዋት ሦስት ሰዓት ገደማ ከማታውቀው ቁጥር ስልክ ተደወለላት።
"በኢሞ 'ማይ ብላክ' የሚል ስም ያለው እና ቁጥሩ የማይታይ፣ የፕሮፋይል ፎቶው ሽጉጥ የሆነ ስልክ ተደወለልኝ። 'ዮርዳኖስ ነሽ?' ብሎ ጠየቀኝ። 'አዎ' ብዬ ነገርኩት። ልጄ ጠፍቷል ብለሽ ፌስቡክ ላይ የለጠፍሽው ልጅሽ አልጠፋም። በማይ ጸብሪ አካባቢ በሽፍቶች እጅ ነው ያለው። ገንዘብ ከከፈልሽ ይለቀቅልሻል" እንዳሏት ለቢቢሲ ተናግራለች።
ልጄ እኳንም ጉድጓድ ውስጥ አልገባ እንጂ "ገንዘብ ከሆነ የፈለጋችሁት መጠን እልክላችኋለሁ" ስትል እሷም መለሰች።
የልጇ አጋቾች ሁለት ሚሊዮን ብር እንድትከፍል ጠየቋት።

የፎቶው ባለመብት, Yordanos Gayim
የጠየቋትን ገንዘብ መጠን ያህል ለመክፈል አቅም እንደሌላት ነግራቸው፤ የልጇን አባት በጠየቀችውም ወቅት ገንዘቡ በጣም ብዙ ስለሆነ እንዲቀንሱት እንድትጠይቃቸው ነገራት።
ዮርዳኖስ ከልጇ አጋቾች ጋር ዳግም ባደረገችው ድርድር የገንዘቡ መጠን ወደ አንድ ሚሊዮን ሰባት መቶ ሺህ ብር አወረዱላት።
እነዚህ አጋቾች የልጇንም ቪዲዮ ላኩላት። በዚህም ቪዲዮ ላይ "ልጄ፤ 'እናቴ አንዲለቁኝ ገንዘቡን ላኪላቸው' ብሎ አንድ እግሩ ወደሚታይ ሰው ሄዶ ሲታቀፍ ይታያል" ስትል ዮርዳኖስ ታስረዳለች።
ከሁለት ቀናት በኋላ ሐሙስ፣ ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም. 600 ሺህ ብር ወደ አካውንታቸው ያስገባችው ዮርዳኖስ "እባካችሁ አደራ ልጄ እንዳይርበው ሙሉውን ገንዘብ እልክላችኋላሁ ብዬ [ከልጇ አጋቾች ጋር] ተለያየን" ትላለች።
አጋቾቹ ሙሉ ሌሊቱን 'ኦንላይን' ስላልነበሩ ዮርዳኖስ ስትጨነቅ አደረች።
በነገታው አርብ ጠዋት ላይ በኢንተርኔት በላኩላት መልዕክት "ብሩን አንድ ሚሊዮን እናድርግልሽ እና የቀረውን 400 ሺህ አስገቢ " ሲሉ ጠየቋት።
አጋቾቹ ልጇን በቢላ እያስፈራሩ " እናቴ እንዳይገድሉኝ ገንዘቡን ላኪላቸው" ብሎ የሚማጸንበትን ቪዲዮ በኢሞ ልከውላታል።
በአጭር ጊዜ "400 ሺህ ብሩን ካልላከሽ ልጅሽን በሕይወት አታገኚው" ሲሉም እንዳስፈራሯት ትናገራለች።
ይሁን እንጂ በኋላ እንደተረዳችው አጋቾቹ ልጇን ናኦድን አርብ ገድለውት የቀረውን ገንዘብ ለመውሰድ እየተደራደሩ እንደሆነ እና ልጇ በሕይወት ያለ ለማስመሰልም ቀድሞ የተቀዳ ድምጽ ይልኩላት እንደነበር ነው።
በዚህም ልጇን ለማስለቀቅ ላይ፣ ታች በማለት ገንዘቡን ለማግኘት በምትጥርበት ወቅት ቤተሰቦቿ ወደ አገር ቤት መምጣት አለብሽ አሏት።
የልጇ አስክሬን ከእንዳባጉና ወደ ሽረ እንዳሥላሴ በሚወስድ መንገድ ላይ በተለምዶ 'እንዳ ክሬቸራት' በሚባል ስፍራ መንገድ ላይ በሚገኝ ቱቦ ተጥሎ በእረኞች በመገኘቱ ነበር፤ እሷ ባታውቅም ቤተሰቦቿ ወደ አገርሽ ነይ የሚል መልዕክት የላኩላት።
የናዖድን ግድያ ያረጋገጡት የዮርዳኖስ ቤተሰቦች ቲኬቷን ቆርጣ ወደ አገር ቤት እንድትመጣ እና ምንም ዓይነት ገንዘብ እንዳትልክላቸው ማስጠንቀቃቸውን ትናገራለች ።
ነገር ግን ወደ አገሯ ለማቅናት እየተዘጋጀች እያለ የልጇን አስክሬን በድልድል ላይ ተጥሎ የሚያሳይ ፎቶ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አየች።
"የልጄን የአስክሬን ፎቶ ፌስቡክ ላይ የማጽናኛ መልዕክት ጋር ሲልኩልኝ ራሴን ስቼ ወደቅኩ። ከዚያም ሰዎች አንስተው ካረጋጉኝ በኋላ ወደ አገሬ ሸኙኝ" የምትለው እናት፤ ከኅሊናዋ መቼም ቢሆን የማይጠፋውን የልጇን የሞት ምሥል እንዴት እንዳየች ታስታውሳለች።
ዮርዳኖስ ሽረ ስትደርስ የልጇ አስክሬን ለምርመራ ከሄደበት መቀለ ወደ ሽረ መጣ "ወደ ሽረ ከልጄ አስክሬን ጋር ተቀዳድመን ነው የገባነው። በልጄ ቀብር ላይ ተገኘሁ" ስትል ልቧ በሐዘን የተሰበረው እናት ትናገራለች።

የፎቶው ባለመብት, Yordanos Gayim
ከናዖድ ተኽላይ ብርሃነ ግድያ ጋር በተያያዘ የእንዳባጉና ከተማ የፀጥታ ኃላፊ እስካሁን ከታዳጊው እገታ እና ግድያ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ ዘጠኝ ሰዎችን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በመቀጠልም በተደረገው ማጣራት በወንጀሉ የተሳተፉ ወደ ውጭ አገር እንደሸሹም ምርመራ ማሳየቱን ፤ እንዲሁም ይገኙበታል የተባለውን አገር እኚህ የፀጥታ ኃላፊ ለቢቢሲ ቢናገሩም ምርመራ እንዳያስተጓጎል የአገሩ ስም እንዳይጠቀስ በመጠየቃቸው ቢቢሲ ከመግለጽ ተቆጥቧል።
ተጠርጣሪዎቹ በዓለም አቀፉ የወንጀል አዳኝ ተቋም ኢንተርፖል እገዛ በቁጥጥር ስር የሚውሉበትን መንገድ እየፈለጉ መሆናቸውንም የፀጥታ ኃላፊው ለቢቢሲ አስረድተዋል።
ተጠርጣሪዎቹ እስካሁን ፍርድ ቤት አንድ ጊዜ የቀረቡ ሲሆን፣ ዛሬ አርብ፣ ነሐሴ 9/2017 ዓ.ም ቀጠሮ ተይዞላቸዋል።
በእንዳባጉና ከተማ ሕጻን ታግቶ ገንዘብ ሲጠየቅበት ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን የተናገሩት እኚህ የፀጥታ ኃላፊ ሆኖም በመላው ትግራይ ተመሳሳይ ወንጀል እየተበራከተ መሆኑን ገልጸዋል።
"ለሕብረተሰቡ ምስጋና ይግባውና ትንሽ ተጽናንቻለሁ ነገር ግን መንግሥት ባለበት አገር ሕጻናት እንደዚህ በጭካኔ ታግተው ሲገደሉ ማየት ያሳዝናል" ስትል የናኦድ እናት የተሰማትን ጥልቅ ሐዘን ገልጻለች።
የእንዳባጉና ነዋሪዎች እንደ ናዖድ ያሉ ህጻናት ወደ ሱቅ እንኳን ሲላኩ እንደሱ ያጋጥማቸው ይሆን እንዴ? በሚል ፍርሃትና ሰቀቀን ውስጥ መሆናቸውን የምትናገረው እናት የፍትሕ ሥርዓቱ ልጇን አፍነው በገደሉ ወንጀለኞች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንዲወስድ ተማጽናለች።















