በትግራይ ክልል 11 ሰዎች በኮሌራ ሳቢያ እንደሞቱና 425 ሰዎች በወረርሽኙ እንደተያዙ ተገለጸ

ጉሉኮስ የተሰካለት እጅ

በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የኮሌራ ወረርሽኝ እንደተቀሰቀሰና 11 ሰዎች ሕይወታቸው እንዳለፈ ተገለጸ።

የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ የኅብረተሰብ ጤና የድንገተኛ ክፍል አስተባባሪ አቶ መብራሕቶም ሐፍተ ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ ከሐምሌ 19/2017 ዓ. ም. አንስቶ በክልሉ የኮሌራ ወረርሽኝ ታይቷል።

የአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ዞን አዋሳኝ በሆኑ አካባቢዎች ሰለዋ እና ሳምረ በተባሉ ወረዳዎች ወረርሽኙ እንደጀመረ ተናግረዋል።

"በዋግ ኽምራ በሽታው እንዳለ ሰምተን ነበር። ከዋግ ኽምራ አበርገለ ወረዳ ጋር የሳምረ እና ሰለዋ ወረዳዎች መረጃ እየተለዋወጡ ነበር። ከዚያ በኋላ እኛ ጋር በኮሌራ የተጠረጠሩ ሰዎች ስናይ ናሙና እየወሰድንና ሕክምናውን እያደረግን ቆየን" ሲሉ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

በትግራይ ክልል ደቡብ ምሥራቅ ዞን የሚገኘው ሳምረ ወረዳና በደቡብ ዞን የሚገኘው ሰለዋ ወረዳ ወረርሽኙ በታየ በ22 ቀናት ውስጥ በሰሜን ምዕራብ ዞን ሰየምቲ አዲ አቦ አካባቢ ወረርሽኙ መከሰቱን አክለዋል።

"እስከ አሁን ባለው መረጃ ወደ 425 ሰዎች ታመዋል።11 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል" ሲሉም ተናግረዋል።

አቶ መብራሕቶም፣ ከትግራይ ክልል ለእርሻ ሥራ ወደ ዋግ ኽምራ ሄደው የነበሩ ሰዎች በበሽታው መያዛቸው መሰማቱን ገልጸዋል።

በዋነኛነት ለበሽታው መስፋፋት ምክንያት ብለው አቶ መብራሕቶም ያስቀመጡት የሰዎችን ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀስን ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"ለቀብርም ለገበያም ወደ ዋግ ኽምራ የሄዱ ሰዎች ነበሩ። ከትግራይ ታመው ወደ ዋግ ኽምራ የሄዱም ሰዎች አሉ። እነሱ እዛ ታክመዋል። እኛም ከዋግ ኽምራ የመጡትን አክመናል። የሕዝቡ እንቅስቃሴ ስላለ በሽታው ሊሰራጭ ችሏል" በማለት አብራርተዋል።

በሳምረ ወረዳ በባህላዊ መንገድ ወርቅ የሚያወጡ ሰዎች ባሉበትም በሽታው እንደታየ አክለዋል።

"ወርቅ የሚያወጡት ሰዎች አንድ ቦታ ይሄን ያህል ወርቅ ቦታ የሚል መረጃ ሲሰማ ይንቀሳቀሳሉ። ወደ 500 ግራም በሰሜን ምዕራብ ዞን ተሰማ የሚል ነገር ሲሰማ ወደዚያ ሄደዋል። በእንቅስቃሴ ምክንያት በሽታው ሊስፋፋ ችሏል።"

የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ወረርሽኙን ለመከላከል ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ እየሠራ እንደሆነና ምላሽ ሰጪ ቡድን ወደ ክልሉ እንደተላከ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

"እስካሁን ባለው ሁኔታ እጥረት የለብንም። የውሃ ማከሚያ ግብዓቶች እጥረት ነበረ። እሱም ተፈቷል። ሌላም የሚያስፈልገንን እየገለጽን እያገኘን ነው" ብለዋል።

"ሕይወትን እስከማሳጣት የሚደርሰው ኮሌራ የሚከሰተው በንጽህና ጉድለት ነው። ኅብረተሰቡ ካላገዘን በሽታውን መቆጣጠር አንችልም። ማኅበረሰቡ ወረርሽኙን ለመከላከል ከየት አካባቢ ወደ የት አካባቢ ሄደ የሚለውን መከታተል አለበት" ሲሉ መክረዋል።

መፀዳጃ ቤትን በንጽህና ይዞ መጠቀምና ንጹህ የመጠጥ ውሃ መጠጣት አልያም ውሃን አክሞ መጠጣት ወረርሽኙን ለመከላከል እንደሚረዳ አቶ መብራሕቶም አክለዋል።

"የቧንቧ ውሃ መጠጣት ወይም ውሃ አክሞ መጠጣት ያስፈልጋል። ውሃ ማከሚያ ካልተገኘ አፍልቶ መጠጣት ይቻላል። ምግብ አብስሎ መብላትም ያስፈልጋል" ብለዋል።

አክለውም" ፍራፍሬ በትኩሱ በደንቦ አጥቦ መብላት ያስፈልጋል። በበሽታው በሰዓታት ስለሚገድል በበሽታው የተያዘ ሰው በቶሎ ወደ ሕክምና መሄድ አለበት። ወደ ሕክምና እስከሚሄዱ ኦአርኤስ በአንድ ሊትር ውሃ በጥብጦ የወጣውን ፈሳሽ መተካት አለበት" በማለትም ምክራቸውን ለግሰዋል።

በኮሌራ ወረርሽኝ የሞቱ ሰዎች አስከሬን መነካት እንደሌለበትና ክስተቱ ለባለሙያዎች ጥቆማ መስጠት እንደሚያሻ ገልጸዋል።

"በበሽታው የሞተ ሰው ቀብር አለመሳተፍ ወይም በቀብሩ ላይ አለመብላትና አለመነካካት በሽታውን ለመከላከል ያግዛል" ብለዋል።