በጋምቤላ ክልል ግጭት ለምን ይደጋገማል?

የፎቶው ባለመብት, gambella tourism
በጋምቤላ ክልል ግጭት በድጋሚ ከተቀሰቀሰ ሦስት ሳምንታት አለፉ። ሆኖሞ የክልሉም ሆነ የፌደራሉ መንግሥት ስለ ግጭቱ ምክንያት፣ ስለ ግጭቱ ስፋት፣ ስለ ግጭቱ ተዋናዮች እና ስለደረሠው ጉዳት ዝርዝር ማብራሪያ አልሠጡም።
የክልሉ መንግሥት ከአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 7/2025 ጀምሮ ግጭቱ በተከሠተባቸው በጋምቤላ ከተማ፣ በጋምቤላ ወረዳ እና በኢታንግ ልዩ ወረዳ ላልተወሰነ ጊዜ ሰዓት እላፊ አውጇል።
ካለፉት ጥቂት ቀናት ወዲህ ግን የፌደራሉ መንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር እያዋሉ እንደሆነ እና ክልሉ ወደመረጋጋት እየተመለሠ እንደሚገኝ ተገልጧል።
የታጠቁ አካላት የፈጸሙት ጥቃት እና ግጭቱ በዋናነት በአኝዋ እና ኑዌር ጎሳዎች መካከል የተከሠተ ነው።
የሰብዓዊ መብት ተማጋቹ ያሬድ ኃይለማርያም፣ መንግሥት ጋምቤላ ላይ ለሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶች በቂ ትኩረት አይሠጥም ሲሉ ለቢቢሲ በሠጡት ቃል ይወቅሳሉ።
በሰሞኑግጭት፣ በተለይ ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ድምጽ ባያሠሙ ኖሮ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሁንባለበት ሁኔታ ፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ ጥሪ ማደረጉን እንደሚጠራጠሩ ያሬድ ገልጸዋል።
የግጭት ምክንያቶች
በጋምቤላ ነባር የሚባሉት ብሔረሰቦች ኑዌር፣ አኝዋ፣ መዠንገር፣ ኦፖ እና ኮሞ ናቸው። በአውሮፓውያኑ 2007ቱ የሕዝብ ቆጠራ የኑዌሮች ብዛት 47 በመቶ ሲደርስ፣ የአዋዎች ብዛት ወደ 22 በመቶ አሽቆልቁሏል። በቀደሙት ዓመታት ግን አኝዋዎች አብላጫ ቁጥር ነበራቸው።
የኑዌሮች ቁጥር ብልጫ የያዘው በደቡብ ሱዳን የነጻነት ትግል ወቅት የኑዌር ጎሳ ተወላጅ ደቡብ ሱዳናዊያን በብዛት ወደ ጋምቤላ ተሰደው የኢትዮጵያ ዜግነት በመውሰዳቸው እንደሆነ ይታወቃል።
በክልሉ ለሚከሠቱ ግጭቶች መነሻዎች ከፖለቲካ ሥልጣን እና ውክልና፣ ከአስተዳደራዊ መዋቅሮች ብዛት እና ድንበር፣ ከበጀት ድልድል፣ ከሃብት ክፍፍል፣ ከሕዝብ ብዛት እና ከተቃራኒ የአኗኗር ዘይቤ ጋር የተያያዙ ናቸው።
ለአብነትም፣ ተደጋጋሚ ግጭት የምታስተናግደው እና አኝዋዎችም ኑዌሮችም በብዛት የሚኖሩባት ኢታንግ ወረዳ ቀደም ሲል በአኝዋ ዞን ስር ነበረች። ሆኖም በአኝዋዎች እና ኑዌሮችመካከል እየተባባሰ የሄደውን ግጭት ለማብረድ ሲባል፣ ኢታንግ ከአውሮፓውያኑ 2003 ጀምሮ ወደ ልዩ ወረዳ መዋቅር አድጋ ተጠሪነቷ ለክልሉ መንግሥት ሆኗል። ያም ሆኖ ኢታንግ እስከ ዛሬም የደም አፋሳሽ ግጭት ቀጠና ከመሆን አላመለጠችም።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ያሬድም፣ በክልሉ የመንግሥት መዋቅር የቱ ብሔረሰብ ምን ሥልጣን ያዘ? የሚለው አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን አጽንዖት ይሰጡታል።
በብሔር-ተኮሩ ፌደራላዊ ሥርዓት ቀመር መሠረት፣ ለኑዌሮች የተከለሉ ወረዳዎች እና የካቢኔ ሥልጣኖች ከብሔረሰቡ ቁጥር ጋር አብረው ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመራቸው በአኝዋዎች ዘንድ ቅሬታ እና ስጋት መፍጠሩ ግልጽ ነው።
የእንስሳት አርቢዎቹን ኑዌሮች የግዛት ማስፋፋት የአኗኗር ዘይቤ፣ በተወሠነ መሬት ላይ የሚኖሩት በግብርና የሚተዳደሩት አኝዋዎች የኅልውና ስጋት አድርገው ነው የሚያዩት። ይህም ተጨባጭ ስጋት እንደሆነ አካባቢውን ያጠኑ አጥኚዎች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው።
ከዚህ አንጻር የሁለቱ ብሔረሰቦች የቆየ ውጥረት እና ግጭት መንግሥት የደቡብ ሱዳን ስደተኞችን ከክልሉ ማኅበረሰብ ጋር በዘላቂነት ለመቀላቀል እየተገበረ ባለው የ"ማካተት" ፖሊሲ ላይ አንድምታ ይኖረዋል ወይ? ስንል ያሬድን ጠይቀናቸው ነበር።
ያሬድ "በክልሉ ለዘመናት የሠፈኑ ውጥረቶች ሳይበርዱ፣ የባላንጣ ብሔረሰቦች የፖለቲካ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ምላሸ ሳያገኙ፣ ፖሊሲውን መተግበር አደጋ አለው" ባይ ናቸው።
"ፖሊሲው የአንዱን ብሔረሰብ ቁጥር በመጨመር፣ የፖለቲካ ሥልጣን፣ የመሬት ባለቤትነት እና ኢኮኖሚ ችግሮችን ያባብሳል" የሚል ስጋት እንዳላቸው ያሬድ ጠቁመዋል።
በተለይ በደቡብ ሱዳን መንግሥት እና በተቃዋሚው የቀድሞ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር ኃይሎች መካከል በአውሮፓውያኑ 2013 ግጭት ካገረሸ ወዲህ፣ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ኑዌር ስደተኞች ወደ ጋምቤላ ገብተዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ400 ሺህ በላይ ስደተኞች አኝዋ ዞን ውስጥ በሰባት መጠለያ ጣቢያዎች እንደሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል።
ይህም በስደተኞቹ እና በተቀባይ ማኅበረሰቦች መካከል ግጭቶች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሲሆን፣ ታይቷል። በግጭት ጊዜ፣ የጋምቤላ ኑዌሮችም ስደተኞቹን በማገዝ በአኝዋዎች ላይ ጥቃት የፈጸሙባቸው ክስተቶች እንዳሉ አጥኚዎች ይገልጣሉ።
ኢሰመኮም በ2016 ዓ.ም. ባወጣው የጋምቤላ ክልል የሰብዓዊመብት ሪፖርቱ፣ የስደተኛ ተቀባይ ማኅበረሰቦች በስደተኞች ላይ የሚያነሷቸው ቅሬታዎች የግጭት ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሷል።
ባለፈው ዓመት ከደቡብ ሱዳን ጦር የአጸፋ ጥተት የሸሹ የኑዌሩ አማጺ ቡድን "ነጩ ሠራዊት" አባላት ከነትጥቃቸው ጋምቤላ መግባታቸው በወቅቱ ተዘግቧል።
ከደቡበ ሱዳኑ ግጭት ጋር በተያያዘ፣ የጦር መሳሪያ በብዛት ወደ ጋምቤላ እንደሚገባ እና የደቡብ ሱዳን "ነጩ ሠራዊት" ታጣቂዎችም የጋምቤላ ኑዌሮች ከአኝዋዎች ጋር በሚጋጩበት ጊዜ ኑዌሮችን ለማገዝ ወደ ጋምቤላ እንደሚገቡ እና በጥምር ጥቃት እንደሚፈጽሙ ሪፍት ቫሊ ኢንስቲትዩት በግጭቱ ዙሪያ ያደረገው ጥናት ያመለክታል።
የደቡብ ሱዳን ኑዌር ስደተኞች እና ታጣቂዎች በብዛት ወደ ጋምቤላ መግባት፣ አኝዋዎች ከቀድሞዎቹ ደርግ እና ኢሕአዴግ ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግሥታት ከለላ እየነፈጓቸው እንደሄዱ እና ለኑዌሮች እንደወገኑ አድርገው እንዲያስቡ አድርጓቸዋል ሲሉ ፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሠ በአንድ ጥናታቸው ላይ ይገልጣሉ።
አንድ የአንዱ ብሔረሰብ ተወላጅ በግል ጠብ የሌላኛውን ብሔረሰብ ተወላጅ ነፍስ ካጠፋ፣ የሟች ብሔረሰብ ግድያው በብሔረሰቡ ላይ እንዳነጣጠረ በመቆጠር ወዲያው ለበቀል እንደሚነሳሳ በተደጋጋሚ የታየ ክስተት ነው።
የብሔረሰቦቹ ልሂቃንም ለግል እና ለቡድናዊ ፓለቲካዊ ግባቸው እናጥቅማቸው ሲሉ፣ ወጣቶችን አደራጅተው ለግጭትእንደሚያንቀሳቅሱ ተደጋግሞ ተነግሯል። በብሔረሰቦቹ ባህል፣ ከባላንጣ ወገን የሚገደሉ ሰዎችን ብዛት፣ የኃይል ሚዛን ማረጋገጫ አድርጎ የማየት ሁኔታ አለ።

የግጭት ታሪካዊ ዳራ
በክልሉ በተደጋጋሚ የሚከሰተው ግጭት፣ የአኝዋ እና ኑዌር ብሔረሰቦች ግጭት ነው። ከተለያዩ ክልሎች የሄዱ በተለምዶ "ደገኞች" ተብለው በሚጠሩ ነዋሪዎች እና በነባር ሕዝቦች፤ በደቡብ ሱዳን ስደተኞች እና በተቀባይ ማኅበረሰቦች እንዲሁም በታጣቂ ቡድኖች እና በመንግሥት ፀጥታ ኃይሎችመካከልም ግጭቶች ይፈጠራሉ።
የጋምቤላ ታጣቂ ወይም አማጺ ቡድኖች እና የደቡብ ሱዳንሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎችም፣ ድንበር ተሻግረው በሲቪሎች ላይ ጥቃቶችን ይፈጽማሉ። በክልሉ የግጭት ተዋናዮች ብዛት እና የግጭቱ ባህሪ ውስብስብ ነው።
በክልሉ ባለፉት ዓመታት የተከሠቱ ዋና ዋና ግጭቶች እና ጥቃቶች አሉ።
በተለይ በ"ደገኞች" እና በነባር ሕዝቦች መካከል የበርካቶችን ሕይወት በመቅጠፍ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው፣ በአውሮፓውኑ 2003 የተከሠተው ግጭት ነው። በዚህ ግጭት በርካታ የአኝዋ ብሔረሰብ አባላት እና "ደገኞች" ተገድለዋል።
ከግንቦት ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሐምሌ 2015 እንዲሁም ከመስከረም 2016 ዓ.ም. እስከ ጥር 2016 ዓ.ም. በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የክልሉን መደበኛ ፖሊስ እና የቀድሞውን ልዩ ኃይል የደንብ ልብስ የለበሱ "ማንነታቸውያለታወቁ" ታጣቂዎች በርካታ ጥቃቶችን መፈጸማቸውን ኢሰመኮ በወቅቱ ባወጣው ሪፖርት ገልጧል።
በዚሁ ግጭት እና ጥቃት፣ በኢታንግ ልዩ ወረዳ፣ በጋምቤላ እና በጎግ ወረዳዎች እንዲሁም በጋምቤላ ከተማ ስደተኞችን ጨምሮ የተገደሉት ሰዎች ብዛት 138 ሰዎች እንደነበር ተቋሙ በወቅቱ አስታውቆነበር።
ኢሰመኮ የታጠቁ ቡደኖች አደረጃጀት እና ጥቃቶቹ "የብሔረሰብ እዝማሚያ" ታይቶባቸዋል በማለት ጭምር ግጭቱ ምን ባህሪ እንዳለው መግለጡ የሚታወስ ነው።
ከደቡብ ሱዳኑ ጆንገሌ ግዛት የሚነሱ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ሌላኛው የጋምቤላ ፈተና ሆነው ነው የዘለቁት። በአውሮፓውያኑ ሚያዝያ 2016 የሙርሌ ታጣቂዎች በተለይ ከኑዌር ቀበሌዎች ከ200 በላይ ሴቶች እና ሕጻናትን አፍነው መውሰዳቸው አስደንጋጭ ክስተት ሆኖ ነበር።
የሙርሌ ታጣቂዎች ድንበር አልፈው ተደጋጋሚ ጥቃት የሚፈጽሙት ዘመናዊ መሳሪያ ታጥቀው እና በተቀናጀ ሁኔታ መሆኑ ደግሞ፣ እስካሁንም የጥቃቱን ትክክለኛ ዓላማ እንቆቅልሽ እንዳደረገው ይገኛል።
በሁለቱ አገራት ድንበር ርዝመት እና በክልሉ ፀጥታ ኃይል አቅም ውስንነት ሳቢያ፣ የደቡብ ሱዳን አማጺያንም ሆኑ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በቀላሉ ወደ ክልሉ እንዲገቡ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, gambela comm.
ከጠ/ሚ ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ
በአውሮፓውያኑ 2018 ኢትዮጵያ ውስጥ የተካሄደውን የመንግሥትለውጥ ተከትሎም፣ በጋምቤላ ግጭቶች አልቆሙም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሥልጣን ከያዙ በኋላ፣ በክልሉ በቶሎ የሥልጣን ሽግሽግ ባለመካሄዱ ወጣቶች የአደባባይ ተቃውሞ ያደርጉነበር።
ሆኖም ተቃውሞውን ተከትሎ ግጭት በመከሰቱ የመጀመሪያው የኑዌር ብሔረሰብ ተወላጅ የሆኑት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጋትሏክ ቱት ከስምንት ወራት በኋላ ከሥልጣን ሊነሱ ችለዋል።
ጋትሏክን የተኳቸው፣ የአኝዋ ተወላጁ ኡሞድ ኦጁሉ ነበሩ። የኡሞድ ሹመት ግን፣ ሥልጣን ተነጠቅን ላሉት የኑዌር ፖለቲከኞች ስጋት ፈጥሮባቸው እንደነበር 'ሪፍት ቫሊኢንስቲትዩት' የተሠኘው የምርምር ተቋም ባለፈው ዓመት ያደረገው አንድ ጥናት ይጠቁማል።
በአውሮፓውያኑ የካቲት 2020ም፣ ባንድ የኑዌር ተወላጅ ባለሥልጣን ግድያ ሳቢያ ግጭት ተቀስቅሶ በርካቶች ተገድለዋል፤ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
ከዚያም "የጋምቤላ ነጻነት ግንባር" የተባለ አማጺ ተመሥርቶ፣ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በሲቪሎች ላይ ለተፈጸሙ ጥቃቶች መንግሥት ተጠያቂ አድርጎት እንደነበር ይታወሳል።
ቡድኑ ስሙ ጎልቶ የወጣው ግን በ2022 ከአማጺው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር ጋምቤላ ከተማ ላይ የጣምራ ጥቃት የፈጸሙ ጊዜ ነበር። ይህ ጥቃት፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በጋምቤላ ግጭት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጥታ የተሳተፈበት ሲሆን፣ የጣምራ ጥቃቱ ዓላማ በትክክል ምን እንደነበር ግን እስካሁንም ግልጽ አልሆነም።
ኢሰመኮ በወቅቱ ባወጣው ሪፖርት፣ የቡድኖቹን ጥቃት ተከትሎ የክልሉ ፀጥታ ኃይሎች ከአማጺያን ጋር ተባብረዋል ያሏቸውን 50 ሲቪሎች በጅምላ ገድለዋል ሲል ወንጅሏል።
የፌደራል ፀጥታ ኃይሎችም፣ በግጭቱ እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩትን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አመራሮች እና ሌሎች የፀጥታ አባላት በቁጥጥር ስር አውለው ነበር።
በሚያዚያ 2023 በፌደራል መንግሥቱ ትዕዛዝ የጋምቤላን ጨምሮ የክልል ልዩ ኃይሎች ከፈረሱ በኋላ ባንድ ወር ውስጥ በኢታንግ፣ በጎግ እና በጋምቤላ ወረዳዎች በተከሰቱ ግጭቶች በርካቶች ተገድለዋል።
የበላይ አመራሩም በብቃት ማነስ ተገምግሞ ከሥልጣን ሲወርድ፣ የአሁኗ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ በነሐሴ 2024 ወደ ሥልጣን ሊመጡ ችለዋል።
የዓለሚቱ መስተዳድርም ላንድ ዓመት ከደም አፋሳሽ ግጭት አላመለጠም። የአሁኖቹ ግጭቶች እና ጥቃቶቹ ስፋት ገና በዝርዝር ባይታወቅም፣ የመንግሥት ሠራተኞች ከሦስት ሳምታት በላይ ከሥራ ውጪ መሆናቸው ግን ብዙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሠቶችተፈጽመው ሊሆን እንደሚችል ያሳያል የሚል እምነትእንዳላቸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ያሬድ ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት የኢሕአዴግ አጋር የነበረው የክልሉ ገዥ ፓርቲ የጋምቤላ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ፈርሶ፣ አመራሮቹ በውህዱ ብልጽግና ፓርቲ የውሳኔ ሠጪ መዋቅሮች ውስጥ በቀጥታ ተሳታፊ ሆነዋል። ሆኖም በከፊል ከፖለቲካ ሥልጣን እና ከሃብት ቅርምት ጋር የተያዙት ግጭቶች ተባብሰውእንደቀጠሉ ነው የሚገኙት።
የመንግሥት ምላሽ እና መፍትሄዎች
መንግሥት ለጋምቤላ ግጭቶች በተደጋጋሚ የሚሠጣቸውምላሾች ተመሳሳይ እና የግጭቱን ስረ መሠረት የሚፈቱ አይደሉም የሚል ትችት ይቀርብባቸዋል።
ግጭት በተቀሰቀሰ ማግስት መንግሥት ከሚወስዳቸው እርምጃዎች መካከል፣ መከላከያ ሠራዊትን ማሠማራት፣ ሰዓት እላፊ ማወጅ፣ አንዳንድ የክልል ባለሥልጣናትን እና የፀጥታ ኃላፊዎችን ከሥልጣንማንሳት ወይም ማሰር እና መንግሥት-መራሽ የማኅበረሰብ ውይይቶች ማካሄድ ተጠቃሽ ናቸው።
መደበኛ የመንግሥት ተቋማት፣ የብሔረሰብ ቅሬታዎች እና ውጥረቶች ወደ ብሔረሰብ ግጭት ከመሸጋገራቸው በፊት የግጭት መከላከያ ሁነኛ መፍትሄ ሲያስቀምጡ አይታዩም።
ያሬድም፣ መንግሥት የግጭቶችን የጉዳት መጠን በአብዛኛው እንደማይገልጥ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሠቶች ምርመራ እንደማያደርግ እና አጥፊዎችም ሲቀጡ እንደማይታይ ይጠቅሳሉ። በዚህም ምክንያት፣ ግጭቱ በተደጋጋሚ ሲያገረሽ ይታያል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የተሳተፈበት ጥቃት የተፈጸም ጊዜ፣ በግጭቱ ዙሪያ ከጋምቤላ ወደ አዲስ አበባ ሪፖርት የላኩ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) እና የኢሰመኮ ባለሙያዎች በክልሉ መንግሥት ዛቻ ከክልሉ ለመውጣት መገደዳቸውን ያሬድ ያስታውሳሉ።
ያሬድ፣ የዚህ ምክንያቱ በክልሉ መንግሥት በኩል በግጭቱ ዙሪያ መረጃ እንዲሰበሰብ እና እንዲጣራ ካለመፈለግ ሊሆን ይችላል ባይ ናቸው። ጋምቤላ የግጭት ምርመራ ለሚያደርጉ ጋዜጠኞችም "አደገኛ" ቦታ እየሆነች መሄዷን ጭምር ያሬድ ገልጸዋል።
ያሬድ በክልሉ ለሚከሠቱት ግጭቶች፣ ግጭት የሚደጋገምበትን ምክንያት በጥልቀት ማጥናት፣ የድንበር ጥበቃ ማድረግ እና ከታጠቁ ኃይሎች ጋር በሰላም መደራደር ወይም በኃይል ትጥቅ ማስፈታት ከፊል መፍትሄ ሊኾኑ እንደሚችሉ ይጠቁማሉ።
መንግሥት ችግሩን ለማጥናት እና ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ቁርጠኝነት አለው ወይ? የሚለው ግን ወሳኝ ጉዳይ መሆኑንየሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ገልጸዋል።
ጋምቤላ ለኢትዮጰያ ብቻ ሳይሆን፣ ለደቡበ ሱዳን ልማትም ጉልህ አስተዋጸዖ አላት። ሁለቱ አገራት በጋምቤላ በኩል በመንገድ ለመተሳሰር የ738 ሚሊዮን ዶላር ሰምምነት ተፈራርመዋል። ደቡብ ሱዳን በዚህ መንገድ በኩል ወደ ጅቡቲ ሸቀጦችን የማስወጣት እና የማስገባት ዕቅድ አላት።
ይህ የመንገድ ፕሮጀክት ሊሳካ የሚችለው ግን ጋምቤላ ሰላም ስትሆን ብቻ ነው። የጋምቤላ ሰላም ደሞ ከውስጣዊ የኑዌር እና አኝዋ ግጭቶች ባልተናነሰ፣ ከደቡብ ሱዳን ውስጣዊ ግጭት እና የእርስ በርስ ጦርነት ጋር በቀጥታም ይኹን በተዘዋዋሪ የተቆራኘ ነው።















