በእስራኤል ለሰባት ወራት የታሰሩት የጋዛ አልሺፋ ሆስፒታል ኃላፊ ተለቀቁ

የጋዛ አልሺፋ ሆስፒታል ኃላፊ ዶ/ር መሀመድ አቡ ሳልሚያ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በእስራኤል መንግሥት ከሰባት ወራት በላይ የታሰሩት የጋዛ አልሺፋ ሆስፒታል ኃላፊ ዶ/ር መሀመድ አቡ ሳልሚያ ተለቀቁ።

ኃላፊው በእስራኤል እስር ቤቶች ውስጥ የሚኙ ፍልስጤማውያን እስረኞች ከምንጊዜውም በላይ በከፋ ሁኔታ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

ኃላፊው በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት የአልሺፋ ሆስፒታል ለሐማስ ወታደራዊ ማዘዣ እና የቁጥጥር ማዕከል ሆኖ ሲያገለግል እንደነበር የሚያሳይ ማስረጃ አለ ሲል የእስራኤል ጦር ከሷል። የሆስፒታል አስተዳደርም ሆነ ሐማስ ይህንን አይቀበሉትም። በርካታ የእስራኤል ሚኒስትሮች እና ፖለቲከኞች የኃላፊውን ከእስር መፈታታት አውግዘዋል።

ዶክተሩ በእስራኤል እስር ቤት በደረሰባቸው እንግልት እና ስቃት አንዳንድ የሕክምና ባልደረቦቻቸው ህይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል።

በአልሺፋ ሆስፒታል የአጥንት ህክምና ኃላፊ የነበሩት ዶ/ር አድናን አል ቡርሽ በሚያዝያ ወር በእስር ላይ መሞታቸው ተዘግቧል።

ፍልስጤም እስረኞችን በተግባር እና በቃላት ማዋረድ እንዲሁም ምግብ እና ውሃ እየተከለከሉ ስለመሆናቸው ገልጸዋል።

“አስከፊ የሆነ እንግልት እና ስቃይ ደርሶብናል። ትንሿም ጣቴ ተሰበረች። በተደጋጋሚ ጭንቅላቴ ላይ ተደበደብኩ በርካታ ጊዜም ደም ፈሶኛል” ብለዋል።

አክለውም “ በእስራኤል እስር ቤቶች በየቀኑ ማሰቃየት ይደርስብናል። በየእስረኞች ክፍል እየገቡ ድብደባ ይፈጸምባቸዋል” ሲሉም የደረሰባቸውን ተናግረዋል። የህክምና ባለሙያው ብቻ ሳይሆኑ በእስራኤል እስር ቤቶች የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ተመሳሳይ እንግልት እና ስቃይ እንደደረሰባቸው ገልጸዋል።

የእስራኤል ማረሚያ ቤት አገልግሎት ዶ/ር አቡ ሳልሚያ ያቀረቡት ክሶች እንደማያውቅ ገልጾ ነገር ግን ሁሉም እስረኞች በህግ አግባብ መሰረት እንደሚያዙ እና እስረኞችም ቅሬታ የማቅረብ መብት እንዳላቸው ገልጿል።

እስራኤል ከመስከረም መጨረሻ በኋላ በጋዛ እየፈጸመችው ባለው የማያባራ ጥቃት የተገደሉ የህክምና ባለሙያዎችን ቁጥር 496 እንዳደረሰው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም አስታውቆ ነበር።

በተጨማሪም 1 ሺህ 500 የህክምና ባለሙያዎች መቁሰላቸውን እና 309 ደግሞ በእስር ላይ እንዳሉ በሐማስ አስተዳደር ስር ያለው የጤና ሚኒስቴሩ አክሏል።

የህክምና ተቋማት በአለም አቀፍ ህግ የተጠበቁ ቢሆኑም እስራኤል በሆስፒታሎች ላይ በርካታ ወረራዎች እና ጥቃቶች ትፈጽማለች ለዚህም ሐማስ ለውትድርና ተግባራት ሽፋን አድርጎ እንደሚጠቀምባቸው ትናገራለች። ሐማስ ይህንን አይቀበለውም።