በእስራኤል ጥቃት ከተገደለች እናት ማህጸን በሕይወት ወጥታ የነበረችው ጨቅላ አረፈች

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ በፈጸመችው ጥቃት ከተገደለች ፍልስጤማዊት እናት ማህጸን በሕይወት መውጣት ችላ የነበረችው ጨቅላ ከቀናት በኋላ አረፈች።

ሳብሪን አል ሳካኒን ከሙት እናቷ ማህጸን እንድትወጣ ተደርጎ የነበረው በቀዶ ህክምና ነበር።

የህክምና ባለሙያዎች እጃቸውን በመጠቀም አየር ወደ ሳንባዋ እንዲገባ ለማድረግ እና እንድትነቃም ለማድረግ ሞክረው ነበር።

ጨቅላዋ በሕይወት ከወጣች ከቀናት በኋላ ዛሬ ሚያዝያ 18/ 2016 ዓ.ም. ሕይወቷ አልፏል።

በሙት እናቷ ስም ተሰይማ የነበረችው ሳብሪና ከእናቷ አጠገብ ተቀብራለች።

ህጻን ሳብሪና ባለፈው ሳምንት ማገባደጃ ላይ ራፋህ ላይ እስራኤል በፈጸመችው የአየር ጥቃት ከተገደሉ 16 ህጻናት መካከል አንዷ ናት።

እስራኤል መኖሪያ ቤታቸውን ኢላማ አድርጋ በፈጸመችው ጥቃት መላው ቤተሰቧ ተገድሏል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል የሐማስ ታጣቂዎች እና መሠረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ነው ብሏል።

እስራኤል ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ እኩለ ሌሊት ላይ በአልሳካኒ መኖሪያ ቤት ላይ ጥቃት በምትፈጽምበት ወቅት የሰባት ወር ተኩል ነፍሰ ጡር የነበረችው እናት፣ ባለቤቷ ሹክሪ እና የሦስት ዓመት ልጃቸው ማላክ እንቅልፍ ወስዷቸው ነበር።

መላው ቤተሰብ በተገደለበት በዚህ ጥቃት በሳብሪን ማህጸን ውስጥ የነበረችውን ጨቅላ በሕይወት ማትረፍ ተችሎ ነበረ።

እናቲቱን ወደ ሆስፒታል ከወሰዷት በኋላ ድንገተኛ ቀዶ ህክምና (ሲ ሴክሽን) አድርገው ህጻኗ በሕይወት ወጥታ ነበር።

ህጻኗን በጨቅላ ህጻናት ማሞቂያ ውስጥ እንድትገባ የተደረገ ሲሆን፣ የህክምና ባለሙያዎች በአደገኛ ሁኔታ ላይ እንደሆነች በወቅቱ ገልጸዋል።

1.4 ኪሎግራም የምትመዝነው ይህች ጨቅላ ያለጊዜዋ ከመወለዷ ጋር ተያይዞ የመተንፈስ እክል ነበራ ተብሏል።

የህጻኗ አያት ሚርፋት አል ሳካኒ ጨቅላዋን ቤተሰቡ እንደሚያሳድጋት ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

እስራኤል በከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ ውስጥ የጀመረችውን የተቀናጀ ጥቃት ተከትሎ ከ34 ሺህ 180 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ስር ካለው የጤና ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ አመልክቷል።

ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በደቡባዊ እስራኤል ውስጥ በፈጸመው ጥቃት 1 ሺህ 200 ሰዎች መገደላቸውን እና 253 ታጋቾች መወሰዳቸውን የእስራኤል ባለሥልጣናት ማስታወቃቸው ይታወሳል።