ፍልስጤማዊው ዶክተር በእስራኤል እስር ቤት ህይወታቸው አለፈ

የ50 ዓመቱ ዶክተር አድናን አልቡርሽ

በእስራኤል እስር ቤት ውስጥ ከአራት ወራት በላይ በእስር ላይ የቆዩት ፍልስጤማዊው ዶክተር ህይወታቸው ማለፉን የፍልስጤም እስረኞች ማህበር አስታውቋል።

የ50 ዓመቱ ዶክተር አድናን አልቡርሽ እስራኤል ለበርካታ ጊዜ ወረራ የፈጸመችበት የአልሺፋ ሆስፒታል የአጥንት ህክምና ኃላፊ ነበሩ።

የእስራኤል እስር ቤት በደህንነት ምክንያት ተይዘው ስለነበሩት እና ኦፈር በተሰኘው እስር ቤት የሞቱት እስረኛ ዶክተር አልቡርሽ መሆናቸውን አረጋግጧል። የዶክተሩን የሞት መንስኤ በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ያልሰጠው የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ነገር ግን በምርመራ ላይ መሆኑን ገልጿል።

የፍልስጤም እስረኞች ተሟጋች ቡድኖች በዚህ ሳምንት ሐሙስ ዕለት በጋራ በሰጡት መግለጫ የዶ/ር አል ቡርሽ ሞት “ግድያ” እንደሆነ እና አስከሬናቸው በእስራኤል እስር ላይ እንዳለ አስታውቀዋል።

ዶክተር አል ቡርሽ የእስራኤል ጦር በተደጋጋሚ ወረራ የፈጸመበት የጋዛ ትልቁ የህክምና ተቋም አል ሺፋ ሆስፒታል የአጥንት ህክምና ኃላፊ ነበሩ።

በሰሜን ጋዛ በሚገኘው አል ዋዳ ሆስፒታል በጊዜያዊነት እየሰሩ ባለበት ወቅት ነበር በእስራኤል ወታደሮች በቁጥጥር የዋሉት።

ህልፈተ ህይወታቸውንም ተከትሎ የስራ ባልደረቦቻቸው በቀዶ ህክምና ባለሙያው ሞት የተሰማቸውን ኃዘን ገልጸው “ሩህሩህ” እና “ጀግና” ሲሉ አወድሰዋቸዋል።

የአል ሺፋ ሆስፒታል ዳይሬክተር ዶክተር ማርዋን አቡ ሰዓዳ የዶክተሩ ሞት ዜና “ለሰው ነፍስ መሸከም የሚከብድ ነው” ብለዋል።

ሌላኛው የስራ ባልደረባቸው ዶክተር ሱሃይር ማታር በበኩላቸው በሁሉም የጋዛ ሆስፒታሎች ውስጥ ላለው የአጥንት ህክምና “የደህንነት መቆጣጠሪያ” ሲሉ ጠርተዋቸዋል።

“በህይወትህ እሱን የመሰለ ሰው ማግኘቱ ብርቅ ነው ምክንያቱም ከራሱ በላይ ሰዎችን ያገለግል ያነበረ፤ ህይወቱን በሙሉ በትጋት ሲሰራ የነበረ ነው” በማለት ዶክተር ሱሃይር ለቢቢሲ አረብኛ ገልጸዋል።

የቀድሞ የስራ ባልደረባቸውን “መስራት የማይሰለቸው በሁሉም ሰው የተወደደ እና ፈገግታ የማይለው” ሲሉም ነው የገለጿቸው።

እስራኤል በኃይል በተቆጣጠረቻት ዌስት ባንክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ልዩ ራፖርተር ፍራንቼስካ አልባኔዝ በዶክተር አል ቡርሽ ሞት “በከፍተኛ ሁኔታ በጣም መደንገጣቸውን” ገልጸው የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ፍልስጤማውያንን ለመጠበቅ ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ጠይቀዋል።

የዶክተር አል ቡርሽ ሞት እስራኤል ከመስከረም መጨረሻ በኋላ በጋዛ እየፈጸመችው ባለው የማያባራ ጥቃት የተገደሉ የህክምና ባለሙያዎችን ቁጥር 496 እንዳደረሰው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በተጨማሪም 1 ሺህ 500 የህክምና ባለሙያዎች መቁሰላቸውን እና 309 ደግሞ በእስር ላይ እንዳሉ በሐማስ አስተዳደር ስር ያለው የጤና ሚኒስቴሩ አክሏል።

የህክምና ተቋማት በአለም አቀፍ ህግ የተጠበቁ ቢሆኑም እስራኤል በሆስፒታሎች ላይ በርካታ ወረራዎች እና ጥቃቶች ትፈጽማለች ለዚህም ሐማስ ለውትድርና ተግባራት ሽፋን አድርጎ እንደሚጠቀምባቸው ትናገራለች። ሐማስ ይህንን አይቀበለውም።