ኤሎን መስክ የትዊተር ሠራተኞች ረዥም ሰዓት መሥራት ካልቻሉ እንዲለቁ ጠየቀ

ኤሎን መስክ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በቅርቡ ትዊተርን የገዛው ኤሎን መስክ ሠራተኞቹ “ለረዥም ሰዓት በከፍተኛ ጥንካሬ” ለመሥራት ቁርጠኝነት ከሌላቸው ኩባንያውን እንዲለቁ መናገሩን ሪፖርቶች ይፋ አደረጉ።

አዲሱ የማኅበራዊ ድርጅት ባለቤት ለሠራተኞች በላከው ኢሜል ሠራተኞቹ በኩባንያው መቀጠል ከፈለጉ በዚህ ዓይነት አሠራር ለመቀጠል ቃል መግባት እንዳለባቸው ማሳሰቡን ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል።

በኩባንያው አሠራር የማይስማሙና እስከ ሐሙስ ያልፈረሙ የሦስት ወር የሥራ ስንብት ክፍያ እንደሚሰጣቸው መስክ ተናግሯል።

ቢቢሲ የትዊተርን ምላሽ ለማካተት ኩባንያውን አስተያየቱን ጠይቆ ነበር።

ዘጋርዲያን ባየውና ኤሎን መስክ ለሠራተኞቹ በጻፈው ኢሜል ትዊተር ስኬታማ ለመሆን ወጣ ያሉ ጥብቅ እርምጃዎችን መውሰድ እንዳለበት መናገሩም ተዘግቧል።

"ይህ ማለት ለረዥም ሰዓታት በከፍተኛ ጥንካሬ መሥራት ማለት ነው። በልዩ ሁኔታ የኩባንያውን ሥራ በብቃት የሚያከናውኑ ሠራተኞች ብቻ በድርጅታችን ቀጣይ ይሆናሉ" ብሏል።

ሠራተኞቹ "የአዲሱ ትዊተር አባል" መሆን ከፈለጉ ሐሙስ እስከ 11 ሰዓት ድረስ መፈረም እንደሚጠበቅባቸው ተነግሯቸዋል።

አክሎም "ምንም ዓይነት ውሳኔ ብትወስኑ ትዊተርን ስኬታማ ለማድረግ ላደረጋችሁት ጥረት እናመሰግናለን" ብሏል።

የዓለማችን እጅግ ባለጸጋው መስክ ኩባንያውን በ44 ቢሊየን ዶላር ውል ከገዛ በኋላ ግማሽ የሚሆኑት የትዊተር ሠራተኞች እንደሚለቁ አስታውቋል።

መስክ ኩባንያው በቀን 4 ሚሊዮን ዶላር እየከሰረ በመሆኑም ሠራተኞቹን ከመቀነስ ውጭ ምንም ምርጫ እንደሌለው አስረድቷል።

 “ለገቢው ከፍተኛ ማሽቆልቆልም፤ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የማስታወቂያ ኩባንያዎች በማኅበራዊ ድረ ገጹ ላይ እንዳያስተዋውቁ ጫና ማሳደራቸው ነው” ሲል ወቅሷል።

መስክ ድርጅቱን መግዛቱን ተከትሎ በርካታ ከፍተኛ የትዊተር ሥራ አስፈፃሚዎች ከሥልጣናቸው ተነስተዋል።

ባለፈው ሳምንትም ኤሎን መስክ ለትዊተር ሠራተኞች እንደተናገረው የኩባንያውን ሥራ ከቤት ሆኖ መሥራት እንደሚያበቃና "አስቸጋሪ ጊዜያት" ወደፊት እንደሚጠብቃቸው ሪፖርቶች ገልጸዋል።

ኤሎን መስክ ለሠራተኞች በላከው ኢሜል ሠራተኞች በሳምንት ቢያንስ ለ40 ሰዓታት በቢሮ ውስጥ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግሯል ሲል ብሉምበርግ ዘግቧል።