የፌስቡክ እና የትዊተር የሠራተኞች ቅነሳ ከኢትዮጵያ አንጻር ምን አንደምታ ይኖረዋል?

የፎቶው ባለመብት, NURPHOTO
ያለፉት ሁለት ወራት በማኅበራዊ ሚዲያው ዓለም ከፍተኛ ነውጥ የታየበት ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም። የዓለማችን ቁጥር አንድ ሃብታም የሆነው ኤሎን መስክ ትዊተርን መግዛቱን ተከትሎ ቀዳሚ እርምጃው ያደረገው በቀን 4 ሚሊዮን ዶላር ያሳጣኛል ያለውን የሰው ኃይሉን መጠን መቀነስ ነበር።
በመላው ዓለም ሁለት ቢሊየን ገደማ በየቀኑ የሚጎበኙት ደንበኞች ያሉት አንጋፋው ፌስቡክን የሚያስተዳደረው ሜታም ሠራተኞችን የመቀነስ ሃሳቡን ይፋ አድርጓል።
ይህም ወደ 11 ሺህ የሚጠጉ ሠራተኞቹን ሊነካ እንደሚችል የድርጅቱ መሥራች እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማርክ ዙከርበርግ ተናግሯል።
የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎቹ ለሰው ኃይል ቁጥር ቅነሳቸው የዓለም ኢኮኖሚ እየገባበት ያለውን ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስን ምክንያት አድርገው ይጠቅሱታል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሽን የሰውን ሥራ እየተካ መምጣቱ እሙን ነው። በተለይም የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የሰው ኃይላቸውን በመቀነስ በአርቴፊሻል ኢንተለጀስ መተካት መቻላቸው ከሰሞኑ እየተሰማነው ላለው የሰው ኃይል ቅነሳ የራሱ ሚና መጫወቱን ባለሞያዎች በሰፊው እያነሱት ያለ ጉዳይ ነው።
የፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ዋትስአፕ ባለቤት የሆነው ሜታ ሠራተኞቹን እንደሚቀንስ ካሳወቀ በኋላ ቢቢሲ ይህ ውሳኔ ድርጅቱ በአፍሪካ ውስጥ ያለውን ሥራ ምን ያህል እንደሚነካ ጠይቆ ነበር። ነገር ግን የድርጅቱ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማርክ ዙከርበርግ በይፋ ካሳወቀው የቅነሳ መረጃ ውጪ ዝርዝር ነገር እንደማይናገሩ ምላሽ ሰጥተዋል።
ሥራ አስፈጻሚው ከአንድ ሳምንት በፊት ለሠራተኞቹ እንዳሳወቀው፣ የድርጅቱ የሰው ኃይል በ13 በመቶ እንደሚቀነስ እና ይህም 11,000 ሠራተኞችን እንደሚነካ ገልጾ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ብቁ ሆነው በገበያው ውስጥ ለመቀጠል ሌሎች እርምጃዎችንም እንደሚወሰዱ አሳውቋል።
የኢኮኖሚ ጉዳዩን ወደ ጎን ብለን በተለይም በሜታ እና በትዊተር ውስጥ እየተተገበሩ ያሉት እነዚህ ለውጦች ከግጭት አንጻር በተለይም በኢትዮጵያ ባላቸው ተጠቃሚዎች ዘንድ ምን ጫና ሊያመጣ ይችል ይሆን? ስንል እንጠይቃለን።
ስጋቱ ከየት የመነጨ ነው ?
ፌስቡክ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ተጠቃሚ ያለው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ሲሆን፣ በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ግጭቶችን በማባባስ በተደጋጋሚ ተወቅሷል።
የቀድሞው የፌስቡክ ሠራተኛ ፍራንሲስ ሐውገን ከአንድ ዓመት በፊት በአሜሪካ ኮንግረስ ፊት ቀርበው ድርጅቱ በኢትዮጵያ እና በምያንማር ግጭት ቀስቃሽ እና ሐሰተኛ መረጃዎችን ሳያስቆም ቀርቷል ሲሉ መመስከራቸው ይታወሳል።
በደም አፋሳሽ ግጭቶች እና ጦርነት ውስጥ በምትገኘው ኢትዮጵያ ግጭት ቀስቃሽ ይዘቶችን በአግባቡ መቆጣጠር እንዳልቻለ በተደጋጋሚ የሚወቀሰው የፌስቡክ ባለቤት የሆነው ሜታ አሁን ያሰበው የሰው ኃይል ቅነሳ የይዘት ቁጥጥርን ይነካ ይሆን የሚሉ ስጋቶች ጨምረዋል።
የበይነ መረብ ደኅንነት እና የዲጂታል መብቶች አማካሪ እና ተመራማሪ የሆኑት ሰላማዊት ተዘራ እንደሚሉት ትዊተር እስካሁን ባካሄደው የሠራተኛ ቅነሳ የሰብአዊ መብቶች ክፍል ሠራተኞችን በሰፊው ነክቷል። የፌስቡክም እርምጃ ከዚህ የተለየ ይሆናል ብለው አያምኑም።
“ትልልቅ ኩባንያዎች መሠረታዊ የሆነው ኢላማቸው ትርፍ በመሆኑ ተመሳሳይ አሰራር ነው ያላቸው። ስለዚህ አሁን ከሜታ የሰማነው ጉዳይ [የቅነሳ ዜና] የይዘት ክትትል ክፍሉን በእርግጠኝነት ይነካል። የእኔ ስጋት እጅግ ዝቅተኛ ገቢ ባለው ነገር ግን ሰፊው በሆነው ሰፊው ደቡብ የዓለም ክፍል ውስጥ ያለውን ችግር የበለጠ እንዳያባብሰው ነው።”
እነዚህ ትልልቅ የመረጃ ማዘዋወሪያ ዘዴ ባለቤት ኩባንያዎች የሠራተኛ ቅነሳ ከማካሄዳቸው ቀደም ብለው የይዘት ክትትል ሥራቸውን በሰው ከማከናወን ይልቅ በማሽን መስራትን ይመርጣሉ የሚል ወቀሳዎች ሲቀርቡባቸው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በኢትዮጵያ በተለይም ፌስቡክ በአገር ውስጥ ቋንቋዎች በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮቹ ላይ የሚወጡ ልጥፎችን በተመለከተ፣ በጅምላ ጥቂት ቃላትን በመመልከት የአርቲፊሸል ኢንተለጀንስ ሥርዓቱ የሚሰጠው ብያኔ በርካታ ጥያቄዎችን ሲያስነሳ ቆይቷል።
በተቃራኒው ደግሞ ምንም አይነት ድንጋጌዎችን ያልጣሱ ሰዎች ላይ እርምጃ መውሰድ፣ ብሎም አጅግ አሳሳቢ ይዘቶችን አውዱን ባለመረዳት አስፈላጊውን እርምጃ ባለመውሰድ በርካታ ተጠቃሚዎች እሮሯቸውን ያሰማሉ።
የትዊተር የይዘት ክትትል በተለይም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ችግር ያለበት እንደሆነ ከበይነ መረብ እና ከማኅበራዊ ሚዲያ ጋር በተያያዘ ባለሙያዋ ሰላማዊት ይናገራሉ።
ትዊተር የጥላቻ ብሎም አዋራጅ ተግባራትን ለመለየት ቀናትን ይወስድበታል የሚሉት ባለሙያዋ፣ አንድ ይዘት ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት ከደረሰ በኋላ ትዊተር ጉዳዩን መመልከቱ እጅግ አሳሳቢ ነው ይላሉ።
ታዲያ እነዚህ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋማት አሁን ካላቸው የይዘት ተከታታዮች ብሎም የሰብአዊ መብቶች ክፍል ሠራተኞች ላይ ቅነሳ ካካሄዱ፣ ይህ ጉዳይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገራት በርካታ ገጾች ያሉትን ችግር ይዞ ይመጣል የሚል ስጋት ጨምሯል።
“የሚዲያ እውቀት ዝቅተኛ በሆነባቸው አገራት ማኅበራዊ ሚዲያ በተለይም በግጭት ወቅት ከፍተኛ ሚና አለው። ስለዚህ የይዘት ቁጥጥር ሠራተኞች ቅነሳው በአጠቃላይ ከአሜሪካ እና አውሮፓ ውጪ ባሉ አገራት ውስጥ ከፍተኛ ችግርን ይዞ ይመጣል።
“ስለዚህም ለእኔ ሜታ [ፌስቡክ] ኢትዮጵያ ቋንቋዎችን ይዘት የሚከታተሉ ባለሙያዎችን ይቀንሳል ብዬ ለማመን ይከብደኛል” ይላሉ።
በመላው ዓለም ያሉ የዲጂታል መብቶች ተሟጋቾች ፌስቡክ በተለይም በኢትዮጵያ ያለውን የይዘት ክትትል በተመለከተ ተጠያቂ ሲያደርጉት ቆይተዋል። ነገር ግን ትርፋማነቴ እየቀነሰ ነው ብሎ ካመነ ሜታ ይህንን የኢትዮጵያ የይዘት ክትትሉን መንካቱ እንደማይቀር ሰላማዊት ይናገራሉ።
ነገር ግን ፌስቡክ ይህንን ከግምት ሳያስገባ ቅነሳውን ካካሄደ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የጥላቻ ንግግር፣ የሐሰተኛ መረጃ ዝውውር ብሎም መሰል አደገኛ ይዘቶች የበለጠ በማቀጣጠል የበለጠ ሚና እንደሚጫወት ባለሙያዋ ያስጠነቅቃሉ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እነዚህ እርምጃዎች ምን ሊያስከትሉ ይችላሉ?
ተቋማቱ በኢትዮጵያ ቋንቋዎች የይዘት ክትትል ላይ የሰው ኃይል ቅነሳ የሚያደርጉ ከሆነ አሁንም እጅግ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን አቅማቸውን በማዳከም በቀጥታ በሰብአዊ መብቶች ላይ ጫና ከማሳረፉ ባሻገር ተጨማሪ መዘዝ ይዞ መምጣቱ እንደማይቀር ሰላማዊት ይናገራሉ።
የእርምጃቸውን አጠቃላይ ውጤት መተንበይ ባይቻልም በተለይም መንግሥታት ሥልጣናቸውን የሚገዳደር ፈተና የሚያስከትልባቸው ከሆነ ማኅበራዊ ሚዲያን ሙሉ በሙሉ እስከማገድ ሊደርሱ እንደሚችሉም ያክላሉ።
ከዚህ ቀደም የኡጋንዳ እና የኢትዮጵያ መንግሥታት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን እገዳዎች የማድረግ ታሪክ ያላቸው አገራት ናቸው። ናይጄሪያ ትዊተርን የፕሬዝዳንቱን ትዊት ሰርዟል፣ ለተገንጣዮች ወግኗል ብሎም ግጭት ቀስቃሽ ይዘቶችን ችላ ብሏል በሚል ለወራት አግዳው ነበር። ሥራውን መልሶ ለመጀመርም በአገሪቱ ቢሮ እንዲከፍት ጥያቄ ቀርቦም ነበር።
ምንም እንኳን መንግሥታት ማኅበራዊ ሚዲያን ሙሉ በሙሉ የመዝጋታቸው ዕድል ዝቅተኛ ቢሆንም፣ በተለይ በእነዚህ የመገናኛ ዘዴዎች ላይ የሚሰራጩ ይዘቶች በመሬት ላይ የሚያመጡትን ውጤት በመፍራት በጭራሽ እርምጃ አይወስዱም ማለት እንደማይቻል ሰላማዊት ተናግረዋል።
የይዘት ቁጥጥር ተግባራት መሠረት የሚያደርጉት ማኅበራዊ ሚዲዎቹ የሚያዘጋጁትን የተጠቃሚዎች ደንቦችን ነው።
እነዚህን ማደረጃት እና ከጊዜ ወደ ጊዜ ለማሻሻል ዓመታትን የጠየቀ ልፋት መደረጉን ሰላማዊት ይናገራሉ። ተቋማቱ በተለይም በምርጫ ወቀት ዲሞክራሲን ለሚቃረኑ አላማዎች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ በማሰብ በርካታ ሚሊዮኖችን በማውጣት ይሰራሉ።
ፌስቡክ አንድ ዓመት በፊት በኢትዮጵያ በተካሄደው 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ወቅት ግጭት ቀስቃሽ ብሎም ፀረ ዴሞክራሲ ይዘቶችን ለመቆጣጠር ያደረገው ጥረት ይታወሳል።
ታዲያ የሰብአዊ መብቶች እና የይዘት ቁጥጥር ሠራተኞችን ማባረር ይህ ለበርካታ ዓመታት የተለፋበትን መሻሻል ይጎዳዋል ሲሉ ሰላማዊት ይናገራሉ።
ነገር ግን አሁን ባለን መረጃ ላይ ብቻ ተመስርቶ አጠቃላይ ውጤቱን መተንበይ ገና አስቸጋሪ መሆኑንም ያክላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
መፍትሄው ምንድነው?
የሲቪል ማኅበረሰቡ አባላት ብሎም የዲጂታል መብት ተሟጋቾች የፌስቡክ የሰው ኃይል ቅነሳን በተመለከተ እስካሁን ትኩረት የሰጡት አይመስልም።
ነገር ግን የሰው ኃይል ቅነሳው በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ይዘት ክትትል ላይ የሚያመጣውን ጫና ከግምት ውስጥ አስገብተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው በመስኩ ሰፊ ዕውቀት እና በተለያዩ ተቋማት ውስጥ የዓመታት ልምድ ያላቸው ሰላማዊት ይመክራሉ።
የሲቪል ማኅበራት ብሎም መንግሥታት በጋራ በመሆን የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ግጭት ቀስቃሽ ይዘቶችን በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ካላነሱ ተጠያቂ የሚሆኑበትን አሰራር ማበጀት ይገባቸዋልም ይላሉ።
በማኅበራዊ ደንቦች ቅርጽ ብሎም እነሱን ለማስፈጸም በሚደረግ የይዘት ክትትል በኩል ፌስቡክ የተሻለ ርቀት መጓዙን የሚገልጹት ባለሙያዋ፣ አሁን ላይ እንደ ቴሌግራም ያሉት ዘዴዎች የበለጠ ስጋት በመሆናቸው አትኩሮት መስጠት እንደሚገባም ይናገራሉ።
ነገር ግን ዋነኛውና ዘላቂው መፍትሄ የሚሆነው የባሕሪይ ለውጥ ለማምጣት የሚዲያ አጠቃቀም ትምህርትን በሰፊው መስጠት ነው ሲሉም ያሳስባሉ።
ይህ የመረጃ ማጣራት ሥራዎች፣ የጥላቻ እና ሰብእናን የሚያዋርዱ ቃላትን የመለየትን ብሎም የአንድ ዜናን ትክክለኛነት የመለካት ተግባራትን ዜጎች በቀላሉ ማካሄድ እንዲችሉ ማስተማርን ይጠይቃል።












