በኬንያ ትናንት በነበረ ተቃውሞ በትንሹ 11 ሰዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ትናንት ሰኞ ዕለት በኬንያ በነበረ ፀረ መንግሥት ተቃውሞ ቢያንስ 11 ሰዎች ሲገደሉ 567 ሰዎች ደግሞ መታሰራቸውን ፖሊስ አስታወቀ።
ፖሊስ በሰላማዊ ሠልፈኞች ላይ ተኩስ መክፈቱን ከናይሮቢ ወጣ ብሎ በሚገኘው የኤግል ነርሲንግ ሆም የሕክምና ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር አሮን ሲኩኩ ተናግረዋል።
የሕክምና ባለሙያው በጥይት ቆስለው የሞቱ የሁለት ሰዎች አስከሬን ወደ ተቋማቸው መምጣቱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች ከሆስፒታሉ ደጃፍ ተሰብስበው አስከሬኖቹን ለመውሰድ እየተጠባበቁ እንደነበር ጨምረው ገልጸዋል።
ሠልፎቹ እአአ ሐምሌ 7/1990 በኬንያ የመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲን ለመጠየቅ አደባባይ የተወጣበትን 35ኛ ዓመት ታሳቢ በማድረግ የተካሄዱ ናቸው።
ይህ ታሪካዊ ዕለት ሳባ ሳባ (ሰባት ሰባት) በመባል ይታወቃል።
ፖሊስ ሰኞ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ አባላቱ "በቀጠለው አመጽ እና ቁጣ ውስጥ ላሳዩት የተለየ ተዓቅቦ እና ሙያዊ ሥነምግባር" አወድሷል።
ፖሊስ በዚሁ መግለጫው ላይ 52 የፖሊስ አባላት እና 11 ሰላማዊ ሰዎች ቆስለዋል ብሏል።
መንግሥት የሚቆጣጠረው የኬንያ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ቢያንስ 10 ሰዎች መሞታቸውን ተናግሯል።
ኮሚሽኑ ባወጣው አጭር መግለጫ ፖሊስ ከልክ ያለፈ ኃይል ተጠቅሟል ሲል ከስሷል።
ሰኞ ዕለት "ፖሊስ ሲቪል በለበሱ እና ምልክት በሌላቸው ተሸከርካሪዎች" ሲንቀሳቀስ የነበረ ሲሆን "በናይሮቢ፣ ካጂያዶ፣ ናኩሩ፣ ኪያምቡ እና ኤልዶሬት ከታጠቁ የወንጀለኞች ቡድን ጋር ተባብሯል" ብሏል።
ፖሊስ ከዚህ ቀደም እንዲህ ያለውን ክስ ውድቅ አድርጓል።
ቢያንስ ሁለት ሰዎች ታፍነው መወሰዳቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንዳለው የገለፀው ኮሚሽኑ፣ እንዲሁም 29 ሰዎች መቁሰላቸውን እና 37ቱ ደግሞ በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች መታሰራቸውን ገልጿል።
ከማለዳ ጀምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሰቀቀሱ መንገደኞች ከመሀል ናይሮቢ ከ10 ኪሜ ርቀት ላይ በሚገኙ የፍተሻ ጣብያዎችን እንዳያልፉ ተከልክለው የነበረ ሲሆን ጥቂት ተሽከርካሪዎች ብቻ ወደ መዲናዋ ናይሮቢ እንዲገቡ ተፈቅዶላቸዋል።
ወደ ቁልፍ የመንግሥት ቢሮዎች የሚወስዱ መንገዶች፣ የፕሬዚዳንቱ መኖሪያ፣ ቤተ መንግሥት እና የኬንያ ፓርላማን ጨምሮ በሽቦ አጥር ተዘግቶ ነበር።
አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ቤታቸው እንዲቆዩ የሚገልጽ ማሳሰቢያ አስቀድመው ልከዋል።
ነገር ግን በመዲናዋ አንዳንድ አካባቢዎች ሠልፈኞች አደባባይ በመውጣት እና እሳት በማቀጣጠል የፖሊስን እገዳ ለማለፍ ሲሞክሩ ግጭት ተፈጥሯል።
ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ እና ውሃ በመርጨት ምላሽ ሰጥቷል።
የኬንያ ታዋቂ ጋዜጣ የሆነው ዘ ኔሽን እንደዘገበው ከ47ቱ የኬንያ ካውንቲዎች መካከል በ17ቱ ተቃውሞ ሠልፍ ተካሄዷል።
በኬንያ ምሥራቅ ሜሩ ካውንቲ በማኩታኖ ከተማ የገበያ ማዕከል በእሳት ሲቀጣጠል ከሕንጻው ውስጥ ጥቁር ጭስ ወደ ሰማይ ሲትጎለጎል ይታይ ነበር።
በኦል ካሎው ከተማ አንድ ሠልፈኛ በጥይት ተመትቶ ሲገደል ሌላው ደግሞ በጥይት ቆስሎ ተርፏል።
የመጀመሪያው የሳባ ሳባ የተቃውሞ ሠልፍ የተካሄደባት ናይሮቢ አቅራቢያ በምትገኘው ካሙኩንጂ፣ ፖሊሶች በጎዳናዎች ላይ እሳት ካነደዱ ተቃዋሚ ሠልፈኞች ጋር ግጭት ውስጥ ገብተው ታይተዋል።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ራይላ ኦዲንጋ ሊያካሄዱ የነበረው ስብሰባ መንገዶች በመዘጋጋታቸው የተነሳ ተሰርዟል።
"በከተማው ሁሉ ያለው የመንገድ መዘጋት ሰዎች ወደ ካሙኩንጂ ለመሄድ አስቸጋሪ አድርጎባቸዋል" ያሉ ሲሆን፣ "ይህንን አስፈላጊ ቀን ለማክበር ኬንያውያንን መቀላቀል አልቻልኩም" ብለዋል።
ይህን ግን የኬንያ ፖሊስን ከመተቸት አላገዳቸውም።
"ሰዎች ላይ ያለ ከልካይ የሚተኩስ፣ ከቅኝ ገዥዎች የተወረሰ ኃይል" ሲሉ የተቹ ሲሆን፣ የአገሪቱ ፖሊስ ላይ ተሃድሶ እንዲካሄድ ብሔራዊ ውይይት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
ራይላ ኦዲንጋ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1990 በተካሄደው የመጀመርያው የሳባ ሳባ ተቃውሞ ሠልፍ ላይ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው የነበረ ሲሆን ባለፈው ዓመት ግን ድጋፋቸውን ለመንግሥት ሰጥተዋል።

ፖሊስ እሁድ ማምሻውን በሰጠው መግለጫ የሕዝብን ፀጥታ ማስከበር፣ የሰው ሕይወትና ንብረት መጠበቅ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታው መሆኑን ገልጿል።
የሰኞውን ሠልፍ በዋነኛነት ያዘጋጁት ወጣቶች ሲሆኑ ካለፈው ዓመት ጀምሮ መንግሥትን በመቃወም አደባባይ ሲወጡ የሚያነሷቸውን የመልካም አስተዳደር እና በመንግሥት ኃላፊዎች ዘንድ ተጠያቂነት እንዲሰፍን አሁንም አንስተዋል።
አክለውም በፖሊስ ጥቃት ሰለባ ለሆኑ ኬንያውያን ፍትህ ጠይቀዋል።
እአአ ሰኔ 25፣ ባለፈው ዓመት አዲሱን የግብር ሕግ በመቃወም በተካሄደው ሠልፍ ወቅት ለተገደሉት ሰዎች ክብር ሲባል በተካሄደው አገር አቀፍ ተቃውሞ ቢያንስ 19 ሰዎች ተገድለዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ የንግድ ድርጅቶች ተዘርፈዋል፤ ወድመዋል።
እሁድ ዕለት የኬንያ ሠብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከሰኞው ሠልፍ በፊት ሴቶች በመንግሥት የሚፈጸሙ ትቃቶች እንዲቆሙ የሚጠይቅ ጋዜጣዊ መግለጫ እየተሰጠ ባለበት ወቅት የታጠቁ የወሮበሎች ቡድን በዋና መስሪያ ቤቱ ላይ ጥቃት ሰንዝሯል።
የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ኧርነስት ኮርኔል እንዳሉት ወንበዴዎቹ ቢያንስ 25 በሞተር ሳይክሎች ላይ ተጭነው የመጡ መሆኑን ገልጸው "ዛሬ ምንም አይነት ተቃውሞ አይኖርም" እያሉ የሚዘምሩ ናቸው ብለዋል።
"ድንጋዮችን ይዘው ነበር፣ ዱላ የያዙም ይገኙበታል... ላፕቶፖችን፣ ስልክ ሰረቀዋል እንዲሁም እዚያ ከነበሩ ጋዜጠኞች ላይም አንዳንድ ውድ ዕቃዎችን ወስደዋል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የመጀመሪያው የሳባ ሳባ ተቃውሞ በኬንያ ከብዙ ዓመታት የአንድ ፓርቲ አገዛዝ በኋላ የመድበለ ፓርቲ ዲሞክራሲን ለማምጣት የረዳ ቁልፍ ወቅት ነበር።
በወቅቱ በፕሬዚዳንት ዳንኤል አራፕ ሞይ ይመራ የነበረው መንግሥት የሰጠው ምላሽ ጭካኔ የተሞላበት ነበር።
በርካታ ተቃዋሚዎች የታሰሩ ሲሆን በትንሹ 20 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሳባ ሳባ የዜጎችን ተቃውሞ እና በኬንያ ውስጥ ለዲሞክራሲያዊ ነፃነት የሚደረግን ትግል ለመዘከር ይውላል።















