በፖሊስ በጥይት የተመታው ኬንያዊ የጎዳና ነጋዴ ሕይወት አለፈ

የፎቶው ባለመብት, Boniface Kariuki's family
ከሁለት ሳምንት በፊት በኬንያ በተደረገ የተቃውሞ ሰልፍ በፖሊስ ጥይት ጭንቅላቱን የተመታው እና በህይወት ድጋፍ መሳሪያ ሲታገዝ የነበረው የጎዳና ነጋዴ ሕይወቱ ማለፉን ቤተሰቦቹ ተናገሩ።
የቤተሰቡ ጠበቃ ኤሚሊ ዋንጂራ ለቢቢሲ "ቦኒፌስ አሁን የለም። አስከሬኑን አሁን ተመልክተናል" ብለዋል።
ቦኒፌስ ካሩዩኪ የ31 ዓመቱ መምህር እና ጦማሪ አልበርት ኦጅዋንግ በፖሊስ ጣቢያ ሕይወቱ አልፎ መገኘቱን ተከትሎ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ ነበር በፖሊስ በጥይት የተመታው።
መንገድ ላይ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ሻጭ የሆነው ቦኒፌስ በቅርብ ርቀት በጥይት ከተመታ በኋላ በናይሮቢ ሆስፒታል ለሕክምና ገብቶ ነበር።
ለቤተሰቦቹ አዕምሮው መስራት ማቆሙ እና ልቡ ግን እየመታ እንደሆነ ከመነገሩ በፊት ለሁለት ሳምንት ያህል በሕይወት ደጋፊ መሳሪያ ቆይቷል።
ሐኪሞች በርካታ ቀዶ ሕክምና ቢያደርጉም የጥይቱ ቁርጥራጭ በአንጎሉ ላይ መግባታቸውን ተናግረዋል።
የቦኒፌስ አንጎል መሞቱ ከተሰማ በኋላ በፖሊስ ጭካኔ ምክንያት ሕዝባዊ ቁጣ የተቀሰቀሰ ሲሆን፤ ፍትኅ እንዲሰፍን ጥያቄዎች በርትተዋል።
ቤተሰቦቹ ለሕክምና ወጪ ሕዝባዊ እርዳታ መጠየቃቸውንም ተከትሎ መንግሥት የሕክምና ወጪውን እንዲሸፍን በርካታ ኬንያዊያን ጠይቀዋል።
ተኩሱን ተከትሎ ሁለት የፖሊስ መኮንኖች ፍርድ ቤት ቢቀርቡም እስካሁን ድረስ ክስ አልተመሰረተባቸውም።
በሕግ ጥላ ስር ሆነው የምርመራውን ውጤት እየተጠባበቁ ናቸው።
እሁድ ዕለት የቦኒፌስ ቤተሰቦች ምርመራው እንዲፋጠን እና ፍትኅ እንዲያገኙ ባለስልጣናትን ጠይቀዋል።
ባለፉት ሳምንታት ኬንያ የተቃውሞ ማዕበል ያየች ሲሆን፤ ይህም በፖሊስ የሚደርስ ጭካኔ የተቀጣጠለ ነው።
ባለፈው ረቡዕ በነበረው ተቃውሞ ቢያን 19 ሰዎች መገደላቸውን የመብት ድርጅቶች አስታውቀዋል።
ነገር ግን የአገሪቱ ባለስልጣናት ለተፈጠረው ሁከት ፖሊስን እና ፖሊስ ጣቢያዎችን ለማጥቃት ተነስተዋል በሚል ተቃዋሚዎችን ተጠያቂ አድርገዋል።
ሰኞ ዕለት የወንጀል ምርመራ ኃላፊ የሆኑት መሐመድ አሚን በግድያ፣ ሽብር፣ አስገድዶ መድፈር፣ ዝርፊያ፣ የንብረት ውድመት እና በፖሊስ ላይ ጥቃት በመሰንዘር ወንጀሎች የተጠረጠሩ በአጠቃላይ 485 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አሳውቀዋል።
"ማንም ሰው በሰላማዊ ተቃውሞ የወንጀል ድርጊት በመፈፀም ሊደበቅ አይችልም" ያሉት ኃላፊው፤ "በጥቃቱ የተሳተፉትን ለመለየት ካሜራዎችን፣ የስልክ መረጃዎችን፣ የዲጂታል መልዕክት ልውውጦችን እየመረመርን ነው። ተጨማሪ እስራቶች ይቀጥላሉ" ብለዋል።
"የደኅንነት እና የእስር መዝገቦች አንዳንድ ግለሰቦች ሕዝባዊ እና የደኅንነት ተቋማትን ለማጥቃት ትዕዛዝ መቀበላቸውን አመልክተዋል" ሲሉም አክለዋል።
የወንጀል ምርመራ ኃላፊው በተቃውሞው ቢያንስ 11 ፖሊሶች ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ጠቁመው፤ አንዳንዶቹ ሕይወታቸውን የሚያሰጋቸው ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል።
የኬንያ የአገር ውስጥ ሚኒስትር ኪፕቻምቫ ሙርኮመን ባለፈው ሳምንት ተቃውሞውን "ሰላማዊ የመሰለ ሽብር" ብለውታል።
ፖሊስ ጣቢያዎችን የሚያጠቁ ሲቪሎችን "በቅፅበት በጥይት እንዲመቱ" ለፖሊሶች የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ ይህ ንግግራቸውም ከሕግ ባለሙያዎች እና ከመብት ተሟጋቾች ተጨማሪ ትችት አስተናግዷል።















