በኬንያ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ከፖሊስ ጋር ተጋጭተው ቢያንስ አስር ሰዎች ሲገደሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቆሰሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በኬንያ የፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ መንግሥትን በመቃወም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አደባባይ ወጥተው በተቀሰቀሰ ግጭት በትንሹ አስር ሰዎች ሲገደሉ 400 ደግሞ መቁሰላቸው ተገለፀ።
እአአ በ2024 በአገሪቱ የተቀሰቀሰውን ትልቅ የፀረ መንግሥት ተቃውሞ አንደኛ ዓመት ለማሰብ በናይሮቢ እና ሌሎች ከተሞች አደባባይ የወጡት ሠልፈኞች ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል።
አብዛኛዎቹ ሠልፈኞቹ "ሩቶ መውረድ አለበት" እያሉ መፈክር በማሰማት እና ሰላማዊ መሆናቸውን ለመግለጽ የዛፍ ዝንጣፊ እያውለበለቡ አደባባይ ወጥተዋል።
መንግሥት መገናኛ ብዙሃን የተቃውሞ ሠልፎቹን በቀጥታ የቴሌቪዥንና የሬድዮ ስርጭት እንዳያስተላለፉ የከለከለ ቢሆንም ነገር ግን ክልከላው በዋና ከተማዋ ናይሮቢ በሚገኘው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተሽሯል።
ሩቶ ተቃዋሚዎች ወደ ፕሬዚደንቱ መኖርያ እየተጠጉ ሲመጡ ሰላምና መረጋጋት እንዳያደፈርስ አሳስበዋል። ፖሊስ ተቃዋሚ ሠልፈኞቹ ወደ ፕሬዚደንቱ መኖርያ እንዳይጠጉ ተከላክሏል።
ፕሬዚደንቱ "የተቃውሞ ሰልፎች የኬንያን ሰላም ማደፍረስ የለባቸውም። ነገሮች ሲበላሹ የምንሄድበት ሌላ አገር የለንም፤ የአገራችንን ሰላም መጠበቅ የኛ ኃላፊነት ነው" ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ሩቶ ይህን ያሉት በባህር ዳርቻዋ ከተማ ኪሊፊ እየተካሄደ በነበረ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ነው።
ፕሬዚደንቱ በናይሮቢ በሚገኘው መኖርያ ቤታቸው አለመኖራቸው የተረዱ ተቃዋሚ ሠልፈኞች ወደ ቤተ መንግሥቱ ለመሄድ ሞክረዋል።
ፖሊሶች ዋና ዋና መንገዶችን፣ በተለይም ወደ ቤተ መንግሥቱ እና ፓርላማ የሚወስዱትን ለመዝጋት ሽቦ እና መሰናከሎችን ተጠቅሟል።
መንግእሥት ረቡዕ በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የሞቱትን ሰዎች ቁጥር እስካሁን በይፋ አልተናገረም።
ነገር ግን የኬንያ የሕክምና ማሕበር፣ የኬንያ የሕግ ባለሙያዎች ማሕበር እና የፖሊስ ሪፎርም ዎርኪንግ ግሩፕ በጋራ ባወጡት መግለጫ በትንሹ ስምንት ተቃዋሚ ሠልፈኞች መገደላቸውን አስታውቀዋል።
ከተጎዱት 400 ሰዎች መከካል 83ቱ "ልዩ ሕክምና" የሚያስፈልጋቸው ሲሆን ስምንቱ ደግሞ በጥይት ቆስለዋል።
ጉዳት ከደረሰባቸው መከካከል ሦስቱ የፖሊስ አባላት መሆናቸውንም መግለጫው አክሎ ገልጿል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ አምነስቲ ኬንያ የሟቾችን ቁጥር 16 አድርሶታል።
አንድ አሚና ሙዴ የምትባል ሠልፈኛ የተቃውሞ ሠልፉን ለምን እንደተቀላቀለች ለቢቢሲ ስትናገር "የልጆቼን የወደፊት ዕድል ለመታገል" ብላለች።
"እንደ አገር በተለይ በትምህርት እና ሌሎች ነገሮች ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ እየሄድ አለመሆኑ ይሰማኛል። አገሪቱ እና አመራሩ እኛን የሚያዳምጡበት ጊዜ አሁን እንደሆነ ይሰማኛል።"
በናይሮቢ በነበረው የተቃውሞ ሠልፍ ላይ የተቀረፁ የተንቀሳቃሽ ምስሎች ነጭ አስለቃሽ ጭስ ሲተኮስ፣ ተቃዋሚዎች ሽፋን ለማግኘት ሲሯሯጡ፣ ሲያስሉ እና ዓይኖቻቸውን ሲከላከሉ ያሳያል።
በከተማው መሀል ተቃዋሚ ሠልፈኞች በተዘጉ ሱቆች እና ባዶ ጎዳናዎች መካከል አልፈው ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ነበር።
ባለፈው ዓመት በዚህ አካባቢ የተገደሉትን እና የቆሰሉትን ለማስታወስ በፓርላማው ዙሪያ ባለው አጥር ሐዘንተኛ ቤተሰቦች እና እምቢተኛ ወጣቶች የአበባ ጉንጉኖች እና በእጅ የተፃፉ ማስታወሻዎች ይዘው ታይተዋል።
አንዲት የኬንያ ባንዲራ የለበሰች ወጣት ሕዝባዊ ተቃውሞውን ለማስቆም በሚሞክሩ የጸጥታ ኃይሎች የተገደሉትን ሰዎች ስም ዝርዝር የያዘ ፖስተር ይዛ ነበር።















