በፖሊስ ቁጥጥር ስር እያለ በሞተው ጦማሪ ምክንያት የኬንያ ፖሊስ ምክትል አዛዥ ስራቸውን ለቀቁ

ባለፈው ሳምንት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሕይወቱ ያለው ጦማሪ ሞት በኬንያ ሕዝባዊ ቁጣን ቀስቅሷል

የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE/Shutterstock

የምስሉ መግለጫ, ባለፈው ሳምንት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሕይወቱ ያለው ጦማሪ ሞት በኬንያ ሕዝባዊ ቁጣን ቀስቅሷል

የኬንያ ፖሊስ ምክትል አዛዥ ኢሉይድ ላጋት በፖሊስ ቁጥጥር ስር እያለ ሕይወቱ ባለፈው ጦማሪ አልበርት ኦጅዋንግ ሞት ምርመራ እየተደረገ ባለበት ወቅት ስራቸውን ለቀቁ።

ጦማሪውን በማኅበራዊ የትስስር ገፆች ስሜን አጠፋው ያሉት የፖሊስ አዛዡ ስራቸውን እንዲለቁ ከተቃዋሚዎች እና ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጫና ውስጥ ነበሩ።

ፖሊስ በመጀመሪያ ጦማሪው ሕይወቱ ያለፈው በራሱ ላይ ባደረሰው ጉዳት መሆኑን ቢያሳውቅም፤ የአስከሬን ምርመራ ውጤቱ ግን በተደረሰበት ጥቃት እንደሞተ ካረጋገጠ በኋላ መግለጫውን ለማስተካከል ተገዷል።

የፖሊስ አዛዡ ምንም አይነት ጥፋት እንዳልፈፀሙ ቢገልፁም፤ እንደ ምክትል የፖሊስ አዛዥ ኃላፊነታቸው "በጥሩ እና መልካም እሳቤ" ስራቸውን ለመልቀቅ መወሰናቸውን በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

"በአሳዛኙ ክስተት ምርመራ የሚጠበቅብኝን ድጋፍን ለመስጠት ስል ይህን ውሳኔ ወስኛለሁ" ብለዋል።

አዛዡ አክለውም "ለአልበርት ኦጅዋንግ ቤተሰቦች ለደረሰባቸው ጉዳት ጥልቅ ሀዘንኔን እገልፃለሁ" ብለዋል።

ምርመራው እስኪጠናቀቅ ድረስ ላጋት ወደ ቢሯቸው መግባት የማይችሉ ሲሆን፤ ኃላፊነታቸውንም ምክትሎቻቸው ይረከቧቸዋል ተብሏል።

ይህ ውሳኔ የመጣው ጫናዎች እየበረቱ ባለበት ወቅት ሲሆን፤ በዚህ ሳምንት ለ31 ዓመቱ ጦማሪ ህልፈት ግልፅ ምርመራ እንዲደረግ የሚጠይቁ ሰላማዊ ሰልፎች ታቅደዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጦማሪ አልበርት ኦጅዋንግ ከ10 ቀናት በፊት በሆማ ቤይ ከተማ አቅራቢያ በቁጥጥር ስር ውሏል። ከዚህም በኋላ ወደ ናይሮቢ ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ተወስዶ ከታሰረ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሕይወቱ አልፏል።

ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ከሟቹ አባት ጋር መነጋገሩን ደይሊ ኔሽን የተባለ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

ሩቶ ለቀብር ስነ ስርዓት ማስፈፀሚያ ለጦማሪው ቤተሰቦች 15 ሺህ 500 ዶላር ገንዘብ እንደሚሰጡ ቃል መግባታቸውን የዘገበው መገናኛ ብዙኃኑ፤ ታዋቂው ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ራይላ ኦዲንጋ ከቤተሰቡ ጋር ተነጋግረው ግማሹን ገንዘብ እንደሚሸፍኑ ጠቅሷል።

ፖሊስ በመጀመሪያ ባወጣው መግለጫ ጦማሪው በእስር ቤት ክፍሉ ራሱን ስቶ ከተገኘ በኋላ ሆስፒታል ተወስዶ በግንባሩ ግድግዳውን በመደብደብ በደረሰበት ጉዳት ሕይወቱ ማለፉን ገልጿል።

ይሁን እንጂ የአስከሬን ምርመራ እና ፖሊስን በሚከታተለው ገለልተኛ የፖሊስ ቁጥጥር ባለስልጣን በተደረገ ምርመራ ጦማሪው ራሱን ገድሏል የሚያስብል ግምት አልተገኘም።

ምርመራው እንደቀጠለ ቢሆንም የፖሊስ ጣቢያው አዛዥ፣ አንድ የፖሊስ ባልደረባ እና የደኅንነት ካሜራውን አቋርጧል ተብሎ የተጠረጠረ የቴክኒክ ባለሙያ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

የፖሊስ አዛዥ የሆኑት ዳግላስ ካንጃ ጦማሪው ራሱ ላይ ባደረሰው ጉዳት ሕይወቱ አልፏል ለሚለው የመጀመሪያው የፖሊስ መግለጫ ይቅርታ የጠየቁ ሲሆን፤ ከበታች አመራሮች ያገኙት "የተሳሳተ መረጃ" መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ሩቶ ፈጣን ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ ያደረጉ ሲሆን፤ መንግሥታቸው ዜጎችን ከአፈንጋጭ ፖሊሶች እንደሚጠብቅ ቃል ገብተዋል።

ፕሬዝዳንቱ እ.አ.አ በ2022 ወደ ስልጣን ሲመጡ በፖሊስ የሚፈፀምን የጭካኔ እርምጃ እና ያለ ፍርድ ግድያ ከኬንያ ታሪክ ለመፋቅ ቃል ገብተው ነበር።