ኬንያ በተቃውሞ ምክንያት የማዕከላዊ ናይሮቢ መግቢያ እና መውጫ ሁሉንም መንገዶች ዘጋች

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images
በኬንያ ዛሬ ሰኞ፣ ሰኔ 30/2017 ዓ.ም. ከታቀደው ተቃውሞ በፊት የአገሪቱ ፀጥታ ኃይሎች የዋና ከተማዋ ናይሮቢ ማዕከላዊ ክፍል መግቢያ እና መውጫ ሁሉንም ዋና መንገዶችን ዘጉ።
በዛሬው ዕለት የታቀደውን ተቃውሞ በመስጋት የንግድ ተቋማት ተዘግተው አብዛኛው የከተማዋ ማዕከል ወና ሆኗል።
በየመንገዶቹ የፀጥታ ኃይሎች በከፍተኛ ቁጥር ሲሰማሩ፤ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች እንዳይመጡ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
በምሽት እንዲሁም በማለዳ እየተጓዙ የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተሳፋሪዎች አንዳንዶቹም ከማዕከላዊ ናይሮቢ በአስር ኪሎ ሜትር ርቀት እንዲሁም ከዚያ በራቁ የፍተሻ ኬላዎች ላይ እንዲቆሙ ተደርገዋል።
ኬላዎቹን ማለፍ የቻሉት ጥቂት ተሽከርካሪዎች ብቻ ናቸው።
በከተማዋ ወደ ፕሬዚዳንቱ ቤተ መንግሥት እና የኬንያ ፓርላማን ጨምሮ ቁልፍ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚወስዱ መንገዶች በአደገኛ ሽቦ እንዲታጠሩ ተደርገዋል።
ፖሊስ ከተቃውሞው አስቀድሞ እሁድ ማምሻውን በሰጠው መግለጫ ፀጥታን በማስከበር የሰው ሕይወት እና ንብረት የመጠበቅ ህገ መንግሥታዊ ግዴታው እንደሆነ ገልጿል።
ዛሬ የተጠራው ሕዝባዊ ተቃውሞ "ሳባ ሳባ" በመባል የሚጠራውን በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ ለመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲ በአገሪቱ የተደረገውን ትግል ለማስታወስ ነው።
በወጣቶች የሚዘጋጁት ሕዝባዊ የተቃውሞ ሰልፎች መልካም አስተዳደርን፣ የመንግሥት ተጠያቂነት እንዲሁም በፖሊስ ጭካኔ ሰለባ ለሆኑት ፍትህ የሚጠይቁ ናቸው።
ኬንያውያን የፋይናንስ ሕግ ረቂቅ መነሻ በማድረግ የአገሪቱን ፓርላማ ጭምር ጥሶ የገባውን ባለፈው ዓመት የተካሄደውን ፀረ መንግሥት ተቃውሞ አንደኛ ዓመትን ለመዘከር ሰኔ 18/2017 ዓ.ም. ሕዝባዊ ተቃውሞ አካሂደዋል።
በዚህም ተቃውሞ 19 ሰዎች ሲገደሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የንግድ ተቋማት ተዘርፈዋል እንዲሁም ወድመዋል።
በቅርቡ የተካሄዱ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ወደቀጠፉ ሁከቶች የተቀየሩ ሲሆን፤ ሰርገው የገቡ "ተቀጣሪ ወሮበሎች" ዝርፊያዎችን እንዲሁም ተቃዋሚዎች ላይ ጥቃቶች ፈጽመዋል የሚሉ ሪፖርቶች ወጥተዋል።
የሲቪል ማኅበራት በእነዚህ ወሮበሎች እና በፖሊስ መካከል ትብብር እንዳለ ክስ የሚያቀርቡ ሲሆን፤ ፖሊስ የቀረበበትን ክስ በጥብቅ አስተባብሏል።
እሁድ ዕለት የታጠቀ የወሮበላ ቡድን ናይሮቢ በሚገኝ መንግሥታዊ ባልሆነ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት ላይ ጥቃት ፈጽሟል።
የኬንያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መንግሥታዊ ጥቃት እንዲቆም የሚጠይቅ በሴቶች የተዘጋጀ ጋዜጣዊ መግለጫ እየሰጠ በነበረበት ወቅት ነው ጥቃቱ የተፈጸመው።
በአገሪቱ ለበርካታ ዓመታት የነበረው የአንድ ፓርቲ አገዛዝ እንዲቋጭ እና የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን ያደረገው 'ሳባ ሳባ' የተሰኘው ሕዝባዊ ተቃውሞ 35ኛ ዓመቱን ያከብራል።
በወቅቱ በፕሬዚዳንት ዳንኤል አራፕ ሞይ ይመራ የነበረው መንግሥት የሰጠው ምላሽ ጭካኔ የተሞላበት ነበር።
አንጋፋው ፖለቲከኛ እና አሁን ከመንግሥት ጋር እየሠሩ ያሉት ራይላ ኦዲንጋን ጨምሮ በርካታ ተቃዋሚዎች ለእስር እና ለስቅይት ተዳርገዋል።
በወቅቱ ቢያንስ 20 ተቃዋሚዎች ተገድለዋል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ 'ሳባ ሳባ' በኬንያ የሕዝባዊ እምቢተኝነት እና ለዲሞክራሲ የሚደረገውን የትግል ተምሳሌት ሆኖ ቆይቷል።
'ሳባ ሳባ' የሚለው የእንቅስቃሴው ስያሜ የመጣው ተቃውሞው የተጀመረበት የአውሮፓውያኑ ሰባተኛ ወር ሐምሌ እና የወሩ ሰባተኛ ቀንን ለማመልከት ሲሆን ይህም በስዋሂሊ ቋንቋ 'ሰባት ሰባት' ማለት ነው።















