የአርጀንቲና ምክትል ፕሬዝዳንት ከግድያ ሙከራ ለጥቂት አመለጡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአርጀንቲና ምክትል ፕሬዝዳንት ክርስቲና ፈርናንዴዝ ዴ ኪርችነር ትላንት ሃሙስ ምሽት ከግድያ ሙከራ ለጥቂት አመለጡ።
ምክትል ፕሬዝዳንቷ በጥይት ከመመታት የዳኑት የተኳሹ መሳሪያ በመንከሱ ነው ተብሏል።
ዴ ኪርችነር ከመኖሪያ ቤታቸው ውጪ ለተሰበሰቡ ደጋፊዎቻቸው ሰላምታ በመስጠት ላይ ሳሉ ነበር አንድ ግለሰብ ከሕዝቡ መካከል ወጥቶ ፊታቸው ላይ ሽጉጡን አነጣጥሮ ለመተኮስ የሞከረው።
የአርጀንቲና ፕሬዝዳንት አልቤርቶ ፈርናንዴዝ ምክትል ፕሬዝዳንቷ ፊት ላይ ተነጣጥሮ የነበረው ጦር መሳሪያ አምስት ጥይቶች ጎርሶ የነበረው ቢሆንም ቃታው ሲሳብ ግን ሳይተኩስ ቀርቷል ብለዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንቷ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ክሳቸውን በመከታተል ላይ ባሉበት በዚህ ወቅት ነው የግድያ ሙከራ የተፈጸመባቸው። የቀረበባቸውን ክስም ፖለቲካዊ አላማ የያዘ በሚል በተደጋጋሚ ውድቅ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ፖሊስ ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን የ35 አመቱ ብራዚላዊ ምክትል ፕሬዘዳንቷን ለመግደል በመሞከር በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጿል። ግለሰቡ ምክትል ፕሬዝዳንቷን ለመግደል ምን እንዳነሳሳው ለመረዳት ምርመራ እየተደረገ እንደሆነም ተገልጿል።
ትላንት ምሽት ንግግር ያደረጉት ፕሬዘዳንት ፈርናንዴዝ ጥቃቱን ያወገዙ ሲሆን በምክትላቸው ላይ የተደረገው የግድያ ሙከራ አርጀንቲና እእአ በ1983 ወደ ዲሞክራሲ ስርዓት ከተመለሰች ወዲህ ካጋጠሙ "እጅግ አሳሳቢ" ክስተቶች መካከል አንዱ ነው ብለዋል።
‘’ከምክትል ፕሬዘዳንቷ ጋር አለመስማማት እና ልዩነቶች ሊኖሩን ይችላሉ። ነገር ግን የጥላቻ ንግግሮች ሁከትን ይወልዳሉ። አመጽ እና ዴሞክራሲ ደግሞ አብረው የመሄድ እድል የላቸውም" ሲሉ ፕረዘዳንት ፈርናንዴዝ ተናግረዋል።
ፕሬዘዳንቱ አክለውም አርብ ቀን ብሔራዊ በዓል ሆኖ እንዲውል እና አርጀንቲናዊያን በሕይወት የመኖር መብትን በመደገፍ ብሎም ምክትል ፕሬዝዳንቷ ላይ የተቃጣውን ጥቃት የሚያወግዙበት ቀን እንዲሆን አውጀዋል።
በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ የተሰራጩ ምስሎች እንደሚያሳዩት ተጠርጣሪው ወደ ግለሰቧ ጭንቅላት ሽጉጡን በማነጣጠር ለመተኮስ ሲሞክር ይታያል። ከዚያም ምክትል ፕሬዘዳንቷ ጎንበስ ብለው ወደ ታች ሲመለከቱ ይታያል። ነገር ግን ምንም ጥይት አልተተኮሰም።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
እ.ኤ.አ. ከ2007 እስከ 2015 መካከል ፕሬዝዳንት የነበሩት ዴ ኪርቸነር በስልጣን ዘመናቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በተጭበረበሩ ጨረታዎች አሸናፊዎችን በመምረጥ ክስ ቀርቦባቸዋል።
አቃቤ ህግ ባቀረበባቸው ክስ መሰረት ጥፋተኛ የሚባሉ ከሆነ የ12 አመት እስራት እና እድሜ ልክ ከፖለቲካ የመታገድ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።
ሆኖም ዴ ኪርችነር የፓርላማው ጸሃፊ እና አባል በመሆናቸው ምክንያት ያለመከሰስ መብት አላቸው። እንዲሁም ቅጣት ቢጣልባቸው እንኳን በአገሪቱ ህግ መሰረት ቅጣቱ በሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ካልፀደቀ ወይም ከአንድ አመት ተኩል በኋላ በሚደረገው ምርጫ የሴኔት መቀመጫቸውን ካላጡ በስተቀር አይታሰሩም።












