'ብራዚል ከጫካ ናት እኛ ደግሞ ከአውሮፓ' ያሉት የአርጀንቲናው ፕሬዝደንት ይቅርታ ጠየቁ

የአርጀንቲናው ፕሬዝደንት አልቤርቶ ፈርናንዴዝ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአርጀንቲናው ፕሬዝደንት ብራዚላዊያን "ከጫካ ነው የመጡት እኛ ግን ከአውሮፓ" ማለታቸውን ተከትሎ ይቅርታ ጠይቀዋል።

"ሜክሲኮዎች ከሕንዶች ነው የመጡት፤ ብራዚላዊያን ከጫካ ነው የመጡት፤ ነገር ግን እኛ አርጀንቲናዊያን ከመርከቦች ነው የመጣነው፤ እኒህ መርከቦች ደግሞ ከአውሮፓ ነው የመጡት" ብለዋል አልቤርቶ ፈርንናዴዝ።

ከአንድ ሙዚቃ ላይ የተወሰደው ይህ አንቀፅ በፕሬዝደንቱ ንግግር ላይ መካተቱ ቁጣን ቀስቅሷል።

ፕሬዝደንቱ ሰዎች ማሕበራዊ ድር አምባዎች ላይ መቆጣታቸውን ተከትሎ የሃገራቸው ብዝሃነት እንደሚያኮራቸው ተናግረዋል።

ፕሬዝደንቱ ይህን ንግግር ያሰሙት የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ለጉብኝት ወደ አርጀንቲና ማቅናታቸውን ተከትሎ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ከፕሬዝደንቱ ጋር ቦነስ አይረስ ውስጥ ባደረጉት የንግድ ስብሰባ ላይ ይህ ንግግር የተሰማው።

ፕሬዝደንቱ ይህን ንግግር ያመጣሁት ከሜክሲኳዊው ገጣሚ ኦክታቪዮ ፓዝ ነው ቢሉም አስተያየት ሰጪዎች ግን ግጥሙ የተመዘዘው ከአርጀንቲናዊው ሙዚቀኛ ሊቶ ኔቢያ ሥራ ነው ብለዋል።

ፕሬዝደንቱ የአርጀንቲናዊው ሙዚቀኛ ሊቶ ኔቢያ አድናቂ እንደሆኑ ይታወቃል።

"እኔ ዩሮፒያኒስት ነው ነኝ። እኔ በአውሮፓ የሚያምን አንድ ግለሰብ ነኝ" ብለዋል ፕሬዝደንቱ።

የአርጀንቲናው ፕሬዝደንት ንግግር በብራዚል መገናኛ ብዙሃን አየር ላይ እንዲውል የተደረገ ሲሆን ቀኝ ዘመሙ የብራዚል ፕሬዝደንት ጃይር ቦልሶናሮ የመልስ ምት እንዲሰጡ አድርጓቸዋል።

ቦልሶናሮ ወደ ትዊተር ገፃቸው አቅንተው ከጥንታዊ የብራዚል ሕዝቦች ጋር ሆነው የተነሱትን ፎቶ ለጥፈዋል።

ከፎቶው ጋር አንዲት ቃል አብረው የለጠፉ ሲሆን ቃሉ "ሴልቫ" ወይም ጫካ ይላል።

የኮንግረስ አባል የሆኑት የቦልሶናሮ ልጅ አድዋርዶ ቦልሶናሮ የአርጀንቲናውን ፕሬዝደንት አስተያየት "ዘረኛ" ሲሉ ገልፀውታል።

"እየሰጠመ ያለው መርከብ የአርጀንቲና ነው" ሲሉ የአርጀንቲናን ምጣኔ ሃብት በመንካት በትዊተር ገፃቸው ፅፈዋል።

ፕሬዝደንቱ ከደረሰባቸው ወቀሳ በኋላ "እኔ ማንንም ላስከፋ አልፈለግኩም፤ በየትኛውም መንገድ የተከፋ ካለ ይቅርታዬን እንኩ" ብለዋል።