ትራምፕ ትዊተርን ያገዱት የናይጄሪያው ፕሬዝደንት ቡሃሪን አደነቁ

ቡሃሪ እና ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የናይጄሪያ መንግሥት ትዊተር የተሰኘው ማህበራዊ ድር አምባን በማገዳቸው አድናቆት ችረዋል።

ትዊተር የሙሃሙዱ ቡሃሪን የትዊተር መልዕክት ከገፁ ላይ ከሰረዘ በኋላ ነው ናይጄሪያ ውስጥ ጥቅም ላይ እንዳይውል የታገደው።

"ራሳቸው ክፉ ሆነው እነሱ ማናቸው እና ነው ጥሩ እና መጥፎውን የሚነግሩን?" ብለዋል ትራምፕ በለቀቁት መግለጫ።

ትዊተርና ፌስቡክ "ነፃና ግልፅ ንግግርን" የማያበረታቱ ከሆነ ሌሎች ሃገራትም እንዲያግዷቸው ጥሪ አቅርበዋል።

ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካዋ መንግሥት መናገኛ ካፒቶል ሂል ላይ ደጋፊዎቻቸው ካደረሱት ጥቃት በኋላ ከሁለቱ ድር አምባዎች መታገዳቸው አይዘነጋም።

ከጥቃቱ በፊትና በኋላ ትራምፕ የለቀቋቸው መልዕክቶች አመፅ አነሳሽ ናቸው ተብለው ነው የታገዱት።

ትዊተር ያኔውኑ ትራምፕን እስከ ወዲያኛው ድረስ ወደ ድሩ ብቁ እንዳይሉ ሲያግዳቸው ፌስቡክ ግን ባለፈው ሳምንት ነው የኢንስታግራም ገፃቸው ጭምር ለሁለት ዓመት ጥቅም ላይ እንዳይውል ያገደው።

የትራምፕ መግለጫ ምን ይላል?

"ፕሬዝደንትሽን በማገዳቸው ትዊተርን ያገድሽው ሃገረ ናይጄሪያ እንኳን ደስ ያለሽ" ይላል ማክሰኞ ዕለት የለቀቁት መግለጫ።

ትራምፕ ሥልጣን ላይ እያሉ ፌስቡክን ሊያግዱ ይገባ እንደነበር መግለጫቸው ጠቆም አድርገዋል።

ነገር ግን የኩባንያው ባለቤት ማርክ ዛከርበርግ "አስር ጊዜ እየደወለ እንዲሁም ወደ ዋይት ሃውስ እየመጣ በጣም ጥሩ መሪ እንደሆንኩ ይነግረኝ ነበር" ብለዋል።

ትራምፕ አክለው አንደ አዲስ ማህበራዊ ድር አምባ "መጥቶ ሁሉን ይቆጣጠራል' ሲሉ ቢናገሩም ስም ግን አልጠቀሱም።

45ኛው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ከፌስቡክና ትዊተር ከታገዱ ወዲህ ትኩረት ለማግኘት ብዙ ጥረዋል።

ባለፈው ወር መልዕክቶቻቸውን ለማስተላለፍ ሲሉ የከፈቱት ድረ-ገፅ ብዙ ሰው ሊጎበኘው ባለመቻሉ ምክንያት ተዘግቷል።

ናይጄሪያ ትዊተርን ለምን አገደች?

የናይጄሪያ ባለሥልጣናት ድር አምባው "የተሳሳተና ሃሰተኛ መረጃ ስለሚሰራጭበት የሃገሪቱን ህልውና የሚፈታተን ነው" ይላሉ።

የናይጄሪያው ፕሬዝደንት ሙሃሙዱ ቡሃሪ ከአራት አስርት ዓመታት በፊት የተደረገውን የናይጄሪያ እርስ በርስ ጦርነት ዋቢ አድርገው ለመገንጠል የሚያስቡ ኃይሎችን ያስጠነቀቁበት የትዊተር መልዕክታቸው እንዲጠፋ ይደረጋል።

ከዚህ በኋላ ነው የናይጄሪያ መንግሥት በርካታ ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ያሉት ትዊተር መታገዱን የጠቆመው።

የናይጄሪያ መረጃ ሚኒስትር ላይ ሞሐመድ ናምዲ ካኑ የተሰኘው የመገንጠል ሐሳብን የሚያቀነቅነው ቡድን መሪ ድር አምባውን ይጠቀማል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ይህ ሰው ያለ ምንም ተጠያቂነት ትዊተርን ተጠቅሞ በደቡብ ምስራቅ በኩል መንግሥት ጥቃት እያደረሰ ነው" ብለዋል ሚኒስትሩ።

የናይጄሪያ ሞባይል ኔትወርክ አቅራቢዎች ድርጅት አልቶን መንግሥት ይህን ድር አምባ እንዲዘጋ እንዳዘዘው ይናገራል።

አልፎም የመንግሥት ሕግጋት ጥሶ ትዊተርን ሲጠቀም የተገኘ ሰው ሊቀጣ እንደሚችል ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች ተሳባስበው በምዕራብ አፍሪካ ክልላዊ ፍርድ ቤት መንግሥትን ከሰዋል።

ታዋቂ ፖለቲከኞችን ጨምሮ በርካታ ናይጄሪያዊያን እንዲሁም የዜና እና የእምነት ተቋማት 'ቪፒኤን' ተጠቅመው አሁንም ትዊት ማድረጋቸው ቀጥለዋል።

ትዊተር እገዳው "እጅግ አሳሳቢ ነው" ብሏል።