አሜሪካዊቷ መነኩሲት ለቁማር በሚል ከፍተኛ ገንዘብ መስረቃቸውን አመኑ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በካሊፎርኒያ የሚኖሩ አንዲት መነኩሲት ይሰሩበት ከነበረው የካቶሊክ ትምህርት ቤት ለቁማር ለመክፈል በሚል ከፍተኛ ገንዘብ መመዝበራቸውን የአሜሪካ አቃቤ ህግ አስታውቋል።
የ79 አመቷ ሜሪ ማርጋሬት ክሩፐር በአስር አመትም ውስጥ 835 ሺህ ዶላር ሰርቀዋል ተብሏዕል።
በወቅቱም የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር እንደነበሩም ተገልጿል።
በአሁኑ ወቅት የ40 አመት እስርም ይጠብቃቸዋል።
በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ መነኩሲትዋ ያለባቸውን የቁማር ብድር ለመክፈል ገንዘቡን መስረቃቸውን ተናግረዋል ተብሏል።
መነኩሲትዋ ሴይንት ጄምስ የተሰኘውን የካቶሊክ ትምህርት ቤት ለ28 አመታት ያህል አገልግለዋል።
ባለስልጣናቱ እንደሚሉት ጡረታ ሊወጡ አስር አመት ባለው ጊዜ መስረቅ መጀመራቸውን ነው። መነኩሲትዋ ጡረታ የወጡት ከሶስት አመታት በፊት ነው።
"በሴይንት ጄምስ ያሉ አገልጋዮች፣ የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ በመነኩሲትዋ ድርጊት አዝኗል እንዲሁም ደንግጧል። የአካባቢው ተወካይ ኤጲስ ቆጶስም ከባለስልጣናቱ ጋር በወንጀል ምርመራው ሙሉ በሙሉ ተባብረዋል" በማለት የሎስ አንጀለስ ኤጲስ ቆጶስ በመግለጫቸው ማስፈራቸውን ሎስ አንጀለስ ታይምስ ዘግቧል።
የመነኩሲትዋ ጠበቃ በበኩላቸው ደንበኛቸው በድርጊታቸው መፀፀታቸውንና ያለባቸው የአዕምሮ ጤንነት ሁኔታ መጓደል ውሳኔያቸውን በደንብ እንዳያጤኑ እክል ፈጥሯል ነው ማለቱን ሎስ አንጀለስ ታይምስ አስነብቧል።
የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር በነበሩበትም ወቅት ሜሪ በትምህርት ቤቱ ተቀጥረው የሚሰሩ መነኩሴዎች ወጪያቸውን ለመሸፈን በሚል በትምህርት ቤቱ የተቋቋመ የቁጠባ ገንዘብ እንዲሁም የብድር ማህበርን በበላይነት ይቆጣጠሩም እንደነበር ከአሜሪካ አቃቤ ህግ የወጣው መግለጫ ያሳያል።
አቃቤ ህግ ከመነኩሲትዋ ጋር የስምምነት ውል የሚፈራረም ሲሆን መነኩሴዋ የእምነት ቃላቸውን በመስጠት በሁለት ክሶች ብቻ ተጠያቂ በመሆን የእስር ጊዜያቸው ቀለል ሊልላቸው እንደሚችል ተገልጿል።












