"የዓለማችን መልካሙ ዳኛ" በመባል የሚታወቁት ፍራንክ ካፕሪዮ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

ፍራንክ ካፕሪዮ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዳኛ ፍራንክ ካፕሪዮ

በዩናይትድ ስቴትስ እና በሌሎች የዓለም ክፍሎች በችሎት ውስጥ በሚያሳዩት ርህራሄ እና ደግነት የሚታወቁት ዳኛ እና የማኅበራዊ ሚዲያ ኮከብ ፍራንክ ካፕሪዮ በ88 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ቤተሰቦቻቸው ገለፁ።

በይፋዊ የኢንስታግራም ገጻቸው ላይ የጣፊያ ካንሰር መያዛቸው ከታወቀ በኋላ ባደረባቸው ሕመም መሞታቸው የተገለፈ ሲሆን "በመልካምነቱ" እና "በሰዎች መልካምነት ላይ ባለው የማያወላውል እምነት" ይታወሳል ሲሉ ቤተሰቦቻቸው ጽፈዋል።

ልጃቸው ዴቪድ ካፕሪዮ አድናቂዎቻቸው ለሰጧቸው ፍቅር እና ድጋፍ አመስግኖ ሰዎች በአባቱ ትውስታ ውስጥ ሆነው "ትንሽ ደግነትን ለሌሎች እንዲያጋሩ" ጠይቋል።

በችሎት ውስጥ ባላቸው ርህራሄ እና ቀልድ የሚወደዱት ዳኛ ካፕሪዮ፣ የችሎት ውሏቸውን እና የፍርድ ሂደቱን የሚያሳዩት ተንቀሳቃሽ ምሥሎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ዕይታዎችን አግኝተዋል።

ከዚህም በመነሳት "የዓለማችን መልካሙ ዳኛ" የሚል ስያሜን አግኝተዋል።

3.4 ሚሊዮን ተከታዮቹ ባሉት የዳኛ ካፕሪዮ የኢንስታግራም ገጽ ላይ በሰፈረው መልዕክት "ስፍር ቁጥር ለሌላቸው የደግነት ተግባራት ምክንያት" መሆናቸው ተጠቅሷል።

መግለጫው አክሎም "የእርሱ ፈገግታ የሞላበት መልካምነት፣ ቀልድ እና ደግነት በሚያውቁት ሁሉ ላይ የማይጠፋ አሻራ ጥሎ አልፏል" ብሏል።

ዳኛ ካፕሪዮ በትውልድ ከተማቸው በፕሮቪደንስ ሮድ አይላንድ በቲቪ የችሎት ውሏቸው ከመተላላፉ በፊት በሺዎች የሚቆጠሩ ጉዳዮችን ዳኝተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

'ኮት ኢን ፕሮቪደንስ' የተሰኘውን የቴሌቪዥን ሾውን የሚያሠራጨው ኩባንያ፣ ዴምባር ሜርኩሪ ዳኛውን "ልዩ የርህራሄ ተምሳሌት እና መተሳሰብ የተሞላበት አቀራረብ" የነበራቸው መሆናቸውን ገልጿል።

"በጣም እንናፍቀዋለን" ሲሉ የኩባንያው ፕሬዝዳንት የሆኑት ሞርት ማርከስ እና ኢራ በርንስታይን በጋራ በሰጡት መግለጫ ላይ ገልጸዋል።

ኮት ኢን ፕሮቪደንስ ( Caught in Providence) የተሰኘው የቴሌቪዥን ትርዒት ለዕይታ በሚበቃበት ወቅት ለሦስት ኤሚዎች ታጭቶ የነበረ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ዳኛ ካፕሪዮ ለብቻቸው በሁለት ዘርፎች ታጭተዋል።

በችሎት ላይ የሚያሳዩት ያልተለመደ ርህራሄ፣ በፍርድ ሂደቱ ወቅት ልጆችን ወደ መቀመጫቸው ጋብዘው አብረዋቸው እንዲቀመጡ እና "አነስተኛ ዳኝነታቸውን" እንዲሰጡ ሲያደርጉ የሚያሳዩ አጫጭር ቪዲዮዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በሰፊው ተጋርተው ይገኛሉ።

ጥርሳቸውን ሲቦርሹ፣ መጽሐፋቸውን ሲፈርሙ እና የራሳቸውን ቪዲዮዎች ሲመለከቱ የሚያሳዩ የቲክቶክ ቪዲዮዎች ብቻ ከ5 ሚሊዮን በላይ ተመልካች አግኝተዋል።

በአውሮፓውያኑ 2019 በሰጡት ቃለ መጠይቅ ላይ ዳኛ ካፕሪዮ የፍርድ ቤት ውሎው "በጣም አስደሳች የሆነ የሮድ አይላንድን ሕይወት ያሳያል እንዲሁም ሰዎች በአገር አቀፍ ደረጃ የሚያጋጥሟቸውን ተመሳሳይ ጉዳዮችን ያዩበታል" ብለው ነበር።

በ2023 የጣፊያ ካንሰር እንዳለባቸው ከታወቀ በኋላ ዳኛ ካፕሪዮ "በምችለው መጠን ለመታገል ሙሉ በሙሉ ዝግጁ ነኝ" በማለት ተከታዮቻቸው ለሚሰጧቸው ድጋፍ አመስግነዋል።

ዳኛ ካፕሪዮ በመጨረሻው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በለጠፉት መልዕክት በሕክምናው ላይ "ችግር" ካጋጠማቸው በኋላ ወደ ሆስፒታል መግባታቸውን አስታውቀው ተከታዮቻቸው እንዲፀልዩላቸው ጠይቀዋል።

ዳኛ ካፕሪዮ ከባለቤታቸው ጆይስ ካፕሪዮ ጋር ወደ 60 ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ የኖሩ ሲሆን፣ አምስት ልጆችን ወልደው ሰባት የልጅ ልጆች እንዲሁም የሁለት ልጆች ቅድመ አያት ለመሆን በቅተዋል።