የአሜሪካ ጊዜያዊ አፈ ጉባኤ ሁለት ከፍተኛ ዲሞክራቶችን ከቢሯቸው አባረሩ

ናንሲ ፔሎሲ እና የረዥም ጊዜ ምክትላቸው ስቴኒ ሆየር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከ35 ዓመታት በላይ በምክር ቤት ያገለገሉት የቀድሞዋ አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ እና የረዥም ጊዜ ምክትላቸው ስቴኒ ሆየር በአሜሪካው ካፒቶል ያላቸውን ቢሮዎች እንዲለቁ በምክር ቤቱ ጊዜያዊ አፈጉባኤ ፓትሪክ ማክሄነሩ ታዘዙ።

ሁለቱም የምክር ቤት አባሎች የቢሯቸው ቁልፎች "እንደሚቀየሩ" ትናንት ረቡዕ መስከረም 23/2016 ዓ.ም ተነግሯቸዋል።

ውሳኔው የተላለፈው ማክሰኞ ኬቨን ማካርቲ ከምክር ቤቱ አፈ ጉባኤነት ከተባረሩ እና ከፍተኛ ተዓማኒነት ያላቸው ማክሄንሪ በጊዜያዊነት ከተሾሙ በኋላ ነው።

በአሁኑ ጊዜ በአመራር ላይ የሌሉት ፔሎሲ ውሳኔውን “ከተለመደው ባህል የራቀ” ሲሉ ተችተዋል።

ሪፐብሊካኑ የምክር ቤት አባል ጋሬት ግሬቭስ ቢሯቸውን ለማካርቲ እንደሰጡ አስታውቀዋል። ይህ ቢሮ የቀድሞ አፈ ጉባዔ ነበር ብለዋል።

ባለፈው ዓመት በተካሄደው ምርጫ ሪፐብሊካኖች በጠባብ ምርጫ የምክር ቤቱን የበላይነት ስፍራ መያዛቸውን ተከትሎም ናንሲ ፔሎሲ ከስልጣናቸው መልቀቃቸው ይታወሳል።

በአሁኑ ወቅት ከስልጣን የተሰናበቱት ኬቨን ማካርቲም ከረዥም ሂደት በኋላም እሳቸውን በመተካት አፈ ጉባኤ ሆነዋል።

"እሷ እና ሌሎች ዴሞክራቶች በፍጥነት የቀድሞ የሚባል አፈ-ጉባዔ እንዲፈጠር ስላደረጉ ራሷን ከዛ ቢሮ አግልላለች… ይህ ዴሞክራቶች እና አፈ-ጉባኤ ፔሎሲ ያንን ቢሮ ለማካርቲ ለመስጠት የወሰኑት ውሳኔ ነው" ብለዋል።

ፔሎሲ ውሳኔውን በመቃወም ማክሰኞ መግለጫ አውጥተዋል።

"አዲሱ የሪፐብሊካን አመራር ሊያደርጋቸው የሚገቡ ወሳኝ ውሳኔዎችን ሁላችንም በጉጉት እየጠበቅን ባለንበት ወቅት በአዲሱ አፈ-ጉባኤ ከተወሰዱት የመጀመሪያ እርምጃዎች አንዱ በካፒቶል የሚገኘውን ቢሮዬን በአስቸኳይ እንድለቅ ትዕዛዝ ተሰጠኝ" ብለዋል።

"በሚያሳዝን ሁኔታ የጓደኛዬን ሃዘን ለመካፈል በካሊፎርኒያ ስለምገኝ ንብረቶቼን እንኳን ማውጣት አልቻልኩም።"

በመሪነት ሚና ላይ ላልሆኑ የምክር ቤት አባላት በካፒቶል ህንጻ ውስጥ ቢሮ ማግኘታቸው ያልተለመደ ቢሆንም፤ ፔሎሲ እና ሆየር ቢሮ ነበራቸው።

ፔሎሲ በመግለጫቸው በተለመደው አሠራር መሠረት ለሪፐብሊካኑ የቀድሞ መሪ አፈ ጉባኤ ወደ ስልጣን ሲመጡ ቢሮ መስጠታቸውን አክለዋል።

ሁለቱም ዲሞክራቶች በተወካዮች ምክር ቤቱ ህንጻዎች በሚገኘው መደበኛ የሥራ ቦታቸውን ውስጥ ይዘው ይቆያሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የቀድሞ አመራሮቹን ከቢሮ የማስወጣት ጉዳይ ለመጀመሪያ ጊዜ የዘገበው ፖሊቲኮ እንዳስነበበው ከሆነ የፔሎሲ ዕቃዎች ማክሰኞ አመሻሽ ላይ በተተኪዋ ሃኪም ጄፍሪስ በሠራተኞች ድጋፍ ለመውሰድ በሚያመች ሁኔታ ታሽገዋል።

ማካርቲን ከአፈ-ጉባኤነት ለማንሳት የተሰጠው ድምጽ ሁለት ሰዓት ሳይሞላው ነበር ጊዜያዊው አፈ ጉባኤ ለፔሎሲ ኢሜይል በመላክ ቢሮውን ለሌሎች ሊሰጥ እንደሆነ የነገሯቸው።

ውሳኔውን ማን እንደወሰነው ግልጽ አይደለም።

ምንም እንኳን ፔሎሲ ለውሳኔው ጊዜያዊ አፈ-ጉባዔውን ተጠያቂ ቢያደርጉም፤ እንደሲኤንኤን እና ኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ ከሆነ ማካርቲ ከድርጊቱ ጀርባ እንዳሉ እና ቀደም ሲል ፔሎሲ ሲጠቀሙ የነበረበትን ቦታ ሊረከቡ እንዳሰቡ ዘግበዋል።

ማክሄንሪ፣ ማካርቲም ሆኑ በሪፐብሊካን የሚመራውና የቢሮ ቦታን የሚደለድለው የምክር ቤት አስተዳደር ኮሚቴ በጉዳዩ ላይ እስካሁን አስተያየት አልሰጡም።

ማካርቲ በመተማመኛ ድምፅ በማጣት የተባረሩ በታሪክ የመጀመሪያ የአሜሪካ አፈ ጉባኤ ሆነዋል።

የ58 ዓመቱ ማካርቲ ቦታቸውን እንዲለቁ 8 ሪፐብሊካኖች ከዲሞክራት አባላት ጎን ተሰልፈው ድምጽ ሰጥተዋል።

ከድምጽ አሰጣጡ በኋላ በሰጡት ረዥም ጋዜጣዊ መግለጫ ማካርቲ በድጋሚ ለአፈ ጉባኤነት እንደማይወዳደሩ ተናግረዋል።

አፈ-ጉባኤ ሲሆኑ የመልቀቅ ጥያቄ ካጋጠማቸው ፔሎሲ “ሁሌም ከጎናቸው እንደሚሆኑ” ቃል ገብተውልኝ ነበር ሲሉም አክለዋል።

ፔሎሲ በተለይ በማክሰኞ ዕለት ቢገኙም ከድምጽ አሰጣጡ ቀደም ብለው ወጥተዋል። ፓርቲያቸውም ማካርቲንን ለማዳን ጣልቃ አልገባም።

ድምጽ ቢሰጡም ማካርቲን ከስልጣን ለማውረድ ድምጽ እንደሚሰጥ አሳውቀዋል።

የ47 ዓመቱ ማክሄንሪ የማካርቲ የቅርብ አጋር ሲሆኑ በዘጠኝ ወር የአፈ ጉባኤነት ዘመናቸውም ቁልፍ ሠው ነበሩ።