በምሥራቅ ኢትዮጵያ ጎርፍ ሊወስደው የነበረን ሕጻን ለማዳን የተፈጸመ ሰብአዊነት እና ጀግንነት

አብዲ ቱፋ

ዕለቱ ማክሰኞ መስከረም 15/2016 ዓ.ም ነበር።

ምሥራቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ሐረርጌ ሂርና ላይ ዝናብ በተከታታይ ለሦስት ሰዓት ሲዘንብ ቆይቶ ኃይለኛ ጎርፍ ፈጠረ።

በአካባቢው የሚኖር አንድ የ10 ዓመት ሕጻን ልጅ ደግሞ የሚጠብቃቸው ፍየሎችን ለመመለስ ሲሞክር በድንገት በጎርፍ ተከበበ።

ይህ ደራሽ ጎርፍ በአካባቢው ያገኘውን ድንጋይ እና ግንድ እያገላበጠ ይነጉዳል።

የልጁን በከባድ ጎርፍ መከበብ የተመለከተው የአካባቢው ማኅበረሰብም በጩኸት አካባቢውን አናወጠው።

በዚያን ሰዓት ዝናብ ትንሽ ጋብ ብሎ ነበር።

ቦታው ከሐረር ወደ አዲስ አበባ በሚወስደው ዋና አውራ መንገድ ዳር ስለነበር በሚንደረደር ጎርፍ የተከበበውን ልጅ የሚያዩ መኪኖች በሙሉ በስፍራው ላይ ቆመው ነበር።

በጎርፍ የተከበበው ሕጻን የቆመበት ቦታ ቀስ በቀስ በውሃ እየተሸፈነ ሄደ።

እስከዚያ ጊዜ ድረስ ከልጁ ቤተሰብም ሆነ፣ ጩኸት ሰምቶ ከተሰበሰበው ሕዝብ መካከል ልጁን ለማዳን ወደ ውሃው ለመግባት የደፈረ አልነበረም።

የቆመው ሕዝብ ሁሉ ጮሆ ያጯጩሀል። ታዳጊውን የከበበው ውሃው ደግሞ በፍጥነት ከፍታውን እየጨመረ ሄደ።

አብዛኞቹ ተስፋ በመቁረጥ ስሜት ውስጥ ሆነው ጎርፉ ልጁን ይዞት ሲሄድ ለማየት ቆመዋል።

በዚህ ጊዜ ነበር ከሐረር ወደ አዲስ አበባ የሚሄድ አውቶብስ ውስጥ የነበረ ወጣት የሚያስግርም እርምጃ የወሰደው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አብዲ ቱፋ ይባላል። የመስቀል በዓልን ሰላሌ ከሚገኙት ቤተሰቦቹ ጋር ለማክበር ነበር ወደ አዲስ አበባ የሚሄድ አውቶቡስ ውስጥ የተሳፈረው።

አብዲ በሐረር ከተማ ውስጥ የግል ሥራ ላይ የተሰማራ መሆኑን ይናገራል።

በዕለቱ ስለነበረው ሁኔታ ለቢቢሲ ሲናገር “በአውቶቡስ እየሄድኩ ነበር። ሂርና ስንደርስ ከእንቅልፍ ነቃሁ እንጂ ከዚያ በፊት ተኝቼ ነበር። ከእንቅልፌ ስነቃ አንድ ሕጻን ልጅ በውሃ ተከብቦ ሕዝብ ከማዶ ቆሞ ሲጮህ ሰማሁ” ብሏል።

“በመስኮት ወደታች ስመለከት እኔ እና ሕጻኑ ልጅ ዐይን ለዐይን ተያየን። ልጁ በጎርፍ ሊበላ ነው። ሊያተርፈው ወደ ውሃው የሚገባ ሰው የለም። ያን ጊዜ ነው በራሴ ላይ የወሰንኩት” ይላል።

አብዲ በጎርፍ ተከቦ መውጫ አጥቶ በጭንቅ ውስጥ የነበረውን ታዳጊ ሁኔታን በተመለከተ ጊዜ ሹፌሩን ‘አቁምልኝ’ በማለት በበር በኩል ለመውጣት ጊዜ አልነበረውም።

“መንገዱ ተዘጋግቶ ስነበር አውቶቡሱ በቀስታ ነበር የሚሄደው። እኔም በፍጥነት አጠገቤ የነበረውን የመኪናውን መስኮት በመክፈት ዘልዬ ወረድኩ። ሮጬም ውሃው ውስጥ ገባሁ።”

በውሃው ሊበላ የነበረውን ትንሽ ልጅ በማየቱ ስሜቱን መቆጣጠር እንዳቃተው የሚናገረው አብዲ፣ በኪሱ ውስጥ ስልክ እና መታወቂያ እንዲሁም ገንዘብ እንደነበረው እንኳን ለማሰብ ጊዜ አልነበረውም።

ከነሙሉ ልብሱ ውሃ ውስጥ ዘሎ በመግባት ልጁ ጋር ደረሰ።

“ልክ ልጁ ጋር ስደርስ ጎርፉ በኃይል ጨመረ። ከዚያ ሁለታችንንም ገፍቶ ወሰደን። ውሃ ወደ ልጁ አፍ እንዳይገባ አንገቱን ቀና በማድረግ ወደ ዳር ለመውጣት ጣርኩኝ” ይላል።

ጎርፉ እርሱን እና ልጁን ወደ 100 ሜትር ያህል እየገፋ ቢወስዳcውም ካለምንም ጉዳት ታዳጊውን ወደ ዳር በማውጣት ሕይወቱን ለመታደግ ችሏል።

በከባድ ጉልበት እና ፍጥነት የሚንደረደረው ጎርፉ ድንጋዮች እና ግንዶች ተሸክሞ ይጓዝ ነበር።

ልጁን ካወጣ በኋላ ራሱ ሊወጣ ጥረት በሚያደርግበት ወቅት ጎርፉ አብዲን ከድንጋይ እና ከእንጨት ጋር አጋጨው።

በዚህም የተነሳ አብዲ የአካል ጉዳት ደረሰበት።

በዚህም እግሩ ከጉልበቱ በታች ተሰበረ። የወገብ እና ሽንጥ አጥንቱ ላይም ጉዳት ደረሰበት።

“እግሬ ከጉልበቴ በታች ተሰብሯል። ወገቤ እና ሽንጤ ላይም አጥንቴ ተጎድቷል። አሁን እየታከምኩ ነው። እግሬ አሁን እየተሻለኝ ነው። ወገቤ ላይ የደረሰው ጉዳት ግን ከባድ ነው” ይላል።

አብዲ ቱፋ

አብዲ ልጁን ለማዳን ወስኖ በወሰደው እርምጃ ለጉዳት ቢዳረግም፣ የታዳጊውን ሕይወት በማትረፉ ግን በጣም ደስተኛ መሆኑን ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ባደረገ ወቅት ተናግሯል።

“ትልቁ ነገር ሕጻኑን ማዳኔ ነው። እኔ ደፍሬ ወደ ውሃው ባልገባ ኖሮ፣ ይህ ሕጻን ልጅ በጎርፍ ይወሰድ ነበር። ልጁ ከተረፈ እኔ ብሞት እንኳ ምንም አልነበረም። ጉዳት ቢደርስብኝም እንኳ በሠራሁት ሥራ በጣም ደስታ ይሰማኛል” ይላል።

ታዳጊውን ከጎርፍ አደጋ ያዳነው ወጣት በአሁኑ ሰዓት ሕክምና እየተከታተለ እና በልጁ ቤተሰቦች እየተረዳ ይገኛል።

አቶ ናሲር ሂብሮሼ ከጎርፉ የተረፈው ልጅ ቤተሰብ ሲሆኑ፣ በአሁኑ ጊዜ አብዲን በቤታቸው እየተንከባከቡት ነው።

እርሳቸውም አብዲን ‘እግዚአብሔር የላከልን መልዕክተኛ’ ሲሉ ይገልጹታል።

አብዲ በሠራው የጀግንነት ተግባር የልጃቸው ሕይወት በመትረፉ በጣም እንዳስደሰታቸው አቶ ናሲር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“በዚህ ዘመን እንዲህ ዓይነት ሰው የለም። የአካባቢው ሰው ቆሞ እየጮኸ ባለበት ሰዓት ነው ይህ ወጣት በራሱ ላይ ወስኖ ልጁን ለማዳን የቻለው። አብዲ ለእኛ ሕጻኑን ለማዳን ከእግዚአብሔር እንደ የተላከ መልዕክተኛ ነው የምናየው” ይላሉ።

የታዳጊው ቤተሰብ በአሁኑ ጊዜ አብዲ ሕክምና እየተከታተለበት ወደሚገኝበት ሆስፒታል በማመላለስ እያሳከሙት እና ቤታቸው ውስጥ እንክብካቤ እያደረጉለት እንዳለ ይናገራሉ።

ሰላሌን በሃሳቡ ይዞ እየተጓዘ የነበረው አብዲ፣ ያደረገው ጀግንነት የተሞላበት ተግባር በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መነጋገርያ ሆኗል።

ይኹን እንጂ አብዲ ላይ የደረሰው ጉዳት ከባድ ከመሆኑ የተነሳ፣ በአሁኑ ጊዜ በአራት ሰዎች ተደግፎ ነው ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሰው።

አቶ ናሲር አብዲ ሙሉ በሙሉ እስከሚሻለው ድረስ አስፈላጊውን እንክብካቤ ሁሉ እንደሚያደርጉለት እና ሲሻለው ደግሞ የጀግና ሽኝት እንደሚያደርጉለት ተናግረዋል።

“አብዲ ከጀግና የሚበልጥ ጀግና ነው። ባይሆን ኖሮ ልጃችን ሞቶ ነበር። በአሁኑ ሰዓት አብዲን እንደ ታላቅ ልጃችን እያየነው ነው” ይላሉ።

አብዲ ከደረሰበት ጉዳት እንዲያገግም ከሠራው በጎ ተግባር የተነሳ ሰዎች ከአገር ውስጥ እና ከባሕር ማዶ ጭምር ድጋፍ እያደረጉለት እንደሆነ አቶ ናሲር ይናገራሉ።