በዋግ ኽምራ እና በሰሜን ጎንደር ዞኖች በተከሰተው ድርቅ ቢያንስ የ34 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ባለሥልጣናት አስታወቁ

በድርቁ የጠፋ ሰብል ላይ ተቀመጠ ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, Waghimra Communicatio

የምስሉ መግለጫ, በዋግ ኽምራ፣ሰሃላ ሰየምት ወረዳ ብቻ በዘር ተሸፍኖ የነበረ ከ8 ሺህ 13 ሔክታር በላይ መሬት ከጥቅም ውጭ ሆኗል።

በአማራ ክልል በሚገኙት የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር እና የሰሜን ጎንደር ዞኖች በተከሰተው ድርቅ ቢያንስ የ34 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የዞኑ ባለሥልጣናት ተናገሩ።

የዞኖቹ የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ባለፈው ዓመት ይጠበቅ የነበረው ዝናብ ባለመዝነቡ በተከሰተው ድርቅ ከጠፋው የሰው ሕይወት ባሻገር ከ54 ሺህ በላይ የቤት እንስሳት ሞተዋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ ሰላምይሁን ሙላት፣ በዞኑ ከሚገኙ 11 ወረዳዎች ውስጥ ስድስቱ በከፊልና ሙሉ በሙሉ ለድርቅ ተጋልጠዋል፤ ወደ 34 ሺህ 200 ሔክታር መሬት ላይ የተዘራ ሰብልም ወድሟል ብለዋል።

በዞኑ ከሚገኙት ወረዳዎች ውስጥ ጃናሞራ ለከፋ ድርቅ የተጋለጠ ሲሆን በጠለምት፣ በበየዳ እንዲሁም በምዕራብ እና ምሥራቅ ጠለምት ወረዳዎች አካባቢም ሲጠበቅ የነበረው ዝናብ አልዘነበም።

“በጃናሞራ ካሉት ቀበሌዎች በ13ቱ ምንም ዓይነት ዝናብ የለም። ግንቦት መጀመሪያ ለተዘራ ሰብል ምንም ዓይነት ዝናብ አለመዝነቡ የተለየ ክስተት ነው” ብለዋል።

በዚህም ምክንያት ወደ 452 ሺህ ዜጎች የዕለት ምግብ ጠባቂዎች የሆኑ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 202 ሺህ የሚሆኑት አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አቶ ሰላምይሁን ተናግረዋል።

ከድርቁ ጋር በተያያዘ እንደ ኮሌራ፣ አተት እና እከክ ያሉ ወረርሽኞች ተከስተዋል።የመድኃኒት እና የሕክምና አቅርቦቱም ከዞኑ አቅም በላይ ሆኗል።

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳዳር ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት አስተባባሪ ምህረት መላኩ በበኩላቸው፣ በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ዝናብ ዘግይቶ መጀመሩን ገልጸው፣ በአብዛኞቹ ወዲያው ነው የቆመው ብለዋል።

አስተባባሪው እንዳሉት በተለይ በድርቁ ክፉኛ በተጎዳው ሰሃላ ሰየምት ወረዳ በሚገኙ 13 ቀበሌዎች ዝናብ የዘነበው ከሐምሌ 28 እስከ ነሐሴ 8/2015 ዓ.ም. ብቻ ነው።

በዚህም በዘር ተሸፍኖ የነበረ ወደ 8 ሺህ 13 ሔክታር በላይ መሬት ከጥቅም ውጭ ሆኗል።

አካባቢው ሰፊ የእንስሳት ሃብት ያለበት እና ነዋሪዎችም በከፊል አርብቶ አደር ናቸው የሚሉት አቶ ምህረት፣ በድርቁ ሳቢያ ቢያንስ የሁለት ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን፣ ወደ 1236 የሚሆኑ በግ፣ ፍየል፣ የጋማ እና የቀንድ ከብቶች መሞታቸውን ተናግረዋል።

በዞኑ በሚገኙት ዝቋላ እና አበርገሌ ወረዳዎችም ድርቁ ተከስቷል። ከዚህም በተጨማሪ በዳሃና ወረዳ ያጋጠመው በረዶ እና ጎርፍ የበርካታ አርሶ አደሮችን እርሻ አውድሞባቸዋል።

በዚህም ምክንያት በዞኑ ውስጥ የሚገኙ ከ123 ሺህ በላይ ሰዎች አስቸኳይ የዕለት ምግብ ድጋፍ ጠባቂ ሆነዋል።

የእርዳታ አቅርቦት

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዞኖቹ ባለሥልጣናት እንዳሉት እስካሁን በአካባቢዎቹ የቀረበ እዚህ ግባ የሚባል እርዳታ የለም።

በዞኑ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እርዳታ የማፈላለግ ሥራ ተሰርቶ እንደነበር የሚናገሩት የሰሜን ጎንደር ዞን ባለሥልጣን ሰላምይሁን፣ ከክልሉ ከቀረበው 1500 ኩንታል በቆሎ በስተቀር ያገኙት እንደሌለ ተናግረዋል።

“የበቆሎ ድጋፉ ለ10 ሺህ ሰዎች እንዲደርስ ጥረት ቢደረግም በቂ አይደለም” ብለዋል።

በመሆኑም አስቸኳይ ድጋፍ ማቅረብ ካልተቻለ የከፋ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችል ባለሥልጣኑ አስጠንቅቀዋል።

እስካሁን ከረሃብ እና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ቢያንስ የ32 ሰዎች ሕይወት ማለፉን በመግለጽም፣ የክልል እና የፌደራል መንግሥት እንዲሁም የረድኤት ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በእነዚህ አካባቢዎች እርዳታ ያቀርቡ የነበሩ ድርጅቶች ድጋፍ በማቋረጣቸው እንዲሁም በክልሉ ውስጥ ባለው የፀጥታ ችግር እና የተፈናቃዮች ቁጥር መበራከት ቀውሱን እንዳባባሰው የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ጽ/ቤት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ምህረት ተናግረዋል።

አካባቢዎቹ ቀድሞውንም የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸው ሲሆን፣ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ከደረሳባቸው ጉዳት አላገገሙም።

የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትግራይ የቀረበው እርዳታ ላልተገባ ዓላማ ለሽጭ ውሏል እና ስርቆት ተፈፅሟል በሚል እርዳታ ማቋረጣቸውን ያስታወቁት ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ ነበር።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ያቋረጠውን የምግብ እርዳታ እንደሚጀምር ነሐሴ ወር ላይ ፍንጭ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም እስካሁን አልጀመረም።

ለኢትዮጵያ ከሚቀርበው እርዳታ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዙት የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና ዩኤስኤአይዲ የእርዳታ ሥርጭት በማቋረጣቸው ድጋፍ ጠባቂ የሆኑ 20 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን እና 800 ሺህ ስደተኞች ችግር ላይ ወድቀዋል።

በድርቁ የሞተ የቤት እንስሳ

የፎቶው ባለመብት, Waghimra communication

የምስሉ መግለጫ, በሰሜን ጎንደር ዞን በተከሰተው ድርቅ ብቻ ከ53 ሺህ በላይ የቤት እንስሳት መሞታቸውን የዞኑ ባለሥልጣን ተናግረዋል።

አቶ ምህረት እንደሚሉት በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ ግብር ሰናይ ደርጅቶች ጋር ከተነጋገሩ አእና የተከሰተውን ድርቅ በጋራ ከጎበኙ ሁለት ሳምንት ቢያልፈውም፣ እስካሁን ግን የቀረበ ድጋፍ የለም።

በዞኑ ክፉኛ በድርቅ ከተጎዱት ሰሃላ ሰየምት ወረዳ ውስጥ የነበሩ ከ1.2 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ እንስሳት ግጦሽ ፍለጋ ተሰደዋል።

እንስሳቶቹ ወደ አጎራባች አካባቢ ሲሄዱ ክትባት ስላላገኙ እንዲሁም ዘረፋ እና የፀጥታ ችግር ይከሰታል የሚል ስጋትም እንዳላቸው አቶ ምህረት ተናግረዋል።

የክልሉ አደጋ እና መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ዛሬ፣ መስከረም 22/2016 ዓ.ም በሰጠው መግለጫም በአማራ ክልል የዝናብ እጥረት በተከሰተባቸው የተከዜ ተፋሰስ አካባቢዎች የሚገኙ 1 ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚፈልጉ አስታውቋል።

ኮሚሽኑ በዚህ መግለጫው የረድኤት ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያቀርቡ ጥሪውን አቅርቧል።

በክልሉ ውስጥ ባለው የፀጥታ ችግር እንዲሁም ከአጎራባች ክልሎች በሚፈፀሙ ማንነት ተኮር ጥቃቶች ከተፈጠረው መፈናቀል እንዲሁም ከድርቅ ጋር በተያያዘ ሚሊዮኖች ድጋፍ ይፈልጋሉ።

የክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን በክልሉ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው 6.7 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች እንዳሉ ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል።