በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሶማሊያን ሕዝብ እና መንግሥት ይቅርታ ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, @TheVillaSomalia
በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር መሐመድ፤ ሶማሊያን በሚመለከት ለአንድ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ቃለምልልስ ላይ የሰነዘሩት ሃሳብ የተሳሳተ መሆኑን በመግለጽ ይቅርታ ጠየቁ።
አምባሳደሩ በቃለ ምልልሳቸው ሶማሊያ “የቅኝ ግዛት ውጤት” እንደሆነች እና በአገሪቱ ውስጥ ስላላው የፀጥታ ሁኔታ የገለጹበትን መንገድ በማስተባበል ነው አገሪቱን ሕዝብ እና መንግሥት ይቅርታ የጠየቁት።
አምባሳደሩ በሶማሊያውያን ዘንድ ቁጣን የቀሰቀሰውን ይህንን ቃለምልልሳቸውን በተመለከተ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የተጠቀሟቸው “ቃላት የተሳሳቱ” እንደነበሩ ገልጸዋል።
አምባሳደር ሙክታር ትላንት እሁድ ጥር 19/2016 ዓ.ም. ይቅርታ የጠየቁበት ቃለ መጠይቅ የተላለፈው ለመንግሥት ቅርበት ባለው ፋና ቴሌቪዥን ነበር።
ባለፈው ሳምንት የተላለፈው ይህ ቃለ መጠይቅ የአምባሳደሩ ግለሰባዊ ማንነት፣ የቀድሞ የሥራ ልምድ እንዲሁም ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የተፈራረሙት መግባቢያ ላይ ያተኮሩ አስተያየቶች የሰጡበት ነው።
ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ ወር ላይ በኢትዮጵያ የሶማሊያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ሙክታር፤ በአምባሳደርነት የተመደቡባት ሶማሊያ ከፀጥታ ሁኔታ አንጻር “ከሰሩባቸው አገራት ሁሉ በጣም አስቸጋሪው” እንደሆነ በዚህ ቃለ መጠይቅ ላይ ጠቅሰዋል።
አምባሳደር ሙክታር፤ “እንደልብሽ መንቀሳቀስ አትችዪም። ስትንቀሳቀሺም ጥበቃ ነው። ጥይት የማይበሳው መኪና ተጠቅመሽ ነው የምትሄጂው። በየትኛውም ጊዜ ከየትኛውም አካባቢ የፈንጂ ጥቃት ሰለባ ልትሆኚ ትችያለሽ” ሲሉ ቃለ መጠይቅ ላደረገችላቸው ጋዜጠኛ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የሶማሊያ አምባሳደርነት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ያሉት “በጣም አስቸጋሪ በሆነ የደኅንነት ድባብ ውስጥ” መሆኑን የገለጹት አምባሳደሩ፤ ይሁንና እስካሁን ምንም እንዳላጋጠማቸው አንስተዋል። አምባሳደር ሙክታር ቃለ መጠይቁ ላይ የሶማሊያ እና ሶማሊላንድ ምሥረታን አስመልክተውም ሀሳባቸውን አጋርተው ነበር።
ሶማሊያ “የቅኝ ግዛት የፈጠራት አገር” እንደሆነች የተናገሩት አምባሳደሩ፤ ሶማሊያ እና ሶማሊላንድ እ.አ.አ በ1960 ነጻነታቸውን ባገኙ በጥቂት ቀናት ልዩነት ውስጥ “እንደተዋሃዱ” አስታውሰዋል።
አምባሳደር ሙክታር፤ “[የሶማሊያ እና ሶማሊላንድ] ውህደቱ የነበረው በቋንቋ፣ ሃይማኖት እና በባህል እንመሳሰላለን በሚል እንጂ ታሪካቸው የተለያየ ነው። የተለያየ ታሪክ ያላቸው አገራት ናቸው። እንግዲህ ችግር የተፈጠረው ከውህደቱ በኋላ ነው። ሶማሊላንዶች ትልቅ በደል ደርሶብናል የሚል ቅሬታ እና ታሪክ ያነሳሉ” ሲሉ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ይህ የአምባሳደሩ ቃለ መጠይቅ በሶማሊኛ ተተርጉሞ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ የተለጠፈ ሲሆን፣ የተሰጠው አስተያየትም ሶማሊያውያንን አስቆጥቷል። ፋና ቴሌቪዥንም በዩቲዩብ ላይ ተጭኖ የነበረውን ሙሉ ቃለ መጠይቅ እና አምባሳደሩን በመጥቀስ ድረ ገጽ ላይ ለጥፎት የነበረውን ዘገባ አውርዷል።
በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር መሐመድም በኤክስ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ቃለ መጠይቁ መከፋት እንደፈጠረ ጠቅሰው ይቅርታ ጠይቀዋል። “የሶማሊያን መንግሥት እና ሕዝብን ከልብ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ቃላቶቼ የተሳሳቱ ነበሩ። ግንኙነታችንን ለመጉዳት አስቤ አይደለም” ብለዋል።
ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ ጥልቅ የሆነ ትስስር እንዳላቸው በመልክዕታቸው ያነሱት አምባሳደሩ፣ የሁለቱን አገራት ትስስር እና ትብብር ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ከአንድ ወር ገደማ በፊት የተፈራረሙትን የመግባቢያ ስምምነት ተከትሎ አዲስ አበባ እና ሞቃዲሾ ግንኙነታቸው ሻክሯል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ የባሕር በር ለማግኘት በምላሹም ሶማሊላንድ እንደ ሀገር በመቁጠር እውቅና ለመስጠት ተስማምታለች መባሉ ሶማሊያን አስቆጥቷል። ይህንን ተከትሎም ሶማሊያ በኢትዮጵያ የሚገኙትን አምባሳደሯን መጥራቷ ይታወሳል።















