በሞቃዲሾ የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ትዝታን የቀሰቀሰው የወቅቱ ውጥረት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከሰሞኑ የሶማሊያ መገናኛ ብዙሃን በአንድ በተመሳሳይ አጀንዳ ተይዘዋል።
መገናኛ ብዙሃኑ ኢትዮጵያን እንደ ታሪካዊ ጠላት አድርጎ የሚገልጸውን እና ጦርነት የሚጎስመውን ሙዚቃ ደጋግመው እያጫወቱ ይገኛሉ።
አንዳንዶች በሶማሊያ መንግሥታዊ ሚዲያዎች እየተከፈተ ያለው ይህ የሶማሊያ ፖሊስ ባንድ ሙዚቃ “ስሜት ቀስቃሽ” ነው ይሉታል።
ከሳምንታት በፊት ኢትዮጵያ እና ነጻ አገርነቷን ያወጀችው ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ የባሕር ጠረፍ ያስገኛል የተባለውን የመግባቢያ ሠነድ መፈራረማቸውን ተከትሎ በአዲስ አበባ እና በሞቃዲሾ መካከል ውጥረት ሰፍኗል።
ይህ የመግባቢያ ሠነድ ተፈጻሚ ሲሆን ኢትዮጵያ ለምትቀበለው የባሕር ጠረፍ በምላሹም ሶማሊያ እንደ አንድ ግዛቷ ለምትመለከታት ሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅናን ትሰጣለች ተብሏል።
ይህ በእጅጉ ያስቆጣቸው የሶማሊያ ባለስልጣናት ስምምነቱ በአገራችን ሉዓላዊነት ላይ የተፈጸመ ጥቃት ነው ሲሉ የቆዩ ሲሆን በተለያዩ መድረኮች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ውስጥ ለመገባት ዝግጁ ነን ሲሉ ተደምጠዋል።
የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዛ አብዲ ባሬ ባሳለፍነው ሳምንት ቅዳሜ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ውስጥ ለመግባት ዝግጁ ነን ብለው ነበር።
“ካልተዋችሁን፤ እንድትተዉን የሚያደርግ ነገር እናሳያችኋለን። . . .ወደ ሶማሊያ ግዛት አንድ ኢንች ለመግባት ቢሞከሩ፤ አስክሬኖችን ይዘው ወደ አገራቸው ይመለሳሉ” ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትር ሐምዛ አብዲ ባሬ።
ከዚህ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ቀደም ብሎ ደግሞ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ኢትዮጵያን የሶማሊያ “ጠላት” ሲሉ ገልጸዋት ነበር።
የሶማሊያ መገናኛ ብዙሃንም ሁለቱ አገራት ከ50 ዓመታት ገደማ በፊት ያደረጉትን ጦርነት የሚያስታውስ ሙዚቃ እያጫወቱ ይገኛሉ።
“ሰላም ካልፈለጋችሁ፤ በ1977 (እአአ) ያደረግናችሁን እንድታስታውሱ ዕድል እንሰጣቹሃለን” ይላል ይህ ሙዚቃ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢትዮ-ሶማሊ ጦርነት ወይም የኦጋዴን ጦርነት ከእአአ 1977 እስከ 1978 ድረስ የተካሄደ ሲሆን የሲዓድ ባሬ ሠራዊት ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ገብቶ በርካታ አካባቢዎች ይዞ ነበር።
ይሁን እንጂ የኮሎኔል መንግሥት ኃይለ ማርያም ጦር የጠላትን ኃይል ከኢትዮጵያ ክልል አስወጥቷል።
ይህን ጦርነት ሁለቱም አገራት አሸንፈናል ይላሉ።
ከዚህ ‘ሪመምበር ዋት ዊ ዲድ ቱ ዩ ኢን 1977’ (በ1977 ያደረግናችሁን አስታውሱ) ተብሎ ከሚጠራው ሙዚቃ በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ጋር የተያያዙ ሌሎች ሁለት ሙዚቃዎች በሶማሊያ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት እየተሰራጩ ነው።












