የዓለም ዋንጫ፡ ብሔራዊ ቡድናቸው በመሸነፉ ደስታቸውን ሲገልጹ ከነበሩ ኢራናዊያን መካከል አንድ ሰው ተገደለ

የፎቶው ባለመብት, SOCIAL MEDIA
ብሔራዊ ቡድናቸው ከዓለም ዋንጫ በጊዜ በመሰናበቱ ደስታቸውን ሲገልጹ ከነበሩ የኢራን መንግሥት ተቃዋሚዎች መካከል አንድ ሰው በጸጥታ አካላት መገደሉ ተገለጸ።
ማከሰኞ ምሽት የህብረተሰብ አንቂ የሆነው ሜህራን ሳማክ በባንዳር አንዛሊ የመኪናውን ጥሩምባ ሲነፋ ግንባሩ ላይ በጥይት መመታቱ ተነግሯል።
ከሌሎች ከተሞች የተገኙ ምስሎች እና ቪዲዮዎች እንደሚያሳዩት በርካታ ሰዎች መንገዶች ላይ ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል።
ብሔራዊ ቡድኑ የኢስላሚክ ሪፐብሊክ ምልክት ነው በማለት ብዙ ኢራናዊያን ድጋፋቸውን ከመስጠት ተቆጥበዋል።
የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን በሃገር ውስጥ እና በውጭ ያሉ ኃይሎች በአሜሪካ 1 ለ 0 በተሸነፈበት የመጨረሻው የምድብ ጨዋታ ወቅት ጫና እንዳሳደሩበት ገልጸዋል።
በእንግሊዝ 6 ለ 1 በተሸነፉበት ጨዋታ ደግሞ ተጫዋቾችቹ ብሔራዊ መዝሙር አልዘመሩም።
ይህም ለተቃዋሚዎች ያላቸውን ድጋፍ ያሳያል ተብሏል።
ዌልስን 2 ለ 0 ባሸነፉበት እና ፖለቲካዊ ውጥረት በነበረው የአሜሪካ ጨዋታ ወቅት ግን ብሔራዊ መዝሙሩን ዘምረዋል።
የቡድኑ አባላት በጸጥታ ሃይሎች ጫና ደርሶባቸው ነው ቢባልም አንዳንድ ተቃዋሚዎች ቡድኑ ብሔራዊ መዝሙሩን በመዘመሩ ከድቶናል የሚል ስሜት ፈጥሮባቸዋል።
በኢራን አለመረጋጋት የጀመረው ከአስር ሳምንታት በፊት ነው። የ22 ዓመቷ ማህሳ አሚኒ የሂጃብ አለባበስ ደንብ ጥሳለች በሚል በስነ ምግባር ፖሊሶች እጅ ህይወቷ ማለፉ ቁጣውን ቀስቅሶታል።
ባለስልጣናት “አመጹን” በውጭ ሃይላት የሚደገፍ ሲሉ ይገልጻሉ።
መቀመጫውን ኖርዌይ ያደረገው የኢራን የሰብዓዊ መብት ቡድን 60 ህጻናትን ጨምሮ በትንሹ 448 ሰዎች መገደላቸውን ገልጿል። ከ18 ሺህ በላይ ሰዎች መታሰራቸውም ተነግሯል።
ኢራን ብሔራዊ ቡድን ሽንፈትን በደስታ ለማክብር የመኪናውን ጥሩምባ ሲነፋ የነበረው የ27 ዓመቱ ሜህራን ሳማክ በጸጥታ ሃይሎች መገደሉን የኢራን ሰብዓዊ መብት ሪፖርት አድርጓል።
ቢቢሲ ፐርዢያ ረቡዕ ጠዋት የተደረገለትን የቀብር ስነ ስርዓት ቪዲዮ ለመመልከት ችሏል።
ሃዘንተኞች “ቆሻሻ ናችሁ፣ ሞራል የላችሁም፣ እኔ ነጻ ሴት ነኝ” የሚሉና በተቃዋሚዎች የሚዘወተሩ መፈክሮችን አሰምተዋል።
የኢራን ጸጥታ ኃይሎች ሠላማዊ ተቃዋሚዎችን አልገደልንም ሲሉ ያስተባብላሉ።
ሌሎች ቪዲዮዎች ደግሞ ቴህራንን ጨምሮ በተለይም በኩርዲስታን ከተሞች የብሔራዊ ቡድኑን ከዓለም ዋንጫ መሰናበት ደስታቸውን የገለጹ በርካታ ናቸው። በቅርቡ የጸጥታ ሃይሎች በወሰዷቸው እርምጃዎች በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል።
በማህሳ አሚኒ የትውልድ ከተማ ሳቄዝ ስካርፋቸውን በማውለብለብ ደስታቸውን ከመግልጽ ባለፈ ርችትም ሲተኩሱ ታይተዋል።












