“ኢትዮጵያውያን በኳታሮች ዘንድ ይከበራሉ” - የዓለም ዋንጫ ዶሃ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዐይን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ግሩም ሰይፉ ጋዜጠኛ ነው። አዲስ አድማስ ለተሰኘው ጋዜጣ ስፖርታዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮችን በመፃፍ ይታወቃል። ግሩም የኳታር የዓለም ዋንጫ ዝግጅትን ለመታደም ወደ ዶሃ ያቀናው ከመክፈቻው ጥቂት ቀናት ቀድሞ ነው።
ዶሃ ከአዲስ አበባ 2200 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ትገናለች። የኢትዮጵያ አየር መንገደ እና ኳታር ኤርዌይስ በየቀኑ መንገደኞችን ያመላልሳሉ።
ግሩም፤ ነፋሻማዋን አዲስ አበባ ለቆ ወደ ዶሃ ሲያመራ የጠበቀው የግንቦት ሃሩር ነው። ነገር ግን ይህ ወቅት ለኳታሮች ቀዝቃዛው ወር ነው።
“ዶሃ የቀትር ፀሐይ የሚባል የለም” ይላል። ምክንያቱም ቀኑን ሙሉ የዶሃን አሸዋማ መሬት የሚቀጠቅጠው ፀሐይ ሃሩር ነው።
ኳታር፤ በሜትሬዎሎጂ ዘገባ አገላለፅ “በአብዛኛው ፀሐያማ” ናት። በአብዛኛው ከማለት ከንጋት እስከ ምሽት ማለት ሳይቀል አይቀርም።
አሁን ባለው የአገሪቱ የአየር ሁኔታ ዝቅተኛው የሚባለው 23 ድግሪ ሴንትግሪድ የሚጀምረው ለሊት 10 ሰዓት ገደማ ነው።
ዎርልድ ፖፑሌሽን ሪቪው የተሰኘው ድረ-ገፅ የኳታር ሕዝብ ብዛት በዚህ ዓመት 2.7 ሚሊዮን ይገመታል ይላል።
ከእነዚህ መካከል ካታሪ የሚባሉት አረቦች 15 በመቶውን ይይዛሉ። ሕንዳዊያን፣ ፊሊፒናውያን እንዲሁም ሌሎች የእስያ አገራት ዜጎች ኑሯቸውን በኳታር ይኖራሉ።
ከዚህ ባሻገር በርካታ ኢትዮጵያዊያን፣ ኤርትራዊያን እና ኬንያዊያን በዋና ከተማዋ ዶሃ እንዲሁም በአር ራያን ይገኛሉ።
በነዳጅ ሃብት የበለፀገችው ኳታር እነሆ በአረቡ የዓለም ሲዘጋጅ የመጀመሪያው የሆነውን የዓለም ዋንጫ በማስተናገድ ላይ ትገኛለች።

የፎቶው ባለመብት, girum
“ኢትዮጵያዊያን የሥራ ሰዎች ናቸው ይባላሉ”
ግሩም፤ ካሜሩን ከሰርቢያ የሚያደርጉትን የቀን 7 ሰዓት የምድብ ጨዋታ ታድሞ ለመዘገብ እየተጓዘ ሳለ ነው በስልክ ያገኘነው።
በየገባህበት ሥፍራ ሁሉ የአየር ማጤዣ ተገጥሟል የሚለው ግሩም፣ ይህ ቴክኖሎጂ ባይኖር ኳታር ለኑሮ ከባድ ትሆን እንደነበር ያምናል።
“አሁን ለምሳሌ በአገሩ ሰዓት አቆጣጠር 5 ሰዓት ከምናምን ነው። እኛ አገር ግንቦት ወር ላይ ያለው የሚያማርረው ሙቀት ነው አሁን እዚህ ያለው።”
ግሩም የኳታር ነዋሪዎችን ስለአየር ሁኔታው ሲጠይቃቸው “በብርድ ወቅት መጣህ” በሚል ዓይን እያዩት “ኧረ እንዲያውም ይሄ እኮ ቀዝቃዛው ጊዜ ነው” ይሉታል።
ኳታር፤ ለዚህ ነው ይህንን ወቅት ለዓለም ዋንጫ የመረጠችው እንጂ ለወትሮው የዓለም ዋንጫ በሰኔ ነበር የሚዘጋጀው።
ከፋርስ ባሕረ ሰላጤ የሚነሳው ነፋስ የኳታር ምሽትን ቀዝቀዝ አድርጎታል።
ኳታር፤ ይህን የዓለም ዋንጫ ስታዘጋጅ ከምዕራቡ ዓለም ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶባት ነበር። አገሪቱ የሰብዓዊ መብት አይከበርባትም፣ ስታድየሞቹ ሲታነፁ በርካታ የጉልበት ሠራተኞች ሞተዋል፣ የአየር ሁኔታው ምቹ አይደለም. . . ብቻ ብዙ ነቀፋ አስተናግዳለች።
ነገር ግን ጋዜጠኛ ግሩም ይህ ነቀፋ ተጋኗል የሚል እምነት አለው። “የኳታር ዜጎች በጣም ሰላምተኞች ናቸው። እንግዳ ተቀባይነታቸውን ማየት ችያለሁ። በአረቡ ዓለም መዘጋጀቱ የአረቡ የዓለም ለእግር ኳስ ያለውን ፍቅር ለማሳየት ልዩ አጋጣሚ ነው” ይላል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እንደሱ አመለካከት ዶሃ ወደፊት ልክ እንደ ዱባይ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡ ጎብኚዎች የምታስናግድ መናኸሪያ እንደምትሆን አምነት አለው።
ግሩም፤ በዶሃ በተዘዋወረባቸው ቦታዎች በርካታ ኢትዮጵያውያን ኑሮን ለማሸነፍ በተለያየ ሥራ ተሠማርተው ሲተጉ አይቷል።
“ስታድየሞች ውስጥ በጎ ፈቃደኛ ኢትዮጵያውያን አግኝቻለሁ። አንድ የሥነ-ጥበብ ባለሙያ ኢትዮጵያዊም ተዋውቄያለሁ። በዓለም ዋንጫው ከትላልቅ የብሮድካስት ኩባንያዎች ጋር የሚሠራ ኢትዮጵያዊም ማግኘት ችያለሁ።”
ጋዜጠኛው ባለኝ መረጃ መሠረት ከ20 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ኳታር ውስጥ ይኖራሉ ይላል።
ስለአገሪቱ የተለያዩ መረጃዎችን የሚያወጣው ‘ኦንላይን ካታር’ የተሰኘው ገፅ ቢያንስ 25 ሺህ ኢትዮጵያዊያን እንደሚገኙ አስፍሯል።
“በቤት ሠራተኝነት የሚሠሩ አሉ። የሚማሩ አሉ። የሕንፃ ግንባታ ባለሙያዎች፤ የታክሲ ሾፌሮች አሉ። በርካታ የኢትዮጵያ ሬስቶራንቶች ያሉበት አንድ አካባቢ አለ። አዲስ አበባ የሚል ስያሜ ያለው ፀጉር ቤት አይቻለሁ። እኔ ከጎበኘኋቸው ሬስቶራንቶች በአንዱ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ተሰባስበው አይቻለሁ።”
ግሩም፤ “ኢትዮጵያውያን በኳታሮች ዘንድ ይከበራሉ። “የሥራ ሰዎች ናቸው ይባላሉ” ይላል።
ጋዜጠኛ ግሩም ከዚህ ቀደም ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም ሩሲያ ተጉዞ የዓለም ዋንጫን መታደም ችሏል። ነገር ግን የዶሃው በብዙ መልኩ እንደሚለይ ይገልጻል።
አንደኛው ምክንያት ስታድየሞቹ የተቀራረቡ በመሆናቸው እሱና የሙያ አጋሮቹ በአንድ ቀን የተለያዩ ጨዋታዎችን መታደም መቻላቸው ነው።
ለምሳሌ በሩሲያው የዓለም ዋንጫ ከዋና ከተማዋ ሞስኮው ወደ ሶቺ ለመሄድ 72 ሰዓታትን በባቡር ተጉዞ ነበር።
አልፎም ከዚህ በፊት ከተመለከታቸው የዓለም ዋንጫዎች በተለየ በምድብ ጨዋታዎች የታየው ፉክክር፣ ተመልካቾች ብዛት፣ የስታድየሞቹ ልዩ ‘ዲዛይን’ ይህንን የዓለም ዋንጫ “ለየት አድርጎብኛል” ባይ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
“በቃ ኳስ ማለት ይሄ ነው”
መስከረም ዘውዴ በኳታር ከ15 ዓመታት በላይ ኖራለች። ዋና ከተማዋ ዶሃን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውራ ሠርታለች። አሁን ዶሃ ውስጥ አቢሲኒያ-ቢሾፍቱ የተሰኘ የቤተሰብ ሬስቶራንት ታስዳድራለች።
የመስከረም ሬስቶራንት ከሰሞኑ ከተለያዩ ክፍለ ዓለማት በሚመጡ ተጠቃሚዎች መሞላቱን “ዕድሜ ለዓለም ዋንጫ” በሚመስል አንድምታ ትናገራለች።
በርካታ ኢትዮጵያውያን እንግዶች፣ ኤርትራውያን፣ ሱዳናውያንን ጨምሮ የበርካታ አገራት ዜጎች ምግብ ቤቷን እንደሚጎበኙ ጠቅሳለች።
ነገር ግን ብዙውን ጊዜ ኢትዮጵያውያን ተጠቃሚዎች የሌሎች አገራት ዜጎች ጓደኞቻቸውን ይዘው መጥተው የአገራቸውን ገበታ ሲቋደሱ ስታይ ደስ ይላታል።
መስከረም ለአራት ዓመታት ያክል ያስተዳደረችው አቢሲኒያ-ቢሾፍቱ ሬስቶራንት፣ ዶሃ ውስጥ ኔአዘር የተሰኘ አካባቢ ይገኛል።
ይህ መንደር በርካታ ኢትዮጵያውያን የሚኖሩበት ነው።
መስከረም የዓለም ዋንጫ መጣ ሲባል ምናልባት አንዳንድ ቦታዎች ላይ ከመጠን በላይ መጨናነቅ ይኖራል የሚል ፍራቻ ነበራት። ነገር ግን ይህ በየአራት ዓመት የሚዘጋጅ ውድድር ደስታን ይዞላት ብቅ ብሏል።
“ሰዉ በጣም ደስተኛ ነው። በነፃነት ነው የሚንቀሳቀሰው። ከዚህ በፊት ከምናውቀው የተለየ ነገር እያየን ነው። ሁሉም ሰው በሥነ-ሥርዓት ይስተናገዳል። ስሜቱም ለየት ይላል።”
አቢሲኒያ-ቢሾፍቱ ሬስቶራንት የ32 አገራት ባንዲራዎች ይውለበለቡበታል። በዓለም ዋንጫ እየተሳተፉ ያሉ 32 አገራትን የሚወክል ነው።
ሬስቶራንቱ ካለበት ቦታ ራቅ ብሎ ያለው ድባብ ልዩ እንደሆነ የምትናገረው መስከረም፣ እግር ኳስ እንዲህ ሰውን ሲያቀራርብ ማየቷ አስደንቋታል።
“በቃ ኳስ ማለት ይሄ ነው። እግር ኳስ የዓለም ሰዎችን የሚያቀራርብ እንደሆነ ነው የገባኝ። በግሌ የተረዳሁት ይህንን ነው። በጣም ነው ደስ የሚለው። በጣም!”
መስከረም፤ ሬስቶራንቱ ከሰሞኑ በደንበኞች በመጨናነቁ እንጂ በስታድየሞች ዙሪያ የኢትዮጵያ ገበታ ለተጠቃሚዎች አስባ ነበር።
ለወትሮው ሙቀቷ ነፍስን የሚያስጨንቀው ኳታር ከሰሞኑ ቀዝቀዝ ማለቷ ለመስከረም አስደንቋታል። እንጂ የዶሃ ሙቀት የሚቋቋሙት አይደለም ትላለች።
ለበርካታ ዓመታት በባሕረ ሰላጤዋ አገር የኖረችው መስከረም ኳታር ወግ አጥባቂ የአረብ አገር እንደመሆኗ እግር ኳስ ለመታደም የሚመጡ ሰዎች እንደልባቸው ላይዝናኑ ይችላሉ የሚል ስጋት ነበራት።
ኳታር ስታዲዬሞች ውስጥ የአልኮል መጠጥ እንዳይሸጥ ከልክላለች። ነገር ግን በምሽት ክለቦች ሜክሲኮ እና የብራዚል ዜጎች ሲጨፍሩ ነው የከረሙት ትላለች መስከረም።
ከሌሎች አገራት የሚመጡ ሰዎች የተለያየ ባሕርይ ይዘው ነው የሚመጡት። ነገር ግን አብዛኛዎቹ ጎብኚዎች ደስተኛ ሆነው በነፃነት ሲንቀሳቀሱ፣ ሲጫወቱ፣ ሲጨፍሩ ተመልክታለች።
“አይቼው የማላውቀው ነው። በእውነት የተለየ ስሜት ፈጥሮብኛል።”

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
“ኳታር በብዙ ነገር አሸንፋለች”
ኢትዮጵያዊው አብዱልሃኪም አብዱልራህማን፤ በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ መኖር ከጀመረ አምስት ዓመታት አልፎታል። አብዱልሃኪም፤ ከዓለም ዋንጫው በጎ ፈቃደኞች አንዱ ነው።
ወጣቱ፤ ከዶሃ ግዙፍ ስታዲዮሞች አንዱ በሆነው ኻሊፋ ዓለም አቀፍ ስታዲዬም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
አብዱልሃኪም ዋነኛ ሥራው ጨዋታ ለመታደም ለሚመጡ ተመልካቾች አቅጣጫ መጠቆም፣ የሚያስፈልጋቸውን ነገር በመርዳት የበኩሉን ይወጣል።
አልፎም በአገሪቱ ሕግ መሠረት የማይቻሉ ነገሮችን ጎብኚዎች ሲፈጽሙ ከተገኙ በማስረዳት የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱን ይወጣል። እያወቁ የሚያጠፉ ሰዎችን ደግሞ ለበላይ አካል ያሳውቃል።
አብዱልሃኪም ይህን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት ከመጀመሩ በፊት የአጭር ጊዜ ሥልጠና ወስዷል።
ወደ ስታዲዬም ጨዋታ ለመመልከት የሚመጡ ሁሉም ሰዎች ምግባረ-መልካም አይደሉም፣ የሚለው ወጣቱ አንዳንድ ጎብኚዎች በጎ ፈቃደኞችን እንደሚያንጓጥጡ ይናገራል።
"ኳታር ሁለተኛ አገሬ ናት" የሚለው አብዱልሃኪም በዓለም ዋንጫው ብዙም ላልተሳካለት የኳታር ብሔራዊ ቡድን ድጋፉን ሲሰጥ ነበር።
በምድብ አንድ ከኔዘርላንድስ፣ ከሴኔጋል እና ከኤኳዶር ጋር የተደለደለችው ኳታር ሦስቱንም ጨዋታዎች ተረትታ ተሰናብታለች።
ቢሆንም አብዱልሃኪም እንደሚለው “ኳታር በብዙ ነገር አሸንፋለች።”
“ከዓለም አገራት ብዙ መልክ እና ፍላጎት ያላቸው እንግዶችን ተቀብላ ማስተናገዷ እንደ አንድ ትልቅ ድል ነው የማየው።”












