ስኮትላንድ እግር ኳስ ተጫዋቾች ‘የቴስታ’ ኳሶችን እንዳይመቱ ልታግድ ነው

እግር ኳስ ተጫዋቾች ኳስ በቴስታ ለመምታት ሲሻሙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በስኮትላንድ ያሉ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋቾች ከጨዋታ አንድ ቀን በፊት እና በኋላ ኳስ በጭንቅላት (በቴስታ) እንዳይመቱ ሊታገዱ ነው።

ክለቦችም የጭንቃላት ኳስ የሚበዛባቸው የልምምድ ቀኖችን በሳምንት ወደ አንድ እንዲቀንሱ ተጠይቀዋል።

ውሳኔው የግላስጎው ዩኒቨርሲቲ ያደረገው ጥናት እግር ኳስ ተጫዋቾች ከሦስት እጥፍ በላይ ከጭንቅላት ጋር በተያያዘ በሽታ እንደሚሞቱ ማሳየቱን ተከትሎ የመጣ ነው።

ባለሙያዎች ችግሩ ኳስን በተደጋጋገሚ በጭንቅላት ከመምታት ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ጠቁመዋል።

የስኮትላንድ እግር ኳስ ማኅበር ከ12 ዓመት በታች ቡድኖች በልምምድ ወቅት ኳስ በጭንቅላት እንዳይመቱ የሚያግድ ሕግ አለው።

አዲሱ ሕግ በአገሪቱ ካሉ 50 የወንዶች እና የሴቶች የእግር ኳስ ክለቦች ጋር ውይይት በማድረግ እና የእግር ኳስ ማኅበሩ በጭንቅላት ኳስ ዙሪያ መረጃ ከሰበሰበ በኋላ ይተገበራል ተብሏል።

ክለቦችም በልምምድ ወቅት የጭንቅላት ኳሶችን ሁኔታ በድንብ እንዲያጤኑ ተነግሯቸዋል።

ዶክተር ጆን ማሊን ከ20 ዓመታት በላይ የስኮትላንድ እግር ኳስ ማኅበር ሐኪም ሆነው አገልግለዋል። በ2019 በተካሄደው እና የቀድሞ ተጫዋቾችን ከዲሜንሺያ (የጭንቅላት ህመም ሲሆን ከመርሳት እና ከማንነት ለውጥ ጋር ይያያዛል) ጋር ባያያዘው ጥናት ተሳትፈዋል።

“ጥናቶቹ እየተጠናከሩ ቢሆንም እስካሁን ባለው ከ24 እስከ 48 ሰዓታት የሚቆይ የመርሳት ችግርን ያስከትላል። ኳስ በጭንቅላት ከተመታ በኋላ የአዕምሮ ፕሮቲኖች በደም ናሙና ውስጥ ተገኝተዋል።”

“የጭንቅላት ኳስ የሚመቱ ተጫዋቾች የአዕምሮ ስካን ላይ ለውጥም ታይቷል። ስለዚህ ዋና ዓላማው በልምምድ ቦታ የጭንቅላት ኳሶችን በመቀነስ በጊዜ ሂደት የሚመጣውን ጉዳት መቀነስ ነው” ብለዋል።

በአዲሱ ሕግ መሠረት ከጨዋታ በፊት የሚኖሩ የቅጣት ምትን ጨምሮ የጭንቅላት ኳስን የሚያካትቱ ልምምዶች ላይ ለውጥ ያመጣል።

“ባለድርሻ አካላትን ለማካተት በሚል ጊዜ ወስደናል” ብለዋል ዶ/ር ማክሊን።

“መሠረታዊ መረጃ ለማግኘት በልምምድ ወቅት ምን ያህል የጭንቅላት ኳስ እንደሚኖር ለማወቅ እንፈልጋለን።”

“በቀመጠልም ከማኅበሩ፣ ከክለቦች እና ከአሰልጣኞች ጋር በመሆን ተጫዋቾችን እናሳትፋለን” ብለዋል።

“ይህ የጋራ ኃላፊነት ሲሆን የተጫዋቾችንም ጤና ለመጠበቅ ያለመ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ኳስ በጭንቅላቷ የምትመታ ልጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የስኮትላንድ እግር ኳስ ማኅበር ዋና ኃላፊ አንዲ ጎልድ እንዳሉት በጨዋታ ወቅት ስላለው የጭንቅላት ኳስ በቂ መረጃ አለ።

የቅርብ ጊዜው ምርምር ግን “በልምምድ ወቅት የጭንቅላት ላይ ያለውን ጫና ለመረዳት በጣም ጠቃሚ ነው” ብለዋል።

አክለውም “ለተጫዋቾቻን ጤና ሲባል በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውይይት ለማመቻቸት የሚያስፈልጉ መረጃዎችን እና አመለካከቶችን ስለሰጡን ክለቦችን፣ አሰልጣኞችን እና ተጫዋቾችን አመሰግናለሁ።”

በዚህ የአውሮፓውያን ዓመት መጀመሪያ ላይ የእንግሊዝ የእግር ኳስ ማኅበር በልምምድ ወቅት ተጫዋቾች በሳምንት 10 ከፍተኛ ተፅእኖ ያላቸውን የጭንቅላት ኳሶች ብቻ እንዲጠቀሙ የሚገድብ መመሪያ ለክለቦች አውጥቷል።

የቀድሞ የሴልቲክ አምበል ቢሊ ማክኔል እና ከእንግሊዝ ጋር የዓለም ዋንጫን አነስቶ የነበረውና በኋላም የአየርላንድ ሪፐብሊክ አሰልጣኝ ለመሆን የቻለው ጃክ ቻርልተንን ጨምሮ በርካታ ታዋቂ የቀድሞ የእግር ኳስ ተጫዋቾች በዲሜንሽያ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል።