ከወሳኝ የምድብ ጨዋታቸው በፊት ኢራን በአሜሪካ ላይ ለፊፋ ክስ አቀረበች

የኢራን ሰንደቅ ዓላማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አሜሪካ እና ኢራን ማክሰኞ ዕለት ቀጣይ ጨዋታ ያደርጋሉ

የኢራን እግር ኳስ ፌዴሬሽን የአሜሪካን ቡድን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቹ ላይ ካወጣው የኢራን ሰንደቅ ዓላማ ጋር በተያያዘ ለፊፋ ክስ አቀረበ።

የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ለዓለም አቀፉ የእግር ኳስ የበላይ አካል አቤቱታ ያረበው የአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የኢራን ብሎ ያወጣው ሰንደቅ ዓላማ እስላማዊ ሪፐብሊኳን የሚወክለውን አርማ አንስቶታል የሚል ነው።

ኢራን እና አሜሪካ ነገ ማክሰኞ ከሚኖራቸው የዓለም ዋንጫ የምድብ ግጥሚያ በፊት፣ የአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን በትዊተር፣ በፌስቡክ እና በኢንስታ ግራም ላይ ከለጠፈው የኢራን ባንዲራ ላይ የአገሪቱ መለያ አርማ አልተካተተም።

አሜሪካ ለዚህ ክስ በሰጠችው ምላሽ በአገሪቱ ውስጥ እየተካሄዱ ካሉት ፀረ መንግሥት ተቃውሞዎች ጋር በተያያዘ “በኢራን መሠረታዊ መብቶች እንዲከበሩ እየታገሉ ላሉት ሴቶች ድጋፈችንን ለመግለጽ” የአገሪቱን ይፋዊ ሰንደቅ ዓላማ ላለመጠቀም መወሰኑን ገልጻለች።

በኢራን ውስጥ ማህሳ አሚኒ የተባለች የ22 ዓመት ወጣት ሂጃብ በአግባቡ አልለበሰችም በሚል በአገሪቱ የሥነ ምግባር ፖሊሶች ተይዛ ከታሰረች በኋላ መሞቷን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው።

“ሙያዊነት በጎደለው ተግባር፣ የአሜሪካ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የኢንስታግራም ገጽ በሰንደቅ ዓላማው ላይ ያለውን የአላህ ምልክትን አስወግዶታል” ሲል የኢራን መንግሥት ዜና ወኪል ኢርና ገልጸወል።

ይህንንም ተከትሎ “የኢራን የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የእግር ኳስ የበላይ አስተዳዳሪው አካል ፊፋ ለአሜሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠንካራ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጥ የሚጠይቅ ኢሜይል ልኳል።”

በኋላ ላይ ግን አንድ የአሜሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቃል አቀባይ እንዳሉት፣ ቅሬታ የቀረበበት የሰንደቅ ዓላማ ምስል ከማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ እንዲነሱ መደረጋቸውንና በምትካቸውም ትክክለኛው የኢራን ሰንደቅ ዓላማ እንዲወጣ መደረጉን ገልጸዋል። ነገር ግን “አሁንም የኢራን ሴቶችን እንደግፋለን” ብለዋል።

ኢራን አሜሪካንን እና ሌሎች ባላንጣዎቿን በአገሯ ውስጥ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ በማባባስ የምትከስ ሲሆን፣ የኢራን መንግሥት በተቃዋሚዎች ላይ እየወሰደ ካለው እርምጃ ጋር ተያይዞ አሜሪካ በአገሪቱ ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ እየጣለች ነው።

በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ላይ በምድብ ለ ከእንግሊዝ፣ ከአሜሪካ እና ከዌልስ ጋር የተደለደለችው ኢራን ሦስት ነጥብ ይዛ ከእንግሊዝ በመከተል በምድቡ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

በእግሊዝ 6 ለ 2 ተሸንፋ ዌልስን 2 ለ 0 ያሸነፈችው ኢራን የምድቡ ወሳኝ ጨዋታዋን ነገ ማክሰኞ ኅዳር 20/2015 ዓ.ም. ከአሜሪካ ጋር ታደርጋለች።

ኢራን ታካሂደዋለች በሚባለው የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ግንባታ ፕሮጀክት የተነሳ ለዓመታት እየተወዛገበቻት ከምትገኘው ከአሜሪካ ጋር በአንድ ምድብ ተደልድለው ከጨዋታቸው ቀደም ብሎ ከሰንደቅ ዓላማዋ ጋር በተያያዘ ቅሬታዋን አቅርባለች።

አሜሪካ እና ኢራን በአይነ ቁራኛ የሚጠባበቁ ባላንጣዎች ሲሆኑ፣ የዲፕሎማቲክ ግንኙነታቸውን ካቋረጡ ከአርባ ዓመታት በላይ ሆኗቸዋል።