የዓለም ዋንጫ፡ አፍሪካን ስለሚወክሉ አገራት ስድስት ወሳኝ ነጥቦች

በኳታር የዓለም ዋንጫ የሚካፈሉ የአፍሪካ አፍሪካ አገራት አዲስ ታሪክ ጽፈዋል። አምስቱም አገራት በራሳቸው ዜጎች ነው የሚሰለጥኑት።
አራቱ አሰልጣኞች በዚህ ውድድር ሲካፈሉ የመጀመሪያቸው ነው። የሴኔጋሉ አሉ ሲሴ ብሔራዊ ቡድኑን ሩሲያ ላይም መምራት ችለዋል።
በ2018 አምስቱም የአፍሪካ ተወካዮች ከምድባቸው ማለፍ አልቻሉም።
ቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ከእነዚህ ቡድኖች ጋር በተያያዘ የሚነሱ ወሳኝ ጥያቄዎችን ይመልሳል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሩብ ፍጻሜው ማለፍ የሚችል ቡድን ይኖር ይሆን?
የአፍሪካ ተወካዮች ፈተና ከየምድባቸው ይጀምራል። ሞሮኮ፣ ሴኔጋል፣ ቱኒዝያ፣ ግብጽ እና ናይጄሪያ ከ2018 የዓለም ዋንጫ ምድብ ጨዋታዎች አልዘለሉም።
ካሜሮን እና ጋና ርዕስ ከነበሩበት የ2014 የዓለም ዋንጫ በኋላ ለዘንድሮው ውድድር በቅተዋል። የካሜሮን ተጫዋቾች ሜዳ ላይ ቡጢ ተሰናዘሩ። ጋናዎች ከቦነስ ክፍያ ጋር በተያያዘ ተጋጩ።
ሴኔጋሎች ለመጀመሪያ ጊዜ አፍሪካ ሻምፒዮን ከሆኑ በኋላ የሚሳተፉበት የዓለም ዋንጫ ነው። የዓለም ኮከብነትን በሁለተኛነት ያጠናቀቀው ሳዲዮ ማኔ በጉዳት ከቡድኑ ርቋል።
ሞሮኮ አዲስ አስልጣኝ ከሾመች ሁለት ወር ብቻ ሆናት። ቤልጂየም፣ ክሮሽያ እና ካናዳ በምድቧ ይገኛሉ።
ካሜሮን ፍጥነት እና ጉልበት የቀላቀለ አጨዋወት ስትመርጥ ይስተዋላል። የቀድሞ ኮከቧ እና የአገሪቱ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ኃላፊ ሳሙኤል ኤቶ ዋንጫውን ማን ያነሳል ተብሎ ተጠይቆ ሞሮኮ እና ካሜሮን ለፍጻሜ ይደርሳሉ ብሏል። ዋንጫው በሪጎበርት ሶንግ የሚመሩት የማይበገሩት አንበሶች ይሆናል ማለቱ ቡድኑ ላይ ጫና እንዳይፈጠር ተሰግቷል።
ሦስት የአፍሪካ አገራት የዓለም ዋንጫው የሩብ ፍጻሜ ደርሰዋል።
አሁን ቀዳሚው ዓላማ ግማሽ ፍጻሜ ነው።
ሴኔጋል እንዴት አድርጋ ማኔን መተካት ትችላለች?
ሴኔጋል ኮከቧን እና በ34 ጎሎች የብሔራዊ ቡድኑ ጎል አግቢነትን የሚመራውን አጥቂዋን ሳዲዮ ማኔን በጉዳት አጥታለች።
ጆርጅ ዊሃ የዓለም ኮከብ የተባለው እአአ በ1995 ነው። ከዚያ ወዲህ በዓለም ኮከብነት ምርጫ ከሦስተኛ በላይ ያለውን ደረጃ ይዞ ማጠናቀቅ የቻለው ማኔ ብቻ ነው።
ሴኔጋል አሁን ተስፋ ያደረገችው በዋትፎርዱ ኢስማሊያ ሳር እና በአላንያስፖሩ አጥቂ ፋማራ ዲድሁ ላይ ነው። ቡላዬ ዲያም ሌላው ተስፋዋ ነው።
ሲሴ ከሴኔጋል ወርቃማ ትውልድ አባላት አንዱ ናቸው። ቡድኑ በጃፓን እና ኮሪያው የ2002 የዓለም ዋንጫ ስምንት ውስጥ መግባት ችሏል። አሰልጣኙ ለዓመታት ያካበቱትን ልምድ ተጠቅመው አዲስ ዕቅድ እንደሚነድፉ ይጠበቃል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ማኔ በሌለበት የአፍሪካ ኮከብ ማን ይሆናል?
ሞሐመድ ሳላህ እና ሪያድ ማህሬዝ ለትልቁ ውድድር ለመብቃት አልቻሉም። አሁን አዲስ አፍሪካ ኮከብ ፍለጋ መውጣት ግድ ይላል።
ከአያክስ ጋር በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ እየፈካ የሚገኘው ጋናዊው አማካኝ ሞሐመድ ኩዱስ ከዕጩዎቹ አንዱ ነው። ካሜሮን ምርጥ የአጥቂ ስብስብ አላት። ኤሪካ ማክሲም ቹፖ-ሞቲንግ፣ ካርል ቶኮ ኤካምቢ እና ቪንሰንት አቡበከር ይጠቀሳሉ።
ቱኒዚያውያን ድንቅ በአማካኛቸው አይሳ ላይዱኒ ይተማመናሉ። ሞሮኮ በበኩሏ ሃኪም ዛይችን ይዛለች።
ዛይች ከቀድሞ አሰልጣኙ ጋር ባለመግባባቱ ራሱን ከብሔራዊ ቡድኑ ቢያገልም አዲስ አስልጣኝ ሲሾም ሃሳቡን ቀይሮ ለቡድኑ መከታ ለመሆን ተዘጋጅቷል።
ጊዜው ለአፍሪካውያን ያደላ ይሆን?
ይህ ዓለም ዋንጫ እንደ ቀደሞዎቹ ሁሉ ሰኔ ላይ አይካሄድም። ይህም በሞቃታማ ወቅት የሚከናወን የዓለም ዋንጫ ያደርገዋል።
የኳታር የአየር ሁኔታ ለአውሮፓዊያን የሚቻል አይመስልም።
ምሽት ላይ አየሩ ቀዝቀዝ ይላል። የስታዲየሞች አየር ተመጣጣኝ እንዲሆን ኳታር ተዘጋጅታለች።
አፍሪካ ቡድኖች ለማጣሪያው በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች እጅግ ሞቃታማ የሆኑ ስታዲየሞችን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ለመጫወት ይገደዳሉ። ታዲያ ይህ ለኳታሩ ውድድር ይጠቅማቸው ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኳታራውያን ለሰሜን አፍሪካ አገራት ይደግፉ ይሆን?
ኳታር አረብ ዋንጫን ባለፈው ዓመት አዘጋጅታ ነበር። ለፍጻሜ ቱኒዝያ እና አልጄሪያ ደረሱ። ዋንጫው ወደ አልጀርስ አቀና።
ቱኒዝያ ብዙ ደጋፊ ኳታር ላይ እንዳላት ያወቀችበት ውድድር ነው። ከዴንማርክ፣ አውስትራሊያ እና ፈረንሳይ ጋር ስትጫወት በሜዳዋ የመጫወት ያህል ስሜት ትጠብቃለች።
ሰሜን አፍሪካ አገራት ወደ ጥሎ ማለፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማለፍ ይህን ድጋፍ ይሻሉ።
“የአፍሪካ በተለይም የአረብ አገራት በኳታር መጫወት ይጠቅመናል” ያለው የቱኒዝያው አምበል ዋህቢ ካዚር ነው።
“በተመሳሳይ ድባብ ውስጥ ነው የምንጫወተው። ብዙ ቱኒዝያውያን ዲያስፖራዎች ኳታር ይኖራሉ። በአረብ ዋንጫ ወቅት ቀዩን ማልያ በለበሱ ደጋፊዎች ስታዲየሞች መሞላታቸውን አስተውለናል። ይህም ይረዳናል” ብሏል።
ይህ ለሞሮኮም ይሠራል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አፍሪካውያን አሰልጣኞች የሚያንጸባርቁበት ወቅት ይሆን?
አፍሪካ በራሷ ልጆች አሰልጣኝነት በዓለም ዋንጫ የተወከለችው ከ40 ዓመት በፊት አንድ የአህጉሪቱ ተወካይ ብቻ በነበረበት፣ በስፔኑ የዓለም ዋንጫ ወቅት ነበር።
ረዥም ጊዜ ያገለገሉት የሴኔጋሉ ሲሴ ሲሆኑ የተሾሙት እአአ በ2015 ነው። ሌሎቹ ዓመትም አልደፈኑም።
ቱኒዝያ (ጃሌል ካድሪ)፣ ጋና (ኦቶ አዶ) እና ካሜሩን (ሶንግ) ከአፍሪካ ዋንጫ መልስ ሹመቱን ያገኙ ናቸው።
ሞሮኮ ደግሞ ነሐሴ ላይ ነው ኃላፊነቱን ለዋሊድ ሬግራጉይን ሰጠችው።












