ፈረንሳያዊው አጥቂ ካሪም ቤንዜማ በጉዳት ምክንያት ከዓለም ዋንጫ ጨዋታ ውጪ ሆነ

ካሪም ቤንዜማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ካሪም ቤንዜማ

ፈረንሳያዊው አጥቂ ካሪም ቤንዜማ በልምምድ ወቅት በታፋው ላይ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ዛሬ ህዳር 11፣ 2015 ዓ.ም በኳታር ከሚጀመረው የዓለም ዋንጫ ውድድር ውጪ መሆኑ ተነገረ።

ቤንዜማ የሚጫወትለት የስፔኑ ክለብ ሪያል ማድሪድ የቻምፒዮን ሊግ እና የላ ሊጋ ዋንጫን እንዲያነሳ በማስቻሉ፣ በዓለም እግር ኳስ በየዓመቱ ለምርጥ ተጫዋቾች የሚሰጠውን የ2022 የባሎን ዶር ሽልማት በዚህ ዓመት አግኝቷል።

የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን እንዳሳወቀው ቤንዜማ በታፋው ላይ ችግር ስላጋጠመው፣ በዓለም ዋንጫ ላይ ከአገሩ ቡድን ጋር ተሰልፎ በውድድሩ አይሳተፍም ብሏል።

“ሁሉም የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች ካሪም የሚሰማውን ሐዘን ይጋራሉ፤ ከጉዳቱም በቶሎ እንዲያገግም ይመኛሉ” ብሏል የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን።

የፈረንሳይ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ቤንዜማ የተደረገለት የኤምአርአይ ምርመራ በታፋው ላይ ባለ ጡንቻ ላይ ጉዳት መድረሱን አረጋግጦ፣ ለማገገም ሦስት ሳምንታት እንደሚያስፈልጉት ገልጿል።

ፈረንሳይ በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ውድድር በምድብ መ ውስጥ የምትገኝ ሲሆን፣ በተለያዩ ቀናት በተከታታይ ከአውስትራሊያ፣ ከዴንማርክ እና ከቱኒዚያ ጋር የምድብ ጨዋታዋን ታደርጋለች።

የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣን ዲዲዬ ዴሾ በቡድኑ ውስጥ በጉዳት የማይሰለፈውን የ34 ዓመቱን የቤንዜማን ቦታ የሚሸፍንለት ተጫወችን አስከ ሰኞ ድረስ ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ከአገሩ ብሔራዊ ቡድን ጋር በ97 ጨዋታዎች ላይ በመሰለፍ 37 ግቦችን ያስቆጠረው የካሪም ቤንዜማ በጉዳት ምክንያት ከቡድኑ ውጪ መሆን ለፈረንሳይ ከባድ ጉዳት ነው።

ብሔራዊ ቡድኑ ከቤንዜማ በተጨማሪ አማካዮቹን ፖል ፖግባን እና ንጎሎ ካንቴን በጉዳት ምክንያት ያጣ ሲሆን፣ በጉዳት ምክንያት ለቡድኑ አምስት ጨዋታዎችን ሳይሰለፍ የቆየው የማንችስተር ዩናይትዱ ራፋኤል ቫራኔ ለብሔራዊ ቡድኑ ሊሰለፍ ይችላል የሚል ተስፋ አለ።

በተጨማሪም ባለፈው ረቡዕ በልምምድ ላይ ጉዳት የደረሰበት የላይፕዚጅ የፊት መስመር ተጫዋቹ ክሪስቶፈር ንኩንኩ ከውድድሩ ውጪ ሲሆን፣ አይንትራክት ፍራንክፈርቱ ራንዳል ኮሎ በተተኪነት ተጠርቷል።

የካሪም ቤንዜማን ቦታን በመሸፈን የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድንን ክፈተት ሊሞላ ይችላል ተብሎ የሚጠበቀው፣ ባለፈው ጥቅምት ወር ተመሳሳይ ጉዳት በታፋው ላይ አጋጥሞት የነበረው የማንችስተር ዩናይትዱ አንተኒ ማርቴይል ነው።

የሪያል ማድሪዱ ቤንዜማ ቡድኑ ባለፉት ሳምንታት ባደረጋቸው የመጨረሻ ስድስት ጨዋታዎች ላይ ከግማሽ ሰዓት በታች ነበር መጫወት የቻለው።

የፈረንሳይ የዓለም ዋንጫ ብሔራዊ ቡድን አንድ ላይ ልምምድ ማድረግ ባለፈው ሳምንት የጀመረ ሲሆን፣ ቤንዜማም ለመጀመሪያ ጊዜ በቡድኑ ሙሉ ልምምድ ላይ የተሳተፈው ቅዳሜ ዕለት ነው። በዚህም በታፋው ላይ ጉዳት ገጥሞት ልምምዱን በማቋረጥ ምርመራ አድርጎ ለቀጣይ ሳምንታት ከጨዋታ ውጪ መሆን እንዳለበት ተነግሮታል።

የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣን ዲዲዬ ዴሾ “ይህንን የዓለም ዋንጫ ዋነኛ ግቡ አድርጎ ለነበረው ለቤንዜማ በጣሙን ነው ያዘንኩት” ሲል የተሰማውን ገልጿል።

“ምንም እንኳን ይህ ችግር ቢገጥመንም፣ በቀሪዎቹ ተጫዋቾች ላይ ሙሉ እምነት አለኝ። የሚጠብቁንን ግጥሚያዎች ሁሉ በብቃት ለመወጣት ሁሉንም ነገር እናደርጋለን” ብሏል አሰልጣኙ።