የዓለም ዋንጫ፡ ቤልጂየም በሞሮኮ መሸነፏ ቁጣ ሲቀሰቅስ ስፔን እና ጀርመን አቻ ተለያይተዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በድራማዎች በተሞላው የኳታር የዓለም ዋንጫ ሞሮኮ በፊፋ የአገራት የደረጃ ሠንጠረዥ ሁለተኛ የሆነችውን ቤልጂየምን በማሸነፍ ታሪክ ጽፋለች።
አብድልሃሚድ ሳቢሪ እና ዛካሪያ አቡክላል ያስቆጠሯቸው ጎሎች አፍሪካዊቷን አገር ወደ ድል መልሰዋል።
ሳቢሪ ከፍጹም ቅጣት ምት በቀጥታ በመምታት ነው ኳሷን ከመረብ ያገናኘው።
የቤልጂየሞችን ተስፋ ያሟጠጠችው ጎል በተጨማሪ ሰዓት በአቡክላል ተቆጥራለች።
ድሉ በአል ቱማማ ስታዲም ለተገኙ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሞሮኳዊያን ፈንጠዝያን ፈጥሯል።
ውጤቱን ተከትሎ ሞሮኮዋ ራባት በደስታዋን ስትገልጽ አምሽታለች።
ብራስልስ ደግሞ ደጋፊዎች ባስነሱት ግጭት ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ ለመተኮስ ተገዷል።
የቤልጂየም ደጋፊዎች የሱቆችን መስታዎቶች ሰባብረዋል። ርችቶችን ከመወርወር በተጨማሪ መኪኖችንም ማቃጠላቸው ታውቋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፖሊስ 11 ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።
በምድቡ ሌላ ጨዋታ ክሮሺያ ምድቡን መምራት የሚያስችላትን ድል አስመዝግባለች።
ካናዳን 4 ለ 1 በማሸነፍ ነው ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ተስፋዋን ያለመለመችው።
ካናዳ በአልፎንሶ ዴቪስ የጎል ቀዳሚ መሆን የቻለችው በሁለተኛው ደቂቃ ነበር።
የካናዳን በላይነት ተቋቁመው ወደ ጨዋታው ተመለሱት ክሮሺያዎች በ36ኛው ደቂቃ አቻ ለመሆን ቻሉ።
ክሮሺያ ካርማሪች፣ ሊቫያ እና ማዬር ባስቆጠሯቸው ጎሎች ሦስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል።
ካናዳ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ አለመቻሏን አረጋግጣለች።
ክሮሺያ እና ሞሮኮ ምድቡን በአራት ነጥብ ተከታትለው ይመራሉ። ቤልጂየም አንድ ነጥብ ሲኖራት ካናዳ ያለምንም ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዛለች።
በቀጣይ ካናዳ ከሞሮኮ እና ክሮሺያ ከቤልጂየም በሚያደርጉት ጨዋታ የምድቡ አላፊ አገራት ይለያሉ።
በምድብ አምስት ሲጠበቅ ነበረው የስፔን እና የጀርመን ጨዋታ አንድ አቻ ተጠናቋል።
ጨዋታውን በመቆጣጠር የጀመሩት ስፔኖች ጎል በማስቆጠርም ቀዳሚ ሆነዋል።
ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አልቫሮ ሞራታ ባስቆጠራት ጎል ስፔን ቀዳሚ ሆነች።
ከጎሉ በኋላ ጫና ፈጥረው መጫወት ቻሉት ጀርመኖች እነሱም ተቀይሮ በገባው ኒክላስ ፉልኩግ አማካይነት አቻ ለመሆን በቅተዋል።
ሌሮይ ሳኔ ባለቀ ሰዓት ጀርመንን አሸናፊ የምታደርግ ዕድል አግኝቶ ሳይጠቀምባት ቀርቷል።
በምድቡ ሌላ ጨዋታ ጃፓን በኮስታ ሪካ 1 ለ 0 ተሸንፋለች።
ጀርመንን በማሸነፍ አስደናቂ ድል ያስመዘገበችው ጃፓን በሁለተኛው ጨዋታ እጅ ሰጥታለች።
የኮስታ ሪካን የተከላካይ መስበር የተሳናት ጃፓን በኬይሸር ፉለር ጎል ተሸንፋለች።
ጃፓን ጀርመንን እንደማሸነፏ እና ኮስታ ሪካ ደግሞ በስፔን 7 ለ 0 መሸነፏን ተከትሎ እስያዊቷ አገር በቀላሉ አሸንፋ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፏን ታረጋግጣለች ተብሎ ነበር።
ሆኖም በ81ኛው ደቂቃ በተቆጠረባት ጎል ጃፓን ለመሸነፍ ተገዳለች።
ምድቡን ስፔን በአራት ነጥብ ትመራለች። ጃፓን እና ኮስታ ሪካ በሦስት ነጥብ ይከተላሉ። ጀርመን በአንድ ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
አራቱም አገራት ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ተስፋ አላቸው።
የዓለም ዋንጫው የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ።
በምድብ ሰባት የሚገኙት ካሜሩን እና ሰርቢያ ሰባት ሰዓት ይገናኛሉ።
ጨዋታው በአል ጃኑብ ስታዲየም ይከናወናል።
አስር ሰዓት ላይ ደቡብ ኮሪያ እና ጋና ይጫወታሉ።
ይህ ምድብ ስምንት ጨዋታ ኤጁኬሽን ሲቲ ስታዲየም ላይ ይደረጋል።
በጉዳት ኔይማርን ጨምሮ ተጫዋቾቿን ያጣችው ብራዚል ከስዊዘርላንድ ትጫወታለች።
ጨዋታው አንድ ሰዓት ላይ በዕቃ መጫኛ ኮንቴነር በተገነባው በስታዲየም 974 ይከናወናል።
ሉሳይል ስታዲየም ምሽት አራት ሰዓት የሚከናወንን የምድብ ስምንት ሁለተኛ ጨዋታ ያስተናግዳል።
በጨዋታው ፖርቹጋል እና ኡራጓይ ይገናኛሉ።












