የሳዑዲ አረቢያን ቡድን ለመደገፍ 1600 ኪሎ ሜትር በእግሩ የተጓዘው ደጋፊ

የሳዑዲ አረቢያን ቡድን ለመደገፍ 1600 ኪሎ ሜትር በእግሩ የተጓዘው ደጋፊ

የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ በውድድሩ ታሪክ በአረብ አገር አስተናጋጅነት ሲካሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። በዚህም ትንሽየዋ ነገር ግን ባለፀጋዋ አገር ኳታር ቢሊዮኖችን አፍስሳ ውድድሩን እያካሄደች ነው።

ይህ በኳታር የሚካሄደው የዓለም ዋንጫ በአረብ የእግር ኳስ አፍቃሪያን ዘንድ በልዩ ሁኔታ እየታየ ነው። ከመላው ዓለም ወደ አገሪቱ ካቀኑት በተጨማሪ በርካታ ሰዎች ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ከባሕረ ሰላጤው አረብ አገራት ውድድሩን ለመታደም በተለያዩ መንገዶች ከስፍራው ደርሰዋል።

ከእነዚህም መካከል አብዱላህ አል ሳልሚ ለዘመናት ሲያልመው የነበረውን ፍላጎቱን ለማሳካት በኳታር የሚስተናገደው የዓለም ዋንጫ ዕድሉን ፈጥሮለታል።

አብዱላህ በመጀመሪያ ጨዋታው የእግር ኳስ ታላቅ አገር የሆነችውን አርጀንቲናን በማሸነፍ ዓለምን ያስደመመውን የአገሩን ቡድን ለመደገፍ ከሳዑዲ አረቢያ ጅዳ እስከ ኳታር ዶሃ ያለውን 1600 ኪሎ ሜትር በእግሩ ተጉዟል።

ጉዞው አስቸጋሪ ቢሆንም ኳታር ከደረሰ በኋላ ግን አብዱላህ ዝነኛ ሆኗል።